Thursday, June 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ካፒታል ስድስት ቢሊዮን ብር እንዲሆን ተወሰነ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዓመታዊ ትርፋቸውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ ከቻሉት ስምንት የግል ባንኮች አንዱ የሆነው ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮኖች የባንኩን ካፒታል በእጥፍ እንዲያድግና ስድስት ቢሊዮን ብር እንዲሆን ተወሰነ፡፡

የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ባለአክሲዮኖች የባንካቸውን ካፒታል በዕጥፍ ለማሳደግ የወሰኑት፣ ታኅሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔ ሲሆን፣ ሦስት ቢሊዮን ብር የነበረው የባንኩ የተፈቀደ ካፒታል ወደ ስድስት ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡

ባንኩ እስካሁን ያለው የተፈቀደ ሦስት ቢሊዮን ብር ካፒታል ሙሉ በሙሉ የተከፈለ ሲሆን፣ ተጨማሪውን የሦስት ቢሊዮን ብር ካፒታል ደግሞ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ መወሰኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህንን ካፒታል ለማሟላት የባንኩ ባለአክሲዮኖች ባላቸው አክሲዮን ልክ አክሲዮን እንዲገዙ ቅድሚያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ባለአክሲዮኖች የተደለደለውን አክሲዮን መግዛት ካልቻሉ አክሲዮኖቹን ከባለአክሲዮኖች ውጪ ላሉ ግለሰቦችና ኩባንያዎች ሊሸጥ የሚችል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ወደ ውጭ ከመውጣቱ በፊት ግን በቀዳሚነት ለባለአክሲዮኖች ዕድል ተሰጥቷል፡፡

ባንኩ እንዲህ ካለው ውሳኔ ባሻገር የ2012 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን በተመለከተም፣ የበጀት ዓመቱ ለባንክ ኢንዱስትሪው ፈታኝ የሆነበት ወቅት ቢሆንም፣ ባንኩ ከ2011 አንፃር ሲታይ በስድስት በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ ማግኘት መቻሉን የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አሰግድ ረጋሳ ለጠቅላላ ጉባዔው ገልጸዋል፡፡

የጨረታ ማስታወቂያ

የባንኩ ዓመታዊ ትርፉ ከግብር በፊት 1.07 ቢሊዮን ብር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ይህ አፈጻጸም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የስድስት ከመቶ ብልጫ አለው፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ከተገኘው ትርፍ፣ አንድ አክሲዮን ያስገኘው ትርፍ 320 ብር ስለመሆኑም ተነግሯል፡፡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና ከማሳደሩና የተከፈለ ካፒታል በ26 በመቶ ዕድገት ከማሳየቱ አኳያ፣ መልካም ውጤት ነው ብሎ መውሰድ እንደሚቻልና የባንኩ ጠቅላላ የሀብት መጠን በስድስት በመቶ ጨምሮ 33.8 ቢሊዮን ብር መድረሱንም ታውቋል፡፡

በብዙዎቹ ባንኮች ሪፖርት ውስጥ እንደተካተተው ሁሉ፣ የኦሮሚያ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ የ2012 የሒሳብ ዓመት ለኢንዱስትሪው ፈታኝ የሚባል መሆኑን በመጥቀስ፣ ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰቡ ረገድ ባንካቸው ከ2011 የሒሳብ ዓመት የአራት በመቶ ብልጫ ያለው ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰቡን ገልጸዋል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 27.7 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ፋይናንሲንግን ጨምሮ የተሰጠው የብድር መጠን 20.3 ቢሊዮን ብር የደረሰ መሆኑን የሚገልጸው የባንኩ ሪፖርት፣ የ17 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው ተብሏል፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢ 3.8 ቢሊዮን ብር መድረሱንና ይህም ከ2011  ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ19 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ የተበላሸ የብድር መጠኑ ደግሞ 3.4 በመቶ መሆኑም ታውቋል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በ2012 የሒሳብ ዓመት የነበሩ ፈተናዎች በብዙ አቅጣጫ ከባድ ቢሆንም ባንኩ ጥሩ ውጤት ማስመዝገቡን ይገልጻሉ፡፡ በተለይ ከምንዛሪ ግኝት አኳያ አገራዊና ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች እንደነበሩ አመልክተዋል፡፡

ይህም በሒሳብ ዓመቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ኣሉታዊ ተፅዕኖ እንደነበረውም አስረድተዋል፡፡ ባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያሳየውም፣ በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 229 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ይህ ገቢ ግን ከቀዳሚው ዓመት በ33 በመቶ ያነሰ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የባንኩን ዕድገት በቀጣይነት ለመምራት የሚያስችል ሦስተኛውን የአምስት ዓመታት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ የተገባ ስለመሆኑም የተገለጸ ሲሆን፣ በተለይ በኤሌክትሮኒክ ባንኪንግ አገልግሎት ላይ ከፍተኛ እመርታ የሚያሳይበት ይሆናል ተብሏል፡፡ እንዲሁም የደንበኞችን ቁጥር በመጨመርና በቅርንጫፍ ኔትዎርክ ዕድገት ላይ በሰፊው በመሥራት የአገልግሎት አሰጣጡን በይበልጥ ያሻሽላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የቦርድ ሰብሳቢው አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም የብድር አገልግሎትን በማሳደግና የማይከፈል ብድር በመቀነስ እንዲሁም ወጪዎችን በመቆጣጠር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መቻሉን የጠቀሱት ሰብሳቢው፣ በተመሳሳይ የሠራተኞችን አመለካከት በማነፅ ባንኩን በኢንዱስትሪ ውስጥ መሪ ከሆኑ ተርታ ለማሠለፍ ስለመዘጋጀቱም አስታውሰዋል፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ተፈሪ መኮንን ለሪፖርተር በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ ወደ ትግበራ የገባው የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ የባንኩን ቀጣይ አቅጣጫ ከማመላከቱ በላይ በብዙ ለውጦች በኢንዱስትሪ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲዘልቅ የሚያስችለው ነው ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ እስካሁን ሲጠቀምበት የነበረውን ስያሜ ‹‹ኦሮሚያ ባንክ›› ወደሚል በመለወጥ በገበያ ውስጥ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆኖ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ተፈሪ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለተሻለ አገልግሎትና አሠራር ባንኩ ኦሮሚያ ባንክ የሚለውን መጠሪያ ይዞ በኢንዱስትሪ ውስጥ እንዲቀጥል የሚያስችለውን ዝግጅት ያጠናቀቀ ሲሆን፣ ከአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤትም ለስያሜው ባለቤትነት ዕውቅና አግኝቷል፡፡

እንደ ስያሜው ሁሉ እስካሁን ሲገለገልበት የነበረውን ዓርማ በመቀየር ከስያሜ ለውጡ ጋር የሚስማማ እንዲያውም አዲሱን የባንኩን አካሄድ የሚገልጽ ዓርማ እንደሚኖረውም አቶ ተፈሪ አመልክተዋል፡፡

ባንኩ አዲሱን ስያሜና ዓርማ ይዞ ሦስተኛውን የስትራቴጂክ ዕቅዱን የሚተገብር እንደሚሆንም ፕሬዚዳንቱ ያስረዱ ሲሆን፣ በአዳዲስ የባንክ አገልግሎቶችና ደንበኞችን መሠረት ያደረገ ሥራውን ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ሥራውን ይቀጥላል፡፡

የስም ለውጡን ተከትሎ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ መልካም ስሙን፣ ዝናውንና ገጽታውን ይበልጥ በማሻሻል ከወቅቱ ጋር አስማምቶ ብርቱ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ፣ ኦሮሚያ ባንክ በተጨማሪ የንግድ ብራንድ ስያሜ የባለቤትነት መብት አስመዝግቦ ወደ ተጠቃሚነት ለመሸጋገር መዘጋጀቱን አመልክተዋል፡፡

ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በአሁኑ ወቅት የስትራቴጂክ ጠቀሜታ አላቸው በተባሉ ዘጠኝ በሚሆኑ ድርጅቶች ላይ ኢንቨስት ያደረገ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ፣ ፀሐይ ኢንዱስትሪ፣ ኢትስዊችና ኢልሞ ቂልጡ የቤቶች ግንባታ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 35 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት የቅርንጫፎቹን ቁጥር ከ300 በላይ ያደረሰ ሲሆን፣ 237 የባንክ ወኪሎች አሉት፡፡ 123 የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች ያሉት ባንኩ የኦሮ ካሽ ደንበኞች ቁጥር 139,976 ሲሆን የኦሮ ካርድ ተጠቃሚዎችም 173,905 ደርሰዋል፡፡

ባንኩ 6,002 ሠራተኞችን የያዘ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 4,066 በቋሚነት የተቀጠሩ ናቸው፡፡ የተቀሩት 1,936 ደግሞ ኮንትራት ሠራተኞች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች