Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ዘመናዊ ደጅ ጠኚዎች!

ሰላም! ሰላም! ያው በየሳምንቱ አዳዲስ ነገር ፍለጋ ላይ የሚያሰማራን ኑሯችን ስንቱን ያሰማናል መሰላችሁ? አንዱ አሜሪካ ሆኖ ለመንግሥት የሹመት ጥያቄ ያቀርባል አሉ፡፡ ምን ስለሆነ ነው ባህር ማዶ ሆኖ ሹመት ስጡኝ አለ ተብሎ ሲወራ አንዱ ምን ቢል ጥሩ ነው? ‹‹የዘንድሮ ሹመት እንደ ባቄላ እሸት መንገድ ላይ የሚቸረቸር መስሎት ይሆናል…›› አለ አሉ፡፡ አንዱ ደግሞ ከአሜሪካ መጥቶ አንዴ ገዥው ፓርቲ ዘንድ ሌላ ጊዜ ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋ ቢመላለስም ነገሬ የሚለው ያጣል አሉ፡፡ ከዚያ ምን ቢል ጥሩ ነው? ‹‹ድሮም ይህች አገር ደህና ሰው አይወጣለትም ብሎ…›› ብሎ ወደ ‹ፓርኪንጉ› ሄደ አሉ፡፡ አንዱ ደግሞ ውጭ አገር ታዋቂ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው የሚያስተምረው አሉ፡፡ እሱ ሆዬ እዚህ አገር ውስጥ ያሉ ምሁራንና ባለሙያዎችን ከመጠን በላይ ይንቃል ነው የሚባለው፡፡ አንድ ቀን አንድ ለምድር ለሰማይ የከበዱ ባለሥልጣን ዘንድ ይደውልና፣ ‹‹ምን እየሠራችሁ ነው?›› ይላቸዋል፡፡ እሳቸውም በትህትና፣ ‹‹አገር እያስተዳደርን ነው…›› ይሉታል አሉ፡፡ አጅሬው ይኼን ጊዜ ከት ብሎ ስቆ፣ ‹‹እኔ በሌለሁበት እንዴት ነው አገር ማስተዳደር የምትችሉት?›› ሲላቸው፣ ‹‹ደጅ ጠኚ ከመቼ ወዲህ ነው እንዲህ የሚንቀባረረው እባክህ?›› ብለው ቆሌውን ገፈፉት ተባለ፡፡ ስንት ጉዶች አሉ እባካችሁ!

ታዲያ አንዳንዱ ደረስኩ ባይ ወግና ሥርዓት የማያውቅ የዘመኑ ሰውፋስት ፉድበለመደበት ሥልጠንምፋስት ፉድሲመስለው ስታዩ ጉድ ያሰኛችኋል። በእንዲህ ዓይነቶች ጥራዝ ነጠቆች መቀለድ የምንወደው እኔና ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነን፡፡ ዕድሜ ጠገብ የሆነውን ሥልጣኔ በሥርዓተ አልበኝነት ካልሻርን ብለው የሚላተሙ አፍለኞችንና ማገዶ ሲፈጁ የኖሩ አልበስል ባዮችን አራዶች ሲያላግጡባቸው ደስ ይለናል እውነቴን ነው የምላችሁ የማንም ጥርብ እየተነሳ በአቋራጭ ሥልጣን ካላገኘሁ አቧራ አስነሳለሁ ሲል፣ ምን ያህል ከሥልጡንነት ርቆ የድንጋይ ዘመን ሰው እንደሚመስለን እኔና ምሁሩ ወዳጄ ብቻ ነን የምናውቀው፡፡ በተቃራነው ደግሞ አጉል ዘመናዊነትን የዕውቀት ቁንጮ አድርገው ለማሳየት የሚመፃደቁ አንዳንዶች፣ የያዙትን ዘመናዊ ሞባይል ስልክ አጠቃቀም አለማወቃቸውን ስትረዱ ‹‹ድንቄም›› ማለታችሁ አይቀርም፡፡ አለባበስ፣ ፀጉር አቆራረጥ፣ አካሄድ፣ አነጋገር፣ ወዘተ. ብቻውን ምን ይረባል? በላዩ ላይ ደርበብ ያለ ዕውቀት ካልታከለበት ባዶ ጉራ ምን ይፈይዳል? ብቻ ተውት አዛውንት ተብዬዎችም ብሶባቸዋል!

 ያው እንደሰማችሁት ለዓመታት ለዓመታት ከተንሰራፉበት ሥልጣን ተባረው ዴሞክራሲያዊና ሰላማው የፖለቲካ ፉክክር ተለማመዱ የተባሉ ነውጠኞች፣ አሻፈረኝ ብለው በጫሩት እሳት ተቃጥለው ደብዛቸው ሲጠፋ ነግ በእኔ ተብሎ ትምህርት መቅሰም ደግ ነው አያስብልም? ‹‹ለአገራችን ትንሳዔ ቢሆንም እኛም በሕይወታችን ብንማር ምን ነበረበት?›› ስለው ምሁሩን የባሻዬን ልጅ፣ ‹‹ነበር ምን ዋጋ አለው! የእናት አገር ፍቅር በትርጉም አልባ የእርስ በርስ ጥላቻና መናናቅ አከርካሪው እየተመታ እንጂ፣ መማርን የመሰለ ምን አለ ብለህ ነው?›› ቢለኝ ክው አልኩ። መቼም አንድ ነገር ሰምቼ ሌላ የሚጎተት ነገር እየበዛብኝ ተቸግሬላችኋለሁ። ነገር ሰንጣቂ የሚባለው እንደ እሱ ዓይነቱ ይሆን? አንዳንዱ የተማረ የሚባለው ግን በአብዛኛው ለምን ይሆን ነገር ሰንጥቆ ሲያበቃ ከመልካሙ ነገር ይልቅ ቅንነት የጎደለው ነገር ላይ ሲያተኩር የምንታዘበው? ‹‹የአገር ፍቅር ዕውን አንተ በምትለው መንገድ አከርካሪው ቢመታ ኖሮ እኔና አንተ በሰዎቹ ፍፃሜ ላይ ቆምን እናወራ ነበር ወይ?›› ስለው፣ ‹‹ወዳጄ ይህች አገራችንማ ዕድለኛ ናት፡፡ ሊያጠፏት ሲያደቡ እነሱው ይጠፋሉ፡፡ አለቀላት ሲባል ትንሳዔዋ ይበሰራል፡፡ ትውልዱ ነቅዞ ጠፋ ብለህ ስትቆዝም በየአቅጣጫው ጀግና ትውልድ ይተማል…›› ሲለኝ ልቤ በተስፋ ሞላ፡፡ ይኼ ‹‹ድሮ ቀረ›› የምንለው ተስፋ አስቆራጭ ነገር ከመዝገበ ቃላታችን ውስጥ መውጣት አለበት፡፡ ሁሌም ተስፋ ነው ስንቃችን!

አዛውንቱ ባሻዬ ደግሞ እንዲህ ለመሳሰለው ተዓምር መሰል ወሬ መናኸሪያ ናቸው። ማለቴ ያው ከዕድር ሰዎቻቸው ጋር እንዲህ ዓይነት ወሬ ካገኙ ቁጭ ብለው ሲሰልቁ ነው የሚውሉት። ታዲያ ሲያገኙዋችሁ እናንተም የመቀላቀል ግዴታ ይኖርባችኋል። በተረፈ የምትሠሩት ሥራ ወይም የምትሄዱበት ቀጠሮ ለእሳቸው ምንም ነው። በነገራችን ላይ እንዲህ ያሉ ሰዎች እኮ ጥቂት አይደሉም። ለምሳሌ ጣደፍ፣ ጣደፍ እያላችሁ ስትጓዙ እጁን በሁለቱ የጃኬት ኪሶቹ ከቶ ጅንን እያለ የሚራመድ የምታውቁት ሰው ያጋጥማችኋል። ከአንገታችሁ ጎንበስ ብላችሁ ሰላምታ ሰጥታችሁ መንገዳችሁን ልትቀጥሉ ስትሉ፣ ‹‹አንተን አይደል እንዴ ስፈልግ የነበረው?›› ይላችኋል። ክንዳችሁን በፈረጠመ ክንዱ ጨብጦ እያሳመመ በትዕቢት ያናግራችኋል። ‹‹የአንዳንዱ ሰው የመዳፍ ስፋት የድሮ እህል እንቅብ ነው የሚያክለው…›› ይላሉ ባሻዬ። ባሻዬን በኖሩበት ዘመን እንዲህ ያለ ንፅፅር ሲያቀርቡ፣ ልጃቸው በበኩሉ፣ ‹‹የእኔ ትውልድ ደግሞ ችግሩም መፍትሔውም ጉልበት ላይ ሆኖበት፣ የሚበጀውን ለማሳካት ሲል ብቻ የሐሜትና የአሉባልታ ፍጆታ ያደርገናል…›› ይላቸዋል ልዩነቱ በደንብ እንዲገባቸው። ሁሉም በመሰለው መንገድ የሚፈልገውን ሲናገር እኔ ሥራዬ ማዳመጥ ብቻ ነው፡፡ ሰምቶ አዳሪነት ልሞክር እንዴ!

‹‹የምግብ ጥያቄ በተመለሰበት አገር ምግብ በቀን አራቴ ማግኘት ግዴታ ነው። በእኛ አገር ደግሞ ምግብ ለማግኘት የራስ ዳሸን ተራራን ያህል ከባድ ነው…›› የሚለኝ የባሻዬ ልጅ ነው። ይህቺ ይህቺ ደግሞ ትጥፋን እንዴ? ድህነትና የምግብ እጥረት ከዚህ ውጪ እንድናስብ ስለማይፈቅዱ ዕድል በዚህ ቢፈታ አንገረም። እናም ስለዚያ ስላስቆማችሁ ሰው ስጨርስላችሁ፣ የባጥ የቆጡን ወሬ ሊያወራችሁ ሲፈልግ በአንዴ ሥራ አጥ አድርጓችሁ ያርፋል። እናንተ የሚጠብቃችሁ ሥራ ወይም ጉዳይ ጊዜ አይሰጥም፡፡ ይኼ ወጠምሻ ደግሞ እንቅ አድርጎ ይዞአችሁ፣ ‹‹እንዴት ነው እባክህ? ጠፋህ እኮ? አምሮብህ የለም እንዴ? በወር ገቢህ ስንት ደረሰ…›› እያለ ማውራት ይጀምራል፡፡ ወደ ሥራችሁ እንደምትቸኩሉ ስትነግሩት፣ ‹‹ምን ከዘንድሮ ጠብ የማይል ሥራ የተሠሩትን ሕንፃዎችና መንገዶች እየዞሩ ማየት ይሻላል…›› እያለ ሲስቅ፣ ከጤነኛ ጋር እየተነጋገራችሁ መሆኑን ትጠራጠራላችሁ፡፡ በምግብ ነው ወይስ በመድኃኒት እንዲህ ሰፊ የሀብታም እርሻ መስሎ የሚንቀሳቀሰው ማለታችሁም አይቀር፡፡ ብቻ አያጋጥም ነው፡፡ ካጋጠመ ግን ከዘመኑ ነውጠኛ ፖለቲከኞች ወይም አክቲቪስቶች ተርታ ሊሆን ይችላል፡፡ ምናለሽ ተራ ይምጣብኝ!

ባሻዬ የስምተኛው ሺሕ ምልክት የሚሉት ሰሞነኛ ጨዋታ አምጥተዋል። ምን መሰላችሁ? ሁሉም ነገር በሺሕ መተመን፣ መጠራትና መቆጠር ከጀመረ እንደ ባሻዬ አባባል በቃ የስምንተኛው ሺሕ ምልክት እሱ ነው። እስኪ ጥቀሱ ሲባሉየጤፍ ዋጋ፣ የቤት ኪራይ ንረት፣ የእህል ገበያ፣ ጉቦ፣ የሕዝብ ብዛት…’ እያሉ ብዙ ይዘረዝራሉ። እኔም ሳዳምጣቸው እቆይና ሁሌም የማይዘሉትንጉቦ’ ‹‹ደግሞ እሱ ምኑ ይሆን በመሠረታዊ ምልክትነት ያስቆጠረው?›› ብዬ ግራ ገብቶኝ እጠይቃለሁ። ‹‹አይ ልጅ አንበርብር! ጉቦማ መቼም ቢሆን አብሮን የሚኖር ባላንጣ ደባላችን ነው። ትተን ማስተው ስላልቻልን እንደ መብት በየመሥርያ ቤቱና በየጉራንጉሩ የሚጠየቀው የእጅ መንሻ መጨመር ሊያሳስበን ይገባል። ምን ነካህ? ዋናውን?›› ሲሉኝ አንገቴን ደፋሁ። በድርጊቴ ተፀፅቼ ቀና ብዬ ዓይናቸውን ማየት አፈርኩ። እሳቸውም ገብቷቸው፣ ‹‹ተወው ልጄ! ተወው! ብቻህን ተናደህ አትችለውም ልጄ፣ ብቻህን ጮኸህ አትዘልቀውም…›› ሲሉኝ ተናደድኩ።ዱብ ዱብ ባይ እንደ በረዶ…የሚለው ፉከራችን ለምን ይሆን የጦር ሜዳ ብቻ ወኔ የሚሆነን? ‹‹ሌብነትን ከመዋጋት ከአንድ ብርጌድ ጋር መዋጋት ይቀላል…›› ያሉት የአራዳ ልጆች ናቸው፡፡ ወይ አራዳ!

ከባሻዬ ጋር እንዲህ ስል እቆይና እግሬ ወስዶኝ ልጃቸውን ያገኘሁት እንደሆነ ደግሞ፣ ከእሱም ጋር ቆም ብዬ አንድ ሁለት እባባላለሁ። አንድ ሁለት ስል እጫወታለሁ ማለቴ ነው። በጠራራ ፀሐይ ያላበው ቢራ የሚያንቆረቁር ስታዩ እኔ ትዝ እንዳልላችሁ አደራ፡፡ ግን እንዲህ ያሉት ሰዎች እንዴት ቢደላቸው ይሆን ሕዝበ አዳም ሲራወጥ እነሱ ተረጋግተው የሚጋቱት? ለነገሩ አትፍረድ ነው፡፡ ምን ይታወቃል የዘንድሮ ሐኪም የማያዘው ነገር አለ ብላችሁ ነው? ‹‹ምነው በቀኑ?›› ብትሉት፣ ‹‹ተረጋጋ ሐኪም አዞልኝ ነው…›› ሊላችሁ ይችላል። ታዲያ መቀበልግድ ነው። ዘንድሮ ካመኑበት መድኃኒት የማይሆን ምን አለ ብላችሁ ነው? ጉድ ነው እኮ፡፡ ባለፈው ሰሞን ከእዚህ ጋር በተያያዘ የሰማሁትን የሱስ ቀልድ ላጫውታችሁ። አባትቼን ስሞከር’ (‘ሰንሰለት አጫሽብዬ ብተረጉመው አይክፋችሁ። ሕልምና እንግሊዝኛ እንደፈቺው ነዋ! ስንቱ አሜሪካ የገባው በምን መሰላችሁ?) የሚባል ነው። ኋላ ሳንባውን ይታመምና ለጥቂት ጊዜ ማጨስ እንዲያቆም ይነገረዋል። እንዳልኳችሁቼንአጫሽ ስለሆነ ግን በአንዴ መተው አይችልምና በይዘቱ ቀላል የሚባል ሲጋራ እንዲያጨስ ታዘዘ። ለአባትዬው ሁሌም ሱቅ እየተመላለሰ ትምባሆ የሚሸምተው ልጁ ቀላል ተብዬውን አንድ ቀን ሲሞክር አባት ደረሰበት። ወዲያው በመምከርና በመገሰፅ ፋንታ፣ ‹‹እውነትህን ነው ዶክተር እየተጫወተብኝ ነው። እሱ ለእናንተ ነው ለእኔ ያንን የለመድኩት ገዝተህልኝ ና…›› አለና መልሶ ልኮት አረፈው። ከቀልድነቱ አልፎ እውነት ቢሆንስ የሚለው ሐሳብ ሲጫነኝ፣ የዘንድሮ ወላጅና አስተዳደጉ ጉዳይ ሕመሜ ነውና ይነሳብኝ ጀመር። በስንቱ ታምሜ ልችለው ይሆን ግን? በዚህ ማኅበራዊ ጉዳያችን በዚያ ፖለቲካችን!

የእኔ ነገር የባሻዬን ልጅ ሳገኘው ብዬ ጀምሬ አልጨረስኩላችሁም። አዎ! የባሻዬን ልጅ አባቱን አግኝቼ በተለየሁበት ስሜት ሆኜ ሳገኘው የማወራው አይቶና ሳያዩ ስለማደግ ነው። ‹‹አይተን ስለማናድግ እኮ ነው ብር ብርቃችን ሆኖ አገር በሌብነት የታመሰችው…›› ስለው በፖለቲካ ያብራራልኛል። ‹‹ልክ ነህ አንበርብር፡፡ ‹‹አገሪቱን ሲዘርፉና ሲያዘርፉ የኖሩት ሰዎች እኮ ግማሹ ፍየል ጠባቂነት፣ ሌላው ከተማሪነት፣ የተቀረው ከአነስተኛና ጥቃቅን የተገኙ መናጢዎች ነበሩ፡፡ ካዝናውን ተከፍቶ ሲያገኙት አንድም ሳያስቀሩ ሲያራቁቱ የኖሩት እኮ ድህነት እንደ ትኋን ሲልሳቸው በማደጋቸው ነው…›› እያለ ሲያወራ ገረመኝ፡፡ እኔ ደግሞ እነዚህ ጉዶች የተረገሙ ቢሆኑ እንጂ በድህነት ቢማቅቁም በሥነ ምግባር የታነፁ የአገሬን ልጆች ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ድህነት በአዕምሮ መስነፍ እንጂ ዕጦት የሰውን ልጅ ነፍስ አያባልግም፡፡ ያገኙትን የአገር ሀብት ሲዘርፉ የኖሩት ግን የሆነ ደዌ እንዳለባቸው ነው የገባኝ፡፡ ለማንኛውም አንዱ ሲናገር ሌላው ማድመጥ ትቶ እንጂ፣ የሁሉም ነገር መፍትሔ ሚዛናዊ ይሆን ነበር። የሚቃወመውም የሚደግፈውም፣ ገዥውም፣ ተገዥውም አገርን ማዕከል ቢያደርጉ ምንኛ በታደልን ነበር። ያውም ዕድሜ ለማይረቡት ነፍሶች በቃርሚያ ወሬ ስንቱ የሚያዝገን አገርና የግል ጉዳዩ እየተምታቱበት እኮ ነው፡፡ አይምታታባችሁ!

እስኪ በሉ እንሰነባበት። ከባሻዬ ልጅ ጋር ሰዓታችንን አመቻችተን በጊዜ ግሮሰሪያችን ተገኝተናል። ‹‹አየህ እንዴት የባጥ የቆጡን ስናወራ ሳምንቱ ያለ ሥራ እንደሚከንፍ?›› አልኩት የጊዜው ሩጫ ገርሞኝ። ‹‹ምን ታደርገዋለህ? ቫት ያልተጀመረው ወሬ ላይ ብቻ ሆኖ እኮ ነው?›› ሲለኝ የሳምንቱን ምርጥ ሳቅ ከልቤ ሳቅኩኝ። ‹‹እውነቴን እኮ ነው አንበርብር! ግማሹ ኢንተርኔት ላይ ተጥዶ እየዋለ ጦር ሜዳ ከሚዋደቀው በላይ ጀግና ነኝ ይላል፡፡ ስንትና ስንት ምሁራንና ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ባሉባት አገር ውስጥ፣ ከየት እንደተገኘ የማይታወቅ ዶክትሬት ላያቸው ላይ ለጥፈው ካልተሾምን አገሪቱ አለቀላት ይሉናል፡፡ በየአገሩ ከ‹ነርሲንግ ሆም› እስከ ‹ፓርኪንግ› እና ቤንዚን ቀጂነት ሲንከራተት የኖረ ደግሞ አማካሪ ካልሆንኩ እያለ ትከሻውን ያሳየናል…›› ካለኝ በኋላ፣ ‹‹አንበርብር ምን መሰለህ? አገሬን ልርዳ፣ በሙያዬ እንዳገለግላት ዕድል ይሰጠኝ፣ ወዘተ ማለት የአባት ነው፡፡ እንዲያው እንደ በረገገ በግ መሆን ግን ይደብራል፡፡ የአራዳ ልጆች ምን ይላሉ መሰለህ? የሆነ ነገር ሲደብራቸው ‹ላሽ በል!› ነው የሚሉት፡፡ የዘመኑ ደጅ ጠኚዎች ሲያበዙት ‹ላሽ በሉ!› ነው ማለት ያለብን…›› ሲለኝ ጆሮዬ ቆሞ ነው ያዳመጥኩት፡፡ እንዲህ ነው እንጂ! መልካም ሰንበት!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት