Monday, May 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የቀላል ባቡር ፕሮጀክትን ከዕዳው ጋር ለመቀበል መቸገሩን ገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የከተማውን ቀላል ባቡር ትራንስፖርት በሥሩ አካቶ ለማስተዳደር፣ ለኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ያቀረበውን ጥያቄ በይደር ማቆየቱን አስታወቀ፡፡ ቢሮው ጥያቄውን በይደር ያቆየው ኮርፖሬሽኑ ከእነ ዕዳው እንዲወስድ ቅድመ ሁኔታ ስላቀረበለት መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ስታጦው አከለ (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡

የትራንስፖርት ቢሮው የከተማ አስተዳደሩን የትራንስፖርት ስትራቴጂ ዝግጅት በተመለከተ፣ ማክሰኞ ታኅሳስ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

ከተሳታፊዎች ስለቀላል የከተማ ባቡር የሥራ ላይ እንቅስቃሴ ችግር ጥያቄ የቀረበላቸው ቢሮው ኃላፊው በሰጡት ምላሽ፣ የቀላል ባቡር ፕሮጀክቱ የታሰበውን ያህል እንቅስቃሴ ያደርግ ዘንድ ቢሮው ተንቀሳቅሶ የነበረ ቢሆንም፣ ፕሮጀክቱን በሥሩ ሊያስተዳድር የሚችለው ያለበትን ዕዳ አብሮ ጠቅልሎ ሲወስድ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ በመግለጹ ጥያቄውን በይደር ሊቆይ እንደቻለ ለተሳታፊዎቹ አብራርተዋል፡፡

የባቡር ፕሮጀክቱ የዲዛይን ችግር አለበት ያሉት የቢሮ ኃላፊው፣ በተለይም በእግረኛ መሻገሪያ ላይ የሚስተዋለው ችግር በከተማው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ  ተፅዕኖ አሳድሯል ብለዋል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ አሁን ጥናት እየተደረገ እንዳለ፣ የከተማ አስተዳደሩ በጀት በመመደብ በመሸጋገሪያ አካባቢዎቹ የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ ወደ ሥራ እንደገባ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በቁጥር 40 ከሚደርሱት የባቡር ፉርጎዎች አሁን በትክክል እየሠሩ ያሉት 16 እንደሆኑ ያስረዱት የቢሮው ኃላፊ፣ ወደ 500 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ብድር ተጠይቆ ወደ ሥራ የገባውን ፕሮጀክት እያስተካከሉ መሥራት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ለተሳታፊዎቹ ገልጸውላቸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ስትራቴጂ አዘጋጅ ቡድን አባል አቶ ኢሳያስ አየለ በበኩላቸው፣ አሁን በ15 በመቶ አቅሙ እየሠራ ያለውን የባቡር ፕሮጀክት ዲዛይን በማሻሻል ችግር በሚቀርፍ ሁኔታ ለመተግበርና የቀላል ባቡር መስመርን በአሥር ዓመቱ ስትራቴጂ ለማራዘም መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ያዘጋጀው የትራንስፖርት ስትራቴጂ አምስት ጉዳዮችን እንዳካተተ ተገልጿል፡፡ እነሱም የትራንስፖርት ፕላኒንግ ልማትና የመሬት አጠቃቀም ቅንጅት፣ የመንገድ መሠረተ ልማት፣ የመንገድ ትራፊክ አስትዳደርና ደኅንነት፣ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትና ተቋማዊ አቅም ግንባታ ናቸው፡፡ ስትራቴጂው በሚቀጥለው ወር ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ቀርቦ ከፀደቀ በኋላ፣ ከግማሽ ዓመቱ የሥራ ዘመን ጀምሮ አገልግሎት ላይ እንደሚውል ተገልጿል፡፡

በኤልያስ ተገኝ

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች