ንብ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር በ2012 የሒሳብ ዓመት ከፍተኛ እንደሆነ የገለጸውን የ163 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገብ መቻሉን ገለጸ፡፡
ኩባንያው ታኅሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደገለጸው፣ በሒሳብ ዓመቱ ከተገኘው ትርፍ ውስጥ 142.9 ሚሊዮን ብር የሚሆነውን ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ ያገኘ ሲሆን፣ ሕይወት ነክ ከሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ ደግሞ 20.1 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ገልጿል፡፡
ይህ የትርፍ መጠን በኮቪድ-19 ወቅት መመዝገቡና ኩባንያው በአሥራ ስምንት ዓመት ታሪኩ ያስመዘገበው ከፍተኛው ትርፍ ሆኖ የተመዘገበ ስለመሆኑ አስታውቋል፡፡ በ2011 የሒሳብ ዓመት ኩባንው ከታስ በፊት አትርፎ የነበረው 113.2 ሚሊዮን ብር፣ የኩባንያው የ2012 የሒሳብ ዓመት የትርፍ ዕድገት የኩባንያውን የትርፍ ድርሻ ክፍፍል መጠን ከፍ አድርጎታል፡፡
አንድ አክሲዮን ያስገኘው የትርፍ መጠን 177 ብር ሲሆን፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት ካስገኘው ትርፍ በ13 ብር ወይም የስምንት በመቶ ብልጫ ያለው ሆኗል፡፡ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ኩባያው በጠቅላላ 468.1 ሚሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 427.7 ሚሊዮን ብር ሕይወት ነክ ካልሆነው ኢንሹራንስ፣ እንዲሁም 40.4 ሚሊዮን ብር ከሕይወት ኢንሹራንስ ያገኘው ገቢ መሆኑንም ገልጿል፡፡
በሁለቱም የኢንሹራንስ ዘርፍ በሒሳብ ዓመቱ የፈጸመው የካሳ ክፍያ 228.0 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ለካሳ ክፍያ ያዋለው የገንዘብ መጠን ከ2011 የሒሳብ ዓመት አንፃር ሲታይ የ1.8 በመቶ ቅናሽ ያለው ነው፡፡
ከተከፈለው አጠቃላይ ካሳ ውስጥ ደግሞ 173.3 ሚሊዮን የሚሆነው ወይም 83.3 በመቶ የሚሆነው ወይም 83.3 በመቶ የሚሆን ለሞተር ወይም ለተሽከርካሪ አደጋ የተከፈለ ነው፡፡ የኩባንያው ጠቅላላ ሀብት በተጠናቀቀው 2012 ሒሳብ ዓመት ብር 1.7 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ ወደ 412 ሚሊዮን ብር አድጓል፡፡
የኢንሹራንስ ሥራውን ለመደገፍ ኩባንያው የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ የሚሳተፍ ሲሆን፣ በሪል ስቴቱ በኩል ባለፈው ዓመት አስገንብቶ ካስመረቀው ባለ ሰባት ወለል የድሬዳዋ ሕንፃ በተጨማሪ፣ ለዋና መሥሪያ ቤት የሚያገለግል አራት ቤዝመንት የመሬት ወለልና ሜዛኒን ክፍሎችን፣ እንዲሁም 18 ፎቆች ከፍታ የሚኖረውን የሕንፃ ግንባታ ፕሮጀክትን ከ815.0 ሚሊዮን ብር በላይ በቦሌ መንገድ እያስገነባ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
የኩባንያውን ዕድገትና የለውጥ ሒደት ማስቀጠል የሚያስችሉና በገበያ ውስጥ ያለውን ውድድር በብቃት ሊወጣበት የሚችል፣ በአዲስ አመለካከትና አስተሳሰብ የተቃኙ ስትራቴጂዎችን ያካተተ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚመራበት መሪ ዕቅድ (ስትራቴጂክ ዕቅድ) በውስጥ አቅም በማዘጋጀት፣ በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ትግበራ እንደገባ ኩባንያው ገልጿል፡፡
ኩባንያው የቅርንጫፍ ሥርጭቱን 43 ያደረሰ ሲሆን፣ አገልግሎቱንም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ፣ በአዲስ አባባና በክልል ባሉ ቅርንጫፎች የኮር ኢንሹራንስ ሶፍትዌርን ተግባራዊ በማድረግ ለደንበኞች አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ እየሰጠ ይገኛል፡፡ የኩባንያው የሠራተኞች ቁጥር 401 ደርሷል፡፡