በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ገርጂ አካባቢ በቻይናው ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በመገንባት ላይ የሚገኘው አደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታው ተጀመረ፡፡ የመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ የተጠናቀቀው ይህ ብሔራዊ ስታዲየም በአጠቃላይ ስምንት ቢሊዮን ብር በጀት የተያዘለት መሆኑ ይታወቃል፡፡
በውጪ ምንዛሪ እጥረት ግንባታው እንደተጓተተ የሚነገርለት ብሔራዊ ስታዲየም፣ የመጀመርያው የግንባታ ምዕራፍ መጠናቀቁን ተከትሎ የሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ አካል የሆነው የጣሪያ ተሸካሚ ምሰሶ ሙሌት መጀመሩ ታውቋል፡፡
የስፖርት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጅሎ ግንባታው በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ከሰሞኑ የመስክ ምልከታ ማድረጋቸው ኮሚሽኑ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ምክትል ኮሚሽነሩ የጣሪያ ተሸካሚ ምሰሶ ሙሌት በፍጥነት ተጠናቆ ቀሪ ግንባታዎች መጀመር እንዳለባቸው መመርያ መስጠታቸው በመግለጫው ተካቷል፡፡
ብሔራዊ ስታዲየሙ መጫወቻ ሜዳውን ጨምሮ የጣሪያ ልባስ፣ መሮጫ ትራክ፣ ወንበር፣ ሰው ሠራሽ ሐይቅ፣ ሔሊኮፕተር ማረፊያ፣ የመኪና ፓርኪንግና ሌሎችም የውስጥ ግንባታዎች በሁለተኛው የግንባታ ምዕራፍ ጎን ለጎን ይጠናቀቃሉ ተብለው ይጠበቃሉ፡