Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናቦርዱ በመጪው ምርጫ የዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ እንዲቀር ፓርላማውን ጠየቀ

ቦርዱ በመጪው ምርጫ የዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ እንዲቀር ፓርላማውን ጠየቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲከናወን ቀን ለተቆረጠለት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ፣ ዕጩዎች ማቅረብ ይጠበቅባቸው የነበረው የድጋፍ ፊርማ እንዲቀርና አገልግሎት ላይ እንዳይውል እንዲደረግ ፓርላማውን ጠየቀ፡፡

በምርጫ ለመወዳደር የሚፈልግ የግልም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲን፣ ግንባርን ወይም ቅንጅትን ወክለው በዕጩነት የሚቀርቡ ተወዳዳሪዎች፣ ከ5,000 እስከ 750 የሚደርሱ የድጋፍ ፊርማዎችን ማቅረብ ይጠበቅባቸው ነበረ፡፡ ይሁንና በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የወረቀት ንክኪን በተቻለ መጠን ለመቀነስና የሚመጡ የድጋፍ ፊርማዎችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ካለው የጊዜ መጣበብ ጋር በተገናኘ አዳጋች ስለሚሆን፣ ፓርላማው ከግንዛቤ አስገብቶ በአዋጁ ላይ ይኼንን ጉዳይ ማሻሻያ እንዲያደርግበት ጥያቄ መቅረቡን፣ የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ታኅሳስ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ገልጸዋል፡፡

በምርጫ አዋጁ መሠረት አንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፖለቲካ ፓርቲን፣ ድርጅትን፣ የድርጅቶች ግንባርን ወይም ቅንጅትን ወክሎ የሚቀርብ ዕጩ 2,000 የድጋፍ ፊርማዎችን ማሰባሰብ የሚጠበቅበት ሲሆን፣ የግል ተወዳዳሪ 5,000 ፊርማዎች፣ አካል ጉዳተኛ የሆነ የግል ዕጩ ደግሞ 3,000 ፊርማዎችን፣ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲን ወክሎ የሚቀርብ አካል ጉዳተኛ ከሆነ 1,500 ፊርማዎችን ማሰባሰብ ይጠበቅባታል፡፡ ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደር ዕጩ ደግሞ ድርጅትን፣ ፓርቲን፣ ግንባርን ወይም ቅንጅትን የሚወክል ከሆነ 1,000 ፊርማዎችን፣ የግል ዕጩ 2,500 ፊርማዎችን፣ አካል ጉዳተኛ ከሆነ 1,500 ፊርማዎችን፣ እንዲሁም አካል ጉዳተኛ የሆነ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካይ ዕጩ 750 ፊርማዎችን ማሰባሰብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ይሁንና ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በሚደረገው ምርጫ ይኼ መሥፈርት ተግባራዊ እንዳይደረግ ለማድረግ እየተሞከረ ነው፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ ይኼንን ጥያቄ ለፓርላማው ማቅረባቸውን ሲናገሩ፣ በራዲሰን ብሉ ሆቴል የተጠራው ስብሰባ ላይ የተገኙ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ደስታቸውን በጭብጨባ ገልጸዋል፡፡

ከስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ጋር አብሮ የሚካሄደው የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልል ሕዝበ ውሳኔ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ በጋራ ክልል ሊመሠርቱ ያቀረቡትን ዞኖች ጥያቄ ተቀብሎ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የሚከናወን ይሆናል፡፡

ካሁን ቀደም ይፋ ተደርጎ የነበረው የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ምርጫው ሲሰረዝ አብሮ መሰረዙ የሚታወስ ሲሆን፣ እሱን ተክቶ አሁን ይፋ የተደረገው አዲሱ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ፣ የምርጫ ጽሕፈት ቤቶችን በሁሉም የምርጫ ክልሎች ለመክፈት አንድ ወር፣ ለምርጫ አስፈጻሚዎች ሥልጠና ለመስጠትና ለመራጮች ምዝገባ 27 ቀናት፣ ለመራጮች ትምህርትና ለዕጩዎች ምዝገባ 34 ቀናት፣ እንዲሁም ለፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ምልክት ማስመዝገቢያና መወሰኛ ሁለት ሳምንታት ይመድባል፡፡

የዕጩዎች ምዝገባ በሁለት ሳምንታት፣ የምረጡኝ ቅስቀሳና የምርጫ ዘመቻ በሦስት ወራት፣ ለመራጮች ምዝገባ ትምህርት መስጠት በሁለት ወራት ከአንድ ሳምንት የሚጠናቀቁ እንደሚሆኑ አዲሱ ሰሌዳ ያስረዳል፡፡

የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ መስተዳድሮች ምክር ቤቶች ምርጫ ድምፅ መስጫ ቀን፣ ሰኔ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደሚከናወን የሚያሳየው አዲሱ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ፣ ይኼ የሆነበት ምክንያት የከተማ መስተዳድሮቹ የምርጫ ክልሎችና የምርጫ ጣቢያዎች የሚወሰኑት፣ በከተሞቹ ምክር ቤቶች ስለሆነ ነው ተብሏል፡፡ እነዚህም የምርጫ ክልሎችና ጣቢያዎች ከጠቅላላ አገራዊ የምርጫ ክልሎችና ጣቢያዎች ጋር የተለያዩ ሊሆኑ ስለሚችሉ፣ የሚፈጥረውን ግርታና የቴክኒክ ውስብስብነት ለመቀነስ ሲባል ለብቻ እንዲደረጉ መወሰኑም ተገልጿል፡፡

ይሁንና ምርጫ ቦርድ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ባለመከናወኑና የምርጫ ክልሎች አወሳሰን ላይ በፓርላማው የተደረገ ለውጥ ስለሌለ፣ ቀደም ሲል የነበሩ የምርጫ ክልሎች እንደሚጠቀም ያስታወቀ ቢሆንም፣ በአዲስ አበባ አዲስ ክፍለ ከተማ መፈጠሩንና በክልሎችም አዳዲስ አስተዳደራዊ ወሰኖች መጨመራቸውን በማንሳት፣ ለምን ይኼ ሆነ የሚል ጥያቄ ያቀረቡ ነበሩ፡፡ ሆኖም አዳዲስ የአስተዳደር ወሰኖች በምርጫ ጣቢያዎቹ ላይ የሚፈጥሩት ለውጥ ስለሌለ፣ ቀድሞ በነበረው የምርጫ ጣቢያዎች ካርታ እንደሚሠራ ቦርዱ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን...