Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሕፃናትን ከዕይታ ችግር የመታደግ ንቅናቄ

ሕፃናትን ከዕይታ ችግር የመታደግ ንቅናቄ

ቀን:

ባለፈው ሳምንት የመጨረሻ ሁለት ቀናት ውስጥ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሕፃናት ከወላጆቻቸው/ከአሳዳጊዎቻቸው ጋር በአንድ ቦታ ላይ ተሰባስበው ታይተዋል፡፡ እኩሉ ሕፃናት በእናቶቻቸው ጀርባ ላይ የታዘሉ ሲሆን ጥቂቶቹ ደግሞ በአሳዳጊዎቻቸው ትከሻ ላይ ቁጢጥ ብለው ተቀምጠዋል፡፡ በእቅፍ የተያዙም አልታጡም፡፡ ስብስብ ብለው ሲቦርቁም ተስተውለዋል፡፡

ሕፃናቱ የተሰባሰቡበት ይህ ቦታ መዋለ ሕፃናት ወይም የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋም ሳይሆን የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ የዓይን ሕክምና ክፍል ቅጥር ግቢ ነው፡፡ በዚህ ግቢ ያሰባሰባቸውም ምክንያት ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት ክፍሉ ነፃ የዓይን ቅድመ ምርመራ (ስክሪኒንግ) እንደሚሰጥ ያስተላለፈውን ጥሪ በመከተል ነው፡፡

ቤዛዊት ታደገኝ (ዶ/ር) የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ የዓይን ሕክምና ክፍል የሕፃናት የዓይን ስፔሻሊስት ሐኪም ናቸው፡፡ እንደሳቸው አነጋገር በተጠቀሱት ቀናት ውስጥ ከ3 ወር እስከ 15 ዓመት ለሆናቸው 650 ሕፃናት የዓይን ቅድመ ምርመራ ተደርጎላቸው ልዩ ልዩ ዓይነት የዓይን ሕመሞች ተገኝቶባቸዋል፡፡

ከተገኘባቸውም የዓይን ችግሮች መካከል የመንሸዋረር፣ የዓይን ሞራ ግርዶሽ፣ በቀላሉ በዓይን መነጽር ሊስተካከል የሚችል የዕይታ ውስንነት እንደሚገኝበት ነው የተናገሩት፡፡

የተጠቀሱትን ዓይነትና ሌላም ችግሮች የታየባቸው ሕፃናት በሆስፒታሉ ውስጥ ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ መመቻቸቱንና አገልግሎቱም በክፍያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሁለት ቀናት ውስጥ የዓይን ችግር ላሉባቸው 600 ሕፃናት የቅድመ ምርመራ ለማድረግ ታቅዶ እንደነበር፣ ነገር ግን ከዕቅዱ በላይ ተጨማሪ 50 ሕፃናት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደተቻለ፣ ከዚህ በላይ ለመስጠት ግን በሐኪሞቹና በጤና ሠራተኞቹ ላይ ጫና የሚፈጥርና አገልግሎቱንም ለማሳለጥ አስቸጋሪ ሆኖ እንደተገኘ ነው ያመለከቱት፡፡

በዚህም የተነሳ በርካታ ሕፃናት አገልግሎቱን ሳያገኙ እንዲመለሱ መደረጉን፣ ይህን ዕድል በዚህ መልኩ ላጡ ሕፃናት አገልግሎቱን እንዲያገኙ ለሁለተኛ ጊዜ ጥሪ እንደሚደረግ ከስፔሻሊስት ሐኪሟ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ወላጆችና አሳዳጊዎች የልጆቻቸውን ጤና ለመጠበቅ እንዲያመቻቸው ከውልደት እስከ ሁለት ዓመት፣ ከዚያም ከሦስት እስከ አምስት ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ሆነው የቅድመ መደበኛ ትምህርታቸውን ሲጀምሩ፣ እንዲሁም አንደኛ ክፍል  ከመጀመራቸው በፊት፣ ከዚህ ዕድሜ በኋላ በየዓመቱ የዓይን ምርመራ ቢደረግላቸው ጤናቸው የተጠበቀ ሊሆን እንደሚችል ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በኢትዮጰያውያን ሕፃናት ላይ በርከት ያሉ ልዩ ልዩ የዓይን ሕመሞች እንዳሉና ከእነዚህም መካከል ዋና ዋናዎቹ በመነጽር ሊስተካከል የሚችል የዕይታ ውስንነት፣ በልጅነት የሚመጣ የሞራ ግርዶሽ፣ በተለያዩ ምክንያት የሚከሰት የዓይን መስተዋት ጠባሳ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

የዓይን መስታወት ጠባሳነት መንስዔውም የቫይታሚን ኤ እጥረት፣ የኩፍኝና ሌሎች በተህዋስያን የሚመጣ የዓይን መስታወት መቆጣት መሆናቸውን ከስፔሻሊስት ሐኪሟ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ የዓይን ሐኪሞች ማኅበር ፀሐፊ ሰዲቅ ታጁ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ውስጥ ለዓይነ ሥውርነት፣ ለዕይታ መቀነስ፣ መጠንና ሥርጭት ላይ ለማወቅ የሚያስችል አንድ ጥናት በ1998 ዓ.ም. በብሔራዊ ደረጃ መካሄዱን ገልጸው፣ በተደረሰበትም ውጤት መሠረት ከአጠቃላዩ ሕዝብ መካከል 1.6 ሚሊዮን ያህሉ የዓይነ ስውርነት ችግር እንዳለበት መረጋገጡን አስረድተዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል 47 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት እንደሆኑ ከእነርሱም መካከል ከ50 እስከ 60 ከመቶ የሚሆኑት በሕክምና ሊድን የሚችል 0.1 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ዓይነ ስውራን እንደሆኑ ነው ያመለከቱት፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የዓይን ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡባቸው የሕክምና ተቋማት ውስን መሆናቸው፣ ይህም ሁኔታ ለችግሩ መባባስ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ተናግረዋል፡፡ አገልግሎት ከሚሰጡት ተቋማት መካከል ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሕክምና ኮሌጅ፣ የጎንደር፣ የጅማና የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ሆስፒታሎች እንደሚገኙበት ከፀሐፊው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

‹‹የዳግማዊ ምኒልክ ሪፈራል ሆስፒታል በዓመት ለ20,000 ሕፃናት የዓይን ሕክምና፣ ለ4,000 ሕፃናት ደግሞ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት መስጠት ይችላል፡፡ ይህም ቢሆን የቀዶ ሕክምና ለማግኘት ቢያንስ የአንድ ዓመት፣ ምርመራ ለማድረግ ወይም መደበኛውን ሐኪም ለማግኘት የሁለት ወራት ቀጠሮ መያዝ ግድ ነው፡፡ የዓይን ችግር ያለባቸው ሕፃናት ወደ ሕክምና ተቋም ዘግይቶ መምጣትም ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ችግር ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህም የሚያሳየው ነገር ቢኖር በሕክምና ረገድ የተደራሽነት፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ደግሞ የግንዛቤ እጥረትና ችግር መኖሩን ነው፡፡ ችግሩንም ለመቅረፍ እንዲቻል ተደራሽነትን ማስፋት፣ እንዲሁም ቀጣይነትና ተከታታይነት ያለው የማስገንዘቢያ ሥራ ማከናወን በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ ነው ያመለከቱት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...