Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኒያላ ኢንሹራንስ ካፒታሉን ወደ 600 ሚሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኒያላ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር የተከፈለ ካፒታል መጠኑን ወደ 600 ሚሊዮን ብር ለማሳደግ መወሰኑን ገለጸ፡፡ በ2012 የሒሳብ ዓመትም ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ዓረቦን መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡

ኩባንያው ሰሞኑን ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ የካፒታል መጠኑን ወደ 600 ሚሊዮን ብር ማሳደጉ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከፍተኛ የተከፈለ ካፒታል መጠን እንዲይዝ እንደሚያደርገው አክሏል፡፡ የነበረው የተከፈለ ካፒታል መጠን 531 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ከኩባንያው የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

የተመሠረተበትን 25ኛ ዓመት በማክበር ላይ የሚገኘው ኒያላ ኢንሹራንስ አ.ማ. በ2012 ሰሳየሐሒየሐሒ የሐሒየሒሳብ ዓመት 565.3 ሚሊዮን ብር ዓረቦን መሰብሰብ ችሏል፡፡

የሥራ አፈጻጸሙን በተመለከተ የኩባንያው ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ቢርቦ፣ ‹‹ባሳለፍነው በጀት ዓመት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰቱ አንዳንድ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ተግዳሮቶች ምክንያት የንግድ መቀዛቀዝና መስተጓጎል ቢኖርም ኒያላ ኢንሹራንስ የ15 በመቶ ዕድገት የተመዘገበበት የዓረቦን ገቢ መሰብሰብ ችሏል፤›› ብለዋል፡፡

የዓረቦን ገቢው ዓምና ከነበረው ገቢ ከፍ ብሎ እንዲመዘገብ ምክንያት የሆነው ኩባንያው አዳዲስ የአሠራር ስትራቴጂዎችን በመንደፍ በተከተለው አሠራር፣ በተለይም ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሙሉ ዋስትና መስጠት መቻሉ፣ በዚህም ምክንያት የበርካታ ደንበኞችን ሥጋት በማቃለሉ፣ አለኝታ መሆኑን በተግባር በማስመስከሩና በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ የአገር ደንበኞችን በመሳቡ እንደሆነም አክለዋል፡፡

የኩባንያው ዓመታዊ ትርፍ ከቀዳሚ ዓመት ያነሰ ቢሆንም፣ 149.1 ሚሊዮን ብር ትርፍ ያስመዘገበ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፣ ከነበረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከፍተኛ ጫና፣ የዋጋ ንረት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች አንፃር የተገኘው ትርፍ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡

በተጠቀሰው በጀት ዓመት የኩባንያው ጠቅላላ ሀብት 2.2 ቢሊዮን ብር ሆኖ መመዝገቡን የሚያመለክተው የኩባንያው መረጃ፣ ይህም ከ2011 የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ7.7 በመቶ ብልጫ እንዳለው የቦርዱ ሊቀመንበሩ አስረድተዋል፡፡

ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ 175.3 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ለደንበኞቹ የፈጸመ ሲሆን፣ ይህም በ2011 ዓ.ም. ከተከፈለው ጋር ሲነፃፀር የ8.2 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አቶ ጌታቸው በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡

የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያሬድ ሞላ በበኩላቸው፣ የኒያላ ኢንሹራንስ አ.ማ. የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ተደራሽነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆን እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

 በተለይም ፊት ለፊት በመገኘት ከሚደረገው የመድን ዋስትና ግብይት በሻገር፣ ለዲጂታል ትውልድ የሚሆን በኢንሹር ቴክ የታገዘ አማራጭ አገልግሎት ለማቅረብ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ኩባንያው የደንበኞቹን ፍላጎት መሠረት በማድረግና ሰፋ ያለ ጥናት በማካሄድ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ያሬድ፣ በተለይ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ከኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ በቀዳሚነት የሕይወትና የጤና ዋስትና ሽፋን መጀመሩንና በዚህ ፈታኝ ወቅት ከደንበኞች ጎን መቆሙን ገልጸዋል፡፡

ኒያላ ኢንሹራንስ አ.ማ. በ1987 ዓ.ም በሰባት ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመና በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ጎዳና ባለ 18 ወለል ዋና መሥሪያ ቤት ገንብቶ በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች