ኢጋድ በሚለው ምህፃረ ቃል የሚታወቀው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት 38ኛ የመሪዎች አስቸኳይ ጉባዔውን ባለፈው ቅዳሜና እሑድ ዋና ጽሕፈት ቤቱ በሚገኝበት ጂቡቲ በማካሄድ፣ በቀጣናው ያሉት የፖለቲካና የፀጥታ ችግሮች በተመለከተ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ቀጣናዊ ተቋም የሆነው ኢጋድ አባል አገሮች ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያና ጂቡቲ ናቸው።
ሰሞኑን በተካሄደው አስቸኳይ የመሪዎች ጉባዔ ከአባል አገሮች መካከል የአምስቱ መሪዎች በጉባዔው የተገኙ ሲሆን፣ ኡጋንዳና ደቡብ ሱዳን ግን መሪዎቻቸውን አላኩም። ኡጋንዳ በኢትዮጵያ የሚገኘውን አምባሳደሯን የወከለች ሲሆን፣ ደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንቷን ወክላለች።
የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር የሆኑት የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የጉባዔውን መክፈቻ ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸውም፣ ‹‹የቀጣናችን አባል አገሮች የተለያዩ ፈተናዎችና ሥጋቶች ከውጭም ሆነ ከውስጥ በከበቡበት ወሳኝ ወቅት የሚደረግ የመሪዎች ጉባዔ ነው። ሕዝባችን ከገጠመው ሥጋት ፈተና ለመውጣት መፍትሔ ከእኛ የሚጠብቅበት ወቅት በመሆኑ፣ መፍትሔ የማመንጨት ትልቅ ኃላፊነት አለብን፤›› ብለዋል።
‹‹ይህንን ማድረግ ካልቻልን እስካሁን የተገኙ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች በጀመሩበት ግለት እንዳይቀጥሉ የሚያደርግና ሊቀለብሳቸውም የሚችል እንደሆነ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በመርህ ላይ በተመሠረተ ውይይት መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል፤›› ሲሉ አክለዋል።
ካልሆነ ግን በቀጣናው አለመረጋጋት እንዲስፋፋና ይኼንንም ተከትሎ በሚመጣ ሰብዓዊ ቀውስ የቀጣናው ሕዝቦች ለችግር ሊጋለጡ እንደሚችሉ ገልጸዋል።
በመሆኑም በሠለጠነ መንገድ በውይይት የተጋረጡ ፈተናዎችን መፍታት ጊዜ የሚሰጥ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ፣ ‹‹የገጠሙ ፈተናዎችን ለመፍታት የምናደርገው ጥረትም የአባል አገሮች ሉዓላዊ መብቶችንና በአገሮች የውስጥ ጉዳዮች ከመግባት በመቆጠብ መሆን አለበት፤›› ሲሉም አስገንዘበዋል።
በንግግራቸው ማገባደጃ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ የተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጋብዘዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በሰጡት ማብራሪያ የትግራይ ክልልን ያስተዳድር በነበረው የሕወሓት ስብስብ ላይ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ባይወሰድ ኖሮ፣ ኢትዮጵያን እንደ አገር የመበትን ውጤት ያስከትል ነበር ማለታቸውን፣ ከኢትዮጵያ አልፎ የኢጋድ አባል ወደ ሆኑት ጎረቤት አገሮች ደኅንነት ጭምር የማናጋት አቅም እንደነበረው ማስረዳታቸውን፣ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ለሪፖርተር ገልጸዋል።
የኢጋድ አባል አገሮች እየተወሰደ ስለነበረው የሕግ ማስከበር ዕርምጃ የተሟላ ግንዛቤ እንዲያገኙ ኢትዮጵያ በማድረጓ የተሟላ ትብብር ከአገሮቹ መሪዎች ማግኘቷ፣ የኢጋድ አባል አገሮች የደረሱበትን የመግባባትና የመናበብ ደረጃ እንደሚያሳይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለጉባዔው መናገራቸውን ዲፕሎማቱ ገልጸዋል።
የመሪዎቹ ጉባዔ በአመዛኙ ጊዜ ወስዶ የተወያየው በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ እንደነበር የጠቆሙት እኚሁ ዲፕሎማት፣ ኢትዮጵያም ጉባዔውን በሚገባ እንደተጠቀመችበት አስረድተዋል።
በዚህም የተነሳ በኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ መሪዎቹ የሐሳብ አንድነት ይዘው ጉባዔው መጠናቀቁን ተናግረዋል። ኢጋድ የመሪዎቹ ስብሰባ መጠናቀቅን ተከትሎ ባወጣው መግለጫም ያስታወቀው ይኼንኑ የሚያመላክት ነው።
የመሪዎቹ ጉባዔ በኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ማብራሪያ ካገኘ በኋላ፣ በትግራይ ክልል የተካሄደው ዘመቻ የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የማስጠበቅ፣ እንዲሁም የአገሪቱን አንድነት በመጠበቅ መረጋጋት ለመፍጠር የተወሰደ መሆኑን በመገንዘብ የተወሰደው ዕርምጃ ተገቢነትን ጉባዔው እንደተቀበለ አመልክቷል።
በኢጋድ ጉባዔ ላይ የተገኙት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ማህመት የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የወሰደው ዕርምጃ፣ ‹‹የአገሪቱን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለማስከበር›› መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ሁኔታ በየትኛውም አገር ቢከሰት የትኛውም መንግሥት ሊወስደው የሚችል ሕጋዊ ኃላፊነት መሆኑን አመልክተዋል።
‹‹ነገር ግን በትግራይ ክልል ውስጥ የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ ከፍተኛ መጠን ያለው መፈናቀል መከሰቱን መካድ አይቻልም፡፡ በዚህ ረገድ ኢጋድ ለስደተኞችና ለተፈናቀሉ ሰዎች የተለየ ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያ ከምታደርገው የሰብዓዊ ድጋፍ ጥረት ከጎኗ ሊቆም ይገባል፤›› ብለዋል።
ሪፖርተር ያነጋገራቸው ዲፕሎማት እንደገለጹት፣ የመሪዎቹ ጉባዔ በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ የሰጠውን ትኩረት ያህል በሌሎች ቀጣናው ላይ በተደቀኑ ፖለቲካዊ ውጥረቶች ላይ የሚገባውን ያህል አልተወያየም።
በኬንያና በሶማሊያ መንግሥታት መካከል እየተካረረ የመጣው ፖለቲካዊ ውጥረት ትኩረት እንዳልተሰጠው ሁሉ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር ይገባኛል ፖለቲካዊ ውጥረትም የጉባዔውን ትኩረት እንዳላገኘ ገልጸዋል።
በተመሳሳይም በደቡብ ሱዳን የዘገየው የሽግግር ሒደት ተገቢውን ትኩረት እንዳላገኘም አስረድተዋል።
የመሪዎቹ ጉባዔ እነዚህን ጉዳዮች አንስቶ በመወያየት የመፍትሔ አቅጣጫ የመፈለግ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም፣ ከጉባዔው ውጪ በመሪዎች የተካሄዱ የተናጠል የጎንዮሽ ውይይቶች የጎሉበት እንደነበርም አውስተዋል።
ከእነዚህም መካከል በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የድንበር ውዝግቡን የተመለከተ ውይይት ሲካሄድ በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል፣ በሶማሊያ ምርጫን የተመለከተ ውይይትና በኬንያና በሶማሊያ መካከል ከሰሞኑ ተነስቶ ስለነበረው አለመግባባት በኢትዮጵያና በኬንያ መሪዎች ውይይት እንደተካሄደበት ዲፕሎማቱ ገልጸዋል።
ኢጋድ የመሪዎቹ ጉባዔ መጠናቀቅን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ በውይይቱ የተላለፉ ወሳኔዎችን ይፋ አድርጓል።
የመሪዎቹ ጉባዔ የሶማሊያ መንግሥት የፀጥታ ኃይል በሶማሊያ ከተሰማራው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ጦር ጋር በመቀናጀት፣ አልሸባብን ለመግታትና ለመዋጋት ያደረገውን ጥረት አድንቋል።
የሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግሥትና ሶማሌላንድ የጋራ ውይይት እንደገና መጀመራቸውን አድንቆ፣ የቀጣናው አገሮች ውይይቶችን በማስተናገዳቸውና በማስተባበራቸው ምሥጋና አቅርቧል።
ሶማሊያን በተመለከተ ባሳለፈው ውሳኔ፣ ሶማሊያ በመጪው የካቲት ወር ፌዴራላዊ ምርጫ ለማካሄድ እያካሄደችው ያለውን ዝግጅትና በሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግሥትና በፌዴራሉ አባላት አመራሮች መካከል ባለፈው መስከረም ወር የተፈረመውን ፕሮቶኮል ተቀብሎ፣ ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
ሱዳንን በተመለከተ በአገሪቱ ከሁለት ዓመታት በፊት የተከሰተውን ሕዝባዊ አብዮት ተከትሎ፣ ዴሞክራሲያዊ ሽግግግር ለማድረግ እየተደረገ ያለውን ጥረት አወድሷል።
የሱዳን ሕዝብና መንግሥት ከሚመለከታቸው ወገኖች የጁባ የሰላም ስምምነት መፈረማቸውን አድንቆ፣ ስምምነቱ በእምነትና በተሟላ መንገድ እንዲፈጸም፣ እንዲሁም ባለድርሻ አካላት የሽግግር ወቅት ሕግ አውጭ ምክር ቤት በአፋጣኝ እንዲመሠርቱ ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም የሱዳን መንግሥት አሜሪካ ከያዘቻቸው አሸባሪነትን የሚደግፉ አገሮች ዝርዝር ውስጥ በመውጣቱ፣ በይነ መንግሥታቱ የተሰማውን ደስታ ገልጿል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች ለሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነት እንዲሠሩ፣ የሱዳን መንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሽግግር ጊዜ ሕግ አውጭ ምክር ቤት እንዲመሠርቱም ጥሪ አቅርቧል፡፡
ከደቡብ ሱዳን ጋር በተያያዘ የአገሪቱ መንግሥትና ፓርቲዎች በአገሪቱ ያለውን ግጭት ለመፍታት ላሳዩት ቁርጠኝነት፣ ስምምነት የተደረሰበትን የመንግሥት መዋቅር ምሥረታ ለመተግበር እያደረጉ ያሉትን ጥረት በበጎነት አውስቷል፡፡
ኢጋድ በጉባዔው ማጠቃለያ ላይ ባወጣው መግለጫ የአገሪቱ መንግሥትና ፓርቲዎች በተሻሻለው የደቡብ ሱዳን የግጭት የውሳኔ ሐሳብ ትግበራ ላይ ያሳዩትን ጥረት በበጎነት አንስቷል።
በተጨማሪም የአገሪቱ ተቀናቃኝ ኃይሎች ያቋረጡትን የሰላም ድርድር እንዲቀጥሉ፣ ከዚህ ቀደም የደረሷቸውን ስምምነቶች ተፈጻሚ ያደርጉ ዘንድም አሳስቧል፡፡
ከዚህ ባለፈም በአገር ምሥረታው ላይና በዘጠኝ ክልሎች በተካሄደው የሥልጣን አሰጣጥ ሒደት የተደሰተ መሆኑን በመጥቀስ፣ በአገሪቱ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሪክ ማቻር ላይ ምንም ዓይነት የጉዞ ዕገዳ አለማስተላለፉን ገልጿል፡፡
ብሔራዊ የሽግግር አንድነት መንግሥት የአስተዳደር መዋቅር በማቋቋሙና አሁንም በተቀመጠው ማዕቀፍ የሰላም ውይይት እንደገና በመጀመሩ፣ እንዲሁም በመንግሥት መዋቅር ምሥረታው ላይ ለተሳተፉ አካላት ምሥጋና አቅርቧል።