Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየቀድሞውን የጉማይዴ ወረዳ ለማስመለስ በተነሳው አለመግባባት የሰብዓዊ መብት ጥሰት መድረሱ ተገለጸ

የቀድሞውን የጉማይዴ ወረዳ ለማስመለስ በተነሳው አለመግባባት የሰብዓዊ መብት ጥሰት መድረሱ ተገለጸ

ቀን:

በደቡብ ክልል የቀድሞውን የጉማይዴ ወረዳ ለማስመለስ በተደረገ እንቅስቃሴ ምክንያት በተነሳው አለመግባባት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየደረሱ መሆኑን፣ 145 ሺሕ ወክለው ወደ አዲስ አበባ የመጡት የጉማይዴ ሕዝብ የሰላም ኮሚቴ አባላት አስታወቁ፡፡

በአካባቢው በተነሳው ግጭት ሳቢያ ዘግናኝ የሆኑ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በሚመለከት ለሕዝብ ለማሳወቅና ተገቢ ፍትሕ ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ የመጡት የጉማይዴ ሕዝብ የተወከሉት ኮሚቴዎች፣ ታኅሳስ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሆቴል ለመገኛኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

የግጭቱ መነሻ የሆነው ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በሰገን ከተማ ተቋቁሞ የነበረው፣ ‹‹የሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን››፣ ሕዝቡ ሳያውቅ በመፍረሱ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የዞኑ መመሥረት በዋነኛነት የተፈለገው፣ የአሁኑ ኮንሶ ዞን፣ ደራሼ፣ አማሮ፣ ቡርጂና አሌ ልዩ ወረዳ ጋር የሚያዋስን በመሆኑ ‹‹የሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን›› እንዲሆን በሕዝብ ፍላጎት እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ተወካዮቹ እንደተናገሩት፣ በሕዝብ ውሳኔ ‹‹የሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን››፣ ያለ ሕዝብ ፍላጎት ወደ ኮንሶ ዞን በመዘዋወሩ ምክንያት ሕዝቡ ቅሬታ ሲያሰማ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ ውሳኔውን በመቃወም በሰላማዊ መንገድ ለሚመለከተው አካል ድምፃቸውን ማሰማታቸውን ያስረዱት ተወካዮቹ፣ ሕዝቡ ጥያቄውን በማንሳቱ ምክንያት ከፍተኛ የደኅንነት ሥጋት ላይ ከመውደቁ በተጨማሪ የሰብዓዊ መብት ጥሰትት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ የደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአካባቢው ከ40,000 በላይ ነዋሪዎች መፈናቀል፣ ከ80 በላይ ንፁኃን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደል፣ ከ300 በላይ ሰላማዊ አርሶ አደሮችና ነዋሪዎች ያለፍትሕ መታሰር፣ ሴቶችና ሕፃናት በጋራና በተናጠል መደፈራቸውን ኮሚቴው አስታውቋል፡፡

ይሁንና የደረሰውን በደል ለወረዳ፣ ለዞንና ክልል ድረስ በተደጋጋሚ ቅሬታ ቢያሰሙም ምላሽ መነፈጋቸውን ተናግረዋል፡፡ የሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን በ2003 ዓ.ም. በፌዴራልና በክልል በተወጣጡ ቡድኖች ዞኑ ምቹ መሆኑ ተጠንቶ የቀረበና ለአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሴቶችና ወጣቶች ተወካዮች በተገኙበት በሐዋሳ ከተማ ማፅደቁን አስታውሰዋል፡፡

በሕዝብ ውሳኔ የፀደቀው ዞን እንዲፈርስ ተደርጎ ለኮንሶ ብቻ ‹‹ዞን›› ተሰጥቶ የሌሎቹ ዕጣ ሳይወሰን መቅረቱ በሕዝቡ ቅሬታ መፈጠሩን ያስረዳሉ፡፡ በዚህም የጉማይዴ የልዩ ወረዳ መዋቅር አደረጃጀት በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዲፈቀድላቸው መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡ የጉማይዴ 17 ቀበሌዎች ማዕከል ‹‹የሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን›› መቀመጫ የነበረችው ሰገን ከተማ መሆኗን ገልጸዋል፡፡

‹‹ፍትሕ፣ መልካም አስተዳደርና ልማት በቅርበት ሰገን ከተማ ላይ ማግኘት እየተቻለ፣ አራት ወረዳዎችን አቋርጠን አንሄድም›› በማለት በጠየቁት ጥያቄ ምክንያት ሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ንብረት ዘረፋና የሕይወት እስከ ማጣት መስዋዕትነት እየከፈሉ መሆኑን ተወካዮቹ ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል ለኮንሶ በመወገን ድብደባ፣ እስር ሲፈጽምባቸው መቆየቱን የሚገልጹት ተወካዮቹ፣ ከኮንሶ ታጣቂዎች ጋር በመተባበር እንግልት ላይ እንደሚገኙ ያስረዳሉ፡፡

በተፈጠረው ምክንያት ኮንሶዎች ከታሰሩ ያለምንም ማጣራት የሚፈቱ ሲሆን፣ በተቃራኒው ያሉት ደግሞ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየደረሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየደረሰባቸው መሆኑን ስለገለጹት ነዋሪዎች የኮንሶ ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሠራዊት ዲባባን ሪፖርተር አነጋግሯቸው እንደገለጹት፣ የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎቻቸውን ይዘው መሄድ የሚችሉት ወደ ሰገን ዙሪያ አስተዳደር መሆን እንደነበረበት ያስረዳሉ፡፡

ጉማይዴ የሚባለው ቦታ ላይ የሰገን ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር ተቋቁሞ እንደሚገኝ የሚገልጹት አቶ ሠራዊት፣ ሕዝቡ ከወረዳው ጋር ተናቦ ጥያቄውን ማቅረብ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ የሰገን ዙሪያ አስተዳዳር ምላሽ መስጠት ካቃተው ወደ የኮንሶ ዞን አስተዳደር፣ በዚያም ካልተስተናገዱ ወደ ክልል የደረሰባቸውን በደል ማሰማት ይችሉ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ሰገን ዙሪያ አስተዳደር ጥያቄ አቅርበው እንደማያውቁና በከተማው ላይ እንደማይኖሩ አቶ ሠራዊት ተናግረዋል፡፡ አቶ ሠራዊት እንደተናገሩት፣ ‹‹የጉማይዴ ሕዝብ የሰላም ኮሚቴ ነኝ የሚለው ሕዝቡን አስተባብሮ ጦርነትና ትርምስ እንዲፈጠር እያደረገ ያለ ኃይል ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አሁን አዲስ አበባ መጥተው ቅሬታ ያቀረቡ ሰዎችን በዝርዝር ወይም በፎቶ›› ሚዲያው የማጋለጥ ሥራ እንዲሠራ ኃላፊውን ትብብር ጠይቀዋል፡፡

ጥያቄ አለን የሚል አካል የኮንሶን ዞንና የአስተዳደሩን የድጋፍ ደብዳቤ ሊይዝ እንደሚገባ፣ ለኮንሶ ዞንና ለክልል ሊያመለክቱ እንደሚገባ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ ማንኛውም ከሰገን ዙሪያ ወረዳ ተወልዶ፣ ተጎዳን የሚል ኃይል በኮንሶ ዞን ጥያቄም እሮሮም ያቀረበ ምንም ዓይነት ግለሰብም ሕዝብም አልመኖሩን ገልጸዋል፡፡

ከጥቅምት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ኮንሶ ዞን አካባቢ የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት፣ አካባቢውን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ፣ ከኅዳር 1 አስከ 11 ቀን 2013 ግጭቱ መነሳቱ ይታወሳል፡፡ በአሌ፣ በኮንሶ ሰገን ዙሪያ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች አማሮ ወረዳ ቡኒቲ ቀበሌ፣ እንዲሁም ከኅዳር 6 እስከ 8 ቀን 2013 ዓ.ም. በደራሼ ወረዳ ጋቶ ቀበሌ ተከታታይ ግጭቶች ዳግም መከሰታቸውን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

በዚህም የደቡብ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በሰገን አካባቢ በተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስና ግጭት 66 ሰዎች መገደላቸውን፣ 39 ሰዎች መቁሰላቸውንና 132,143 ሰዎች መፈናቀላቸው ኮሚሽኑ ባወጣው የምርመራ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡

ታኅሳስ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚገኘው ኢትዮጵያ ሆቴል ከ145,000 በላይ ሕዝብ የተወከለው የጉማይዴ ሕዝብ የሰላም ኮሚቴ፣ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ 40 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም ከ80 በላይ ንፁኃን መሞታቸውንና ከ300 በላይ ሰላማዊ ሰዎች ያለፍትሕ መታሰራቸውን ተናግረዋል፡፡ የኮንሶ ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ኅዳር ወር ላይ ለሪፖርተር እንደተናገሩት በግጭቱ 102 ሰዎች መሞታቸውን 83,131 ዜጎች መፈናቀላቸውን መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...