አርሶ አደሩ የዕለት ጉርሱን የሚያገኝበትን ማሳ መና አስቀርቷል፡፡ ለሚበሉት የተቸገሩም አሉ፡፡ ያለ አባ ወራ ልጆቻቸውን በግብርና የሚያስተዳድሩ እንስቶችንም ተስፋ አስቆርጧል፡፡ ቀንና ማታ ማሳቸው እንዳይበላባቸው ላይ ታች ያሉ ብዙዎች ቢሆኑም፣ መንጋው ከባድ በመሆኑ ልፋታቸው ሳይሳካ የቀሩ አርሶ አደሮች ትንሽ የሚባሉ አይደሉም፡፡
የበረሃ አንበጣ በኢትዮጵያ የተከሰተው ከሰኔ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ቢሆንም፣ ችግሩ ጎልቶ የታየው በመስከረም 2013 ዓ.ም. ነው፡፡ መነሻውን ከየመንና ከሶማሌላንድ ያደረገው የበረሃ አንበጣ በመስከረም 2013 ዓ.ም. በድጋሚ ተፈልፍሎ ሲመጣ ገና ያልደረሱና የደረሱትም የገበሬ ማሳዎች ሙሉ ለሙሉና በከፊል አውድሟል፡፡
የመስከረሙን መንጋ አስከፊ የሚያደርገው እህሉን ሙሉ ለሙሉ ከበላ በኋላ ለከብቶች መኖ ሊሆን የሚችለውን ቀሪ ክፍል ቅርጥፍ አድርጎ የሚመገብ በመሆኑ ነው፡፡ ዛፎች፣ የግጦሽ መሬት በአጠቃላይ አረንጓዴ ነገሮች ሳይቀር ለመንጋው የዕለት ጉርሱ ነበር፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች ላይም ጎረቤት ለጎረቤት ተበዳድሮ የዕለት ጉርሱን እንዳይሸፍን የሁሉም አርሶ አደሮች ማሳ ባዶ በማስቀረቱ የብዙዎችን ችግር አጉልቷል፡፡
አንዳንዶች በኢትዮጵያ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ሲገልጹት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የኢትዮጵያን የጤና ዘርፍ እንደተፈታተነው የአንበጣ መንጋውም የግብርና ዘርፉን ተገዳድሮታል ይላሉ፡፡
የበረሃ አንበጣ ከተከሰተባቸው ክልሎች መካከል በአማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ አፋርና እንዲሁም ሌሎችም አካባቢዎች ብዙ ውድመት ማድረሱ አይዘነጋም፡፡
እስከ ግማሽ ሚሊዮን ሔክታር አውድሟል የተባለውን የበረሃ አንበጣ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከግብርና ሚኒስቴር ጀምሮ እስከ ወረዳና አርሶ አደሩ ድረስ መረባረባቸውም አልቀረም፡፡ ነገር ግን በወቅቱ በቂ የርጭት ሔሊኮፍተሮች አለመኖራቸው ችግሩን አጉልቶታል፡፡ ይህንን ችግር ለመመከት እስራኤል 27 ድሮኖች መስጠቷ ይታወሳል፡፡ ለወረርሽኑ መስፋፋት አመቺ ሁኔታ የፈጠረው የርጭት ሔሊኮፍተሮች መበላሸትና መከላከል የነበረ ሲሆን፣ ይህም ከውጭ አገሮች ጋር በመተባርና 12 ሔሊኮፍተሮችን ወደ ርጭት በማስገባት ችግሩን ለማቃለል ተሠርቷል፡፡
ይህም ሆኖ ቀድሞ በቂ የሄሊኮፍተር ርጭት ባለመደረጉ በተለይ በትግራይና አማራ ክልሎች ከሁሉም ክልሎች የበለጠ ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸው ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ሥጋት ሆኖ የቆየው የዚህ በመንጋ እንቅስቃሴ ጋብ ብሎ የነበረ ቢሆንም፣ አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ማንዣበቡን ቀጥሏል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ከአሥር ቀን በፊት በሐመር ወረዳና አካባቢዎች ላይ የበረሃ አንበጣ መከሰቱን የወረዳው የግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡
በዚሁ ወረዳ በጥር ወር 2012 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ከተከሰተ በኋላ፣ በቀጣይ በሦስትና አራት ወራት ውስጥ መንጋው የሚጥለው እንቁላል ዳግም ሥጋት እንዳይሆን ከፍተኛ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን የሐመር ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ የሺዋስ ዓባይ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ዘንድሮ ከሶማሊያ ተነስቶ ኬንያ ከዚያም በኢትዮጵያ ቦረና አድርጎ ታኅሳስ 2 ቀን 2013 ዓ.ም. በሐመር ወረዳ እንደገባ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በወረዳው ከተከሰተ በኋላ የመከላከል ሥራ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ በተሠራው ሥራ 2,600 ሔክታር ላይ ያረፈውን የአንበጣ መንጋን መቆጣጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ታኅሳስ 12 እና 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ባለው መረጃ መሠረት በወረዳው የገባ አዲስ መንጋ ባይኖርም፣ ወረዳው ካሉት 35 የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ 14 ቀበሌዎች ላይ መንጋው አርፏል፡፡
ያልተሰበሰበ ሰብል፣ የእንስሳት መኖ፣ ግጦሽና ዛፎች ላይ ውድመት ማድረሱን የጠቆሙት አቶ የሺዋስ፣ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ ለማወቅ በባለሙያዎች ተጠንቶ በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በ14 ቀበሌዎች ውስጥ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ጉልህ ጉዳት ሳያደርስ አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች ተባብረው የተቆጣጠሩ ሲሆን፣ በተወሰነ እህል ላይ ደግሞ ጉዳት ማድረሳቸውን አክለዋል፡፡
እስካሁን የበረሃ አንበጣ ያረፈበት በገጠር ቀበሌዎች ላይ ሲሆን፣ በሦስቱ የከተማ ቀበሌዎች ላይ እንዳላረፈ አቶ የሺዋስ ተናግረዋል፡፡
2012 ዓ.ም. ላይ በወረዳው ተከስቶ የነበረው የበረሃ አንበጣ ደግሞ የተከሰተበት ምክንያት ከጎረቤት አገሮች የሚገባው አዲስ መንጋ ላይ ቁጥጥር ማድረግ ባለመቻሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የተከሰተው የበረሃ አንበጣ እንቁላል ጥሎ አደገኛ የሆነ መንጋ እንዳይፈጠር ለማድረግ የገባውን መንጋ ለማጥፋት ከኅብረተሰቡ ጀምሮ እስከ መንግሥት አካል ርብርብ እያደረጉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡
የበረሃ አንበጣ መንጋው ከባለፈው ጋር ሲነፃፀር የተጋነነ ባይሆንም፣ በተቆራረጠ መንገድ ስለሚመጣ ያለ ማቋረጥ የኬሚካል ርጭት በማድረግ መከላከል ላይ እንደሚገኙ ኃላፊው ያስረዳሉ፡፡
አሁን ባለው መረጃ መነሻውን ሶማሊያ አድርጎ በኢትዮጵያ ቦረና እንደሚመጣ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፣ አሁንም ከፍተኛ ሥጋት እንደሆነ አቶ የሺዋስ ይናገራሉ፡፡
በዚህ መነሻነት የአሰሳና የቅኝት ሥራ እየተሠራ ሲሆን፣ የደረሰውን ጉዳት በባለሙያዎች ተጠንቶ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡
ሌላው በቅርቡ የበረሃ አንበጣ ከተከሰተባቸው ክልሎች ውስጥ አፋር ይገኝበታል፡፡ በክልሉ ባለፉት አሥር ቀናት ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የበረሃ አንበጣ መከሰቱ ተጠቁሟል፡፡ አጠቃላይ ያለውን መረጃ ለማሳወቅ በባለሙያዎች እየተጠና መሆኑ ተገልጿል፡፡
በክልሉ አሁንም ከሌላ አገሮች የሚገቡ አዲስ የበረሃ አንበጣ መኖሩ የተገለጸ ሲሆን፣ ካሉት አምስት ዞኖች ውስጥ አንዱ ላይ መኖሩ ታውቋል፡፡
በአፋር ካሉ አምስት ዞኖች ውስጥ ዞን ሁለት የሚባለው ላይ መንጋው ማንዣበቡን የአፋር ክልል የእንስሳትና እርሻ ተፈጥሮ ሀብት ዳይሬክተር ተወካይ መሐመድ ኑር (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የአንበጣ ሥጋት ካለባቸው ቦታዎች መረጃ ለማሰባሰብ የተሰማሩ ባለሙያዎች አጠናቅረው ሲጨርሱ መረጃውን ለኅብረተሰቡ ይፋ እንደሚያደርጉም አክለዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በዘር የተሸፈነው 13.4 ሚሊዮን ሔክታር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ይሰበሰባል ተብሎ የታቀደው ከ379 ሚሊዮን እስከ 460 ሚሊዮን ኩንታል እህል ነው፡፡
እስካሁን ወደ 75 በመቶ የሚሆነው ሰብል የተሰበሰበ ሲሆን፣ በቁጥር ሲገለጽ ወደ 10 ሚሊዮን ሔክታር እንደሚሆን ሚኒስትር ዴኤታው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በዚህ ወር መጨረሻ አካባቢ የሰብል መሰብሰቡ ሥራ እንደሚያልቅና የመኸሩ ሥራም ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅና ዓምና ከነበረው በ12 በመቶ ያድጋል የሚል ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል፡፡
የበረሃ አንበጣ ተፅዕኖ በአገር ደረጃ አነስተኛ ሲሆን፣ በግለሰብ ሲታይ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህም ሙሉ በሙሉ የወደመባቸው አርሶ አደሮች በአደጋ ሥጋትና መከላከል በኩል የዕለት ተደራሽ ምግብ እንዲያገኙ የሚደረግላቸው ናቸው ብለዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር በኩል ደግሞ በሴፍቲኔት እንዲታቀፍ ይደረጋል፡፡ አንድ የሴፍቲኔት የሚደገፍ ቤተሰብ ባላቸው የቤተሰብ ቁጥር ልክ ድጋፍ እንዲያገኙ ይደረጋል ያሉት ዶ/ር ማንደፍሮ፣ በተጨማሪም ውኃ ገብ መሬት ያላቸውን አርሶ አደሮች የዘር፣ ማዳበሪያና ሌሎች ግብዓቶችንም በመደገፍ ራሳቸውን እንዲችሉ ድጋፍ ይሰጣቸዋል፡፡
በአመዛኙ አንበጣ የነበረባቸው ክልሎችና ዞኖች በክልላቸው ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ ለአንበጣ መከላከልና ማጥፊያ የሚውሉ 16 አውሮፕላኖች እንደሚገኙ የገለጹት ዶ/ር ማንደፍሮ፣ ሦስቱ ቅኝት የሚሠሩና ኬሚካል የሚረጩ ናቸው፡፡
አሁን ላይ በድሬዳዋ ኮምቦልቻና አርባ ምንጭ የሚገኙ ሦስት ጣቢያዎች ለበረሃ አንበጣ መከላከል እየዋሉ ነው፡፡ ጣቢያዎቹ በተሽከርካሪ፣ በሰው ኃይልና በአውሮፕላን አስፈላጊው ግብዓት በማሟላት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በየቀበሌው በበረሃ አንበጣ መከላከል ላይ የሠለጠኑ ስካውቶችን በማሰማራት መረጃዎችን እንዲሰበስቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ለዚህም ሥራ የሚውሉ ወደ 25 ሺሕ ታብሌት ለአንድ ቀበሌ ሁለት ለመስጠትና እዚሁ ሆነው ያለውን መረጃ ለመቀባበልና ሥራውን ምቹ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ ሚኒስትር ዴኤታው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ለአንበጣ መከላከል አምስት አውሮፕላኖች ለመግዛት ትዕዛዝ የተሰጠ ሲሆን፣ አሁንም በሶማሌ ክልል ውስጥ የበረሃ አንበጣ መኖሩን በመግለጽ ያሉትን አውሮፕላኖች በባሌ በኩልና በአርባ ምንጭ በኩል የሚገባውን መንጋ በመከላከል ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡