Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየሱዳን ሽግግር መንግሥት የገጠመው ፈተና

የሱዳን ሽግግር መንግሥት የገጠመው ፈተና

ቀን:

ሱዳንን ለ30 ዓመታት የመሩት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር ከሥልጣን ከተወገዱ ሁለት ዓመት ሞልቷል፡፡ ከእሳቸው መነሳት በኋላ የተቋቋመው የሽግግር መንግሥት ደግሞ ዓመት አስቆጥሯል፡፡ ዓምና በሱዳን የተቋቋመው የሽግግር መንግሥት የሦስት ዓመት ዕድሜ ያለው ሲሆን፣ አወቃቀሩም ሲቪሎችንና የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮችን አጣምሮ ነው፡፡

ይህ ጥምር ከጅምሩም ሲመሠረት ማን አብላጫ ወንበር ይያዝ በሚል ክርክር ተነስቶበት የነበረ ቢሆንም፣ ተከታታይ ድርድሮች ተደርገው በተደረሰው ስምምነት መሠረት ሲቪሎች አብላጫውን ይዘው ካውንስሉ ተመሥርቷል፡፡

ዓመት ያለፈው ይህን የሽግግር መንግሥት ግን በመከላከያ ክፍሉ ዘንድ ሥራውን እየተወጣ እንዳልሆነ ይኮንናል፡፡ የሱዳን መከላከያ አዛዥ አብድል ፈታህ አልቡርሃን ሰሞኑን በደቡብ ካርቱም ለሚገኘው የመከላከያ ክፍል ባደረጉት ንግግር፣ የሽግግር መንግሥቱን መንቀፋቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ይህም የሲቪሉና የመከላከያውን ጥምር መንግሥት ግንኙነት አሻክሮታል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሱዳን ሽግግር

ጄኔራል አልቡርሃን የሽግግር መንግሥቱን በማናናቅ ብቻ አላቆሙም፡፡ ይልቁንም ጠንካራ አቅም ያለው አንድ አካልም አቋቁመዋል፡፡ ‹‹የሽግግር መንግሥቱን የሚመራው ምክር ቤት ኦማር አል በሽርን ለመጣል የተቀሰቀሰው አብዮት ግብን አልመታም›› ሲሉም ወቅሰዋል፡፡ ‹‹ከተመሠረተ ዓመት ያለፈው ምክር ቤት የሕዝቡን ፍላጎትና የአብዮቱን ዓላማ ማሳካት አልቻለም›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የሽግግር መንግሥቱ ሉዓላዊ ምክር ቤቱ፣ የሱዳን ከፍተኛ አስፈጻሚ ባለሥልጣናትና ካቢኔ የወታደሩና የሲቪል ማኅበረሰብ የተወከሉበት ሲሆን፣ ከእነዚህ የሲቪሉ መቀመጫ ያይላል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2019 በተደረሰው ስምምነትም ጄኔራል ቡርሃን ሉዓላዊ ምክር ቤቱን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ ካቢኔውን እንዲመሩ ነው የተደረገው፡፡

ሆኖም ቡርሃን መከላከያውን አደናንቀው የሽግግር አካል የሆነውን ካቢኔ ‹‹የሕዝቡን ስቃይ አብዝቶታል›› ብለዋል፡፡

መከላከያውም ‹‹ሕዝቡን ለመከላከል የመጀመርያው ኃይል ነው፣ ሕዝቡንና አብዮቱን እንጠብቃለን፤›› ሲሉ ቡርሃን ቃል ገብተዋል፡፡ የሽግግር አካሉ የነበሩና ወደ ሕግ አውጪው ምክር ቤት ውስጥ መካተት የነበረባቸው እንዲካተቱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የሲቪሉና የመከላከያው ጥምር መንግሥት በተመሠረተ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ 300 አባላት ያሉት የሽግግር ፓርላማ እንዲዋቀር ተብሎ ውሳኔ ያገኘ ጉዳይ ነበር፡፡ ይህ ፓርላማ የመቋቋሚያ ጊዜው የሚያበቃው በፈረንጆቹ 2020 ማብቂያ ማለትም ከስምንት ቀናት በኋላ ነው፡፡

በስምምነት የተቋቋመው የሽግግር መንግሥት የሽግግር ጊዜውን የመምራት ኃላፊነት ያለበት ሲሆን፣ ምክር ቤቱ ደግሞ በሽግግር መንግሥቱ የተካተቱ አካላት ልዩነታቸውን በሰላም እንዲፈቱ ኃላፊነት የተጣለበት አካል ነው፡፡

የጄኔራል ቡርሃንን አካሄድ ያልተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ፣ ቡርሃን ባቋቋመው አዲስ አካል ኃይልን አብዝቶ ለመጠቀም እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

በሱዳን የሽግግር መንግሥት ውስጥ የተፈጠረው ቅራኔ ደግሞ ቀድሞውንም አብዮቱ ግብ አልመታም ሲሉ ይወተውቱ ለነበሩ ሱዳናውያን ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓል፡፡

የቀድሞውን የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር የጣለው አብዮት ሁለተኛ ዓመት ለመዘከር ቅዳሜ ታኅሣሥ 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ሠልፍ የወጣው ሕዝብ፣ ዴሞክራሲያዊ ሪፎርም ይደረግ፣ መንግሥት ይወገድ የሚል መፈክር ሲያሰማ እንደነበር ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል፡፡

በብዛት ወጣቶች ተሳትፈውበታል በተባለው ተቃውሞ መከላከያው ከሽግግር መንግሥቱ ይውጣ የሚል ጥያቄም ተነስቷል፡፡ በሱዳን መኖር ከባድ በሆነበት፣ የመከላከያው የሽግግር መንግሥት ተሳትፎ ላይ ሱዳናውያን በተከፋፈሉበትና የሽግግር መንግሥቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲውን መተግበር ባልቻለበት የተቃውሞው መደረግ ለሱዳን ያሠጋታል ሲል ሱዳን ትሪቡን አስነብቧል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት ሱዳንን አብዝቶ የመታው ጎርፍ፣ ዓምና የተከሰተው ኮቪድ-19 እንዲሁም በኢትዮጵያ በሚካሄደው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ወደ ሱዳን በተሰደዱ ዜጎች ምክንያት ሱዳን ተወጣጥራለች፡፡

ዋና ሠልፉ የተካሄደው በካርቱም በሪፐብሊካን ቤተ መንግሥትና በኡምዱርማን ከተማ በፓርላማ ሕንፃ አካባቢ ነው፡፡

በሪፐብሊካን ቤተመንግሥት አካባቢ የቁጭ በሉ ተቃውሞ የተሳተፉ ሱዳናውያን የመከላከያ ኃይል በሽግግር መንግሥቱ ያለው ተሳትፎ እንዲያበቃና የመከላከያው ሉዓላዊ ምክር ቤት እንዲፈርስም ጠይቀዋል፡፡

በኡምዱርማን በተካሄደው ሠልፍ ደግሞ ከመከላከያ ጋር በነበረ የሰላም ውይይት የዘገየው የሽግግር ሕግ አውጪ ምክር ቤት እንዲቋቋም ተጠይቋል፡፡

በሠልፉ የተሳተፉ የዳርፉር ደጋፊዎች ደግሞ የሽግግር መንግሥቱ የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ያድርግ የሚል መፈክር ይዘው መታየታቸውን ዘገባው አስፍሯል፡፡

ባለፈው ዓርብ የሱዳን ኮሙዩኒስት ፓርቲና የሱዳን የሙያ ማኅበራት አዲስ ሴክሬታሪያት በሽግግር መንግሥቱ በተለይም የመከላከያ ጣልቃ ገብነት አያስፈልግም ሲል ሱዳናውያን ተቃውሞ እንዲወጡ ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡

የሱዳን ሽግግር

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...