የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም የክስ መዝገብ ተከሰው በሌሉበት ሞት ተፈርዶባቸው የነበሩትና ላለፉት 30ዓመታት በጣሊያን ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በጥበቃ ስር የነበሩት ሌፍቴናንት ጀነራል አዲስ ተድላና ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህ በአመክሮ እንዲፈቱ ትእዛዝ ሰጠ።
ዛሬ የቀረበለትን የተዘጋ መዝገብና የአመክሮ ጥያቄ የተመለከተው ፍርድ ቤት፣ ሁለቱ የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከጣሊያን ኤምባሲ በአመክሮ እንዲለቀቁ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ለፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግና ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ትዕዛዙ በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለጣሊያን ኤምባሲ፣ እንዲሁም ሌፍቴናንት ጀነራል አዲስ ተድላና ለኮሎኔል ብርሃኑ ባየህ እንዲደርስም ፍርድ ቤቱ አዟል፡፡
ሁለቱም የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው የነበረ ሲሆን፣ በኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሞት ፍርዱን ወደ እድሜ ልክ እስራት እንዲቀየርላቸው በማድረጋቸውና ዕድሜ ልክ እስር የተፈረደበት ሰው ደግሞ በአመክሮ መፈታት የሚችለው 20 ዓመት ውስጥ እስር ላይ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፍርድ ቤቱ ከእስር እንዲፈቱ ትእዛዝ ሰጥቷል።
ሁለቱ የደርግ ባለስልጣናት የፍርድ ቅጣታቸውን በወህኒቤት ታስረው ባይፈጽሙም ፣በጣሊያን ኤምባሲ ያሳለፉትየ30ዓመታት ጊዜ እንደ እስር ቅጣት ተቆጥሮ የአመክሮ መብታቸው እንዲከበር ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀረበው ማመልከቻ መሠረት፣ ፍርድ ቤቱ በአመክሮ እንዲለቀቁ መወሰኑን ሪፖርተር ለማወቅ ችሏል።