Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ከ582 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉን አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የባንክ ኢንዱስትሪን ከተቀላቀለ አሥራ አንደኛ ዓመቱን የያዘው ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በ2012 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ከ582 ሚሊዮን ብር በላይ ቢያተርፍም፣ ይህ የትርፍ መጠን ግን ከ2011 የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ ቅናሽ ያሳየ ሆኗል፡፡

ባንኩ የ2012 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ይፋ ባደረገበት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደተናገረው፣ የሒሳብ ዓመቱ የትርፍ ምጣኔ ሊቀንስ የቻለበትን ምክንያት፣ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ በተለይ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘና ዓለም አቀፉንና የአገራዊ ኢኮኖሚው መቀዛቀዝ በዋናነት የተጠቀሰ ሲሆን፣ የሒሳብ ዓመቱ በርካታ ገቺ ችግሮች የነበሩበት መሆኑ ተመልክቷል፡፡ እንደ ቦርድ ሊቀመንበር ሰውአለ አባተ (ዶ/ር)፣ የ2012 የሒሳብ ዓመት በአገር ደረጃ ያጋጠሙት ፈተናዎች በባንክ ዘርፍ ላይ የፈጠሩትን ከፍተኛ ጫና በመቋቋም ከግብር በፊት 582.1 ሚሊዮን ብር ትርፍ በማስመዝገብ ትርፋማነቱን ማረጋገጥና ማስቀጠል ስለመቻሉ ተናግረዋል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ የነበሩ ገቺ ምክንያቶች ባስከተሉት ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ ሳቢያ ባንኩ ሊያገኝ ባቀደው የውጭ ምንዛሪ መጠን ላይ ቅናሽ በማስከተሉ የተገኘው አጠቃላይ ትርፍ መጠን ካለፈው የሒሳብ ዓመት የትርፍ መጠን ጋር ሲነፃፀር የ43 ሚሊዮን ብር ወይም የ6.9 በመቶ ቅናሽ እንዲያሳይ ምክንያት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ያም ሆኖ ባንኩ ከእነዚህ ፈተናዎች ጋር ተጋፍቶ በአትራፊነቱ እንዲቀጥል ማድረግ በራሱ ትልቅ ሥልት ተደርጎ መውሰድ ይቻላል፤›› ያሉት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ባንኩ በተለያዩ ተግባራቱ ግን ጥሩ የሚባል ውጤት አሳይቷል ብለዋል፡፡

የጨረታ ማስታወቂያ

የባንኩን 2012 የሒሳብ ዓመት ውጤታማነት ያሳያሉ ተብለው ከተገለጹት ውስጥ የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በ3.3 ቢሊዮን ብር ወይም 31.06 በመቶ ዕድገት በማሳየት 13.9 ቢሊዮን ብር መድረሱ አንዱ ነው፡፡ ከብድር አሰጣጥ ጋር በተያያዘም ባንኩ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው አጠቃላይ የብድር መጠን 3.3 ቢሊዮን ብር ደርሷል ተብሏል፡፡ ይህም ባንኩ የሰጠው የብድር መጠን 40 በመቶ ጭማሪ ያሳየ መሆኑን ነው፡፡ በዓመቱ መጨረሻ ላይም የባንኩ አጠቃላይ የብድር ክምችት ወደ 11.6 ቢሊዮን ብር መድረስ ችሏል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ ከተሰጠው ብድር ውስጥ ለገቢና የወጪ ንግድ የተሰጠው ብድር የ45 በመቶ ድርሻ በመያዝ ከፍተኛው ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ ለግንባታና ኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰጠው ብድር 21 በመቶ፣ ለአገር ውስጥ ንግድና አገልግሎት ዘርፍ የተሰጠው ብድር ደግሞ 19 በመቶው ድርሻ ነበራቸው፡፡

እንደ አብዛኛዎቹ ባንኮች የባንኩ የውጭ ምንዛሪ ግኝት የቀነሰ ሲሆን፣ በሒሳብ ዓመቱ አጠቃላይ ያገኘው የውጭ ምንዛሪ መጠን 139 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ በዓመቱ ከተገኘው አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ ውስጥ የወጪ ንግድ 111 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማስገነት ቀዳሚ ሲሆን፣ ከውጭ አገር በሐዋላና በስዊፍት ከተላከ ደግሞ 28.5 ቢሊዮን ዶላር በማስገኘት በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍና በአገር አቀፍ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ባሳደረው ተፅዕኖ ሳቢያ ከውጭ አገር የሚላክ ሐዋላ መቀነሱ፣ እንዲሁም የኤክስፖርት ሥራ መቀዛቀዙ በውጭ ምንዛሪ ግኝት በኩል የባንኩ አፈጻጸም በተጠበቀው መልኩ እንዳይከናወን አሉታዊ ጫና እንዳሳደረ በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡

የባንኩ ሀብት በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የ4.4 ቢሊዮን ብር ዕድገት ያሳየ ሲሆን፣ ጠቅላላ ሀብቱም ወደ 18.9 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡ ከባንኩ ጠቅላላ ሀብት ውስጥ የተጣራ ብድር 60.9 በመቶውን በመሸፈን ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል ሲል ነው ሪፖርቱ ያመለከተው፡፡

የመክፈያ ጊዜ ያለፈባቸው ብድሮች ወይም የተበላሸ የብድር መጠኑ ከጠቅላላው ብድር ያላቸው ድርሻ 4.64 በመቶ ስለመድረሱም ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የአምስት በመቶ ጣሪያ ያነሰ ቢሆንም፣ ወደፊት ይህ ምጣኔ ከአራት በመቶ ዝቅ እንዲል የባንኩ ቦርድና ማኔጅመንት ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩበት እንደሚገባ የቦርድ ሊቀመንበሩ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ የባንኩን ዓመታዊ ገቢ በተመለከተ እንደተገለጸው፣ 2012 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ ገቢው በ341.6 ሚሊዮን ብር ማሳደጉን አድጓል፡፡ ይህም በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የባንኩ ገቢ 2.17 ቢሊዮን ብር አድርሶታል፡፡  

የጨረታ ማስታወቂያ

ባንኩ የካፒታሉን መጠን በ503.9 ሚሊዮን ብር ያሳደገ ሲሆን፣ ይህም የባንኩን አጠቃላይ የካፒታል መጠን 3.1 ቢሊዮን ብር አድርሶታል፡፡

ባንኩ በበጀት ዓመቱ የተቀማጭ ሒሳብ ደንበኞችን ቁጥር በ268,070 በመጨመር ወይም የ49.6 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉና ይህም አጠቃላይ የደንበኞችን ቁጥር በዓመቱ መጨረሻ ወደ 809,493 ከፍ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ላይ ትኩረት አድርጎ መንቀሳቀሱን ሪፖርቱ አመልክቶ፣ ካሉት ቅርንጫፎች መካከል በ200 ያህሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ብቻ የሚሰጥባቸው መስኮቶችን ከመክፈቱ በተጨማሪ፣ አንድ ከወለድ ነፃ አገልግሎት ብቻ የሚሰጥ ቅርንጫፍ ከፍቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ በዋዲያና ቀርድ ከወለድ ነፃ ሒሳቦች 14,233 ደንበኞችን በመመዝገብ በአጠቃላይ 223.9 ሚሊዮን ብር የተቀማጭ ሒሳብ ለመሰብሰብ ችሏል ተብሏል፡፡   

በበጀት ዓመቱ 37 ቅርንጫፎችን ከፍቷል፡፡ ይህም ባንኩ በአጠቃላይ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2020 የበጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ያሉትን ቅርንጫፎች መጠን 242 አድርሶታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች