Saturday, June 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዳሸን ባንክ ከፍተኛ ትርፍ በማትረፉ የሒሳብ ዓመቱን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቁን ገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተከፈለ ካፒታሉ ወደ 5.5 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ወሰነ

ዳሸን ባንክ ከኢትዮጵያ የግል ባንኮች ሁለተኛውን ከፍተኛ ትርፍ በማትረፍ የ2012 የሒሳብ ዓመትን በተሳካ ሁኔታ ማጠቃለሉን አስታወቀ፡፡ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 5.5 ቢሊዮን ብር እንዲሆን መወሰኑንም አክሏል፡፡

የዳሸን ባንክ ባለአክሲዮኖች ታኅሳስ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ንዋይ በየነ እንደገለጹት፣ በ2012 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ያስመዘገበው የ1.8 ቢሊዮን ብር ትርፍ ከ2011 አንፃር ሲታይ የ40 በመቶ ዕድገት ያለው ነው፡፡ ይህም በኢንዱስትሪው ውስጥ ከፍተኛ የትርፍ ዕድገት ካሳዩ ሁለት ቀዳሚ ባንኮች አንዱ የሚያደርገው መሆኑ ታውቋል፡፡

በተለይ በባንኮች ኢንዱስትሪ ውስጥ ከሌሎች የተለየ ያስባለው፣ የትርፍ ክፍፍል መጠኑ ከ2011 የሒሳብ ዓመት ተገኝቶ ከነበረው የበለጠ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በሒሳብ ዓመቱ የግል ባንኮች ካስመዘገቡት ከፍተኛ የሚባል መሆኑ ነው፡፡ በባንኩ መረጃ መሠረት፣ በ2012 የሒሳብ ዓመት የባንኩ አንድ አክሲዮን ያስገኘው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት በ20 በመቶ ዕድገት በማሳየት 490 ብር ደርሷል፡፡ በ2011 የሒሳብ ዓመት አንዱ የዳሸን ባንክ አክሲዮን ያስገኘው ትርፍ 408 ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከትርፍ ዕድገቱ ባሻገር በሥራ አፈጻጸሙ ውጤታማ መሆኑን ያስታወቀው ዳሸን ባንክ፣ በ2012 የሒሳብ ዓመት 8.8 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን 53.3 ቢሊዮን ብር አድርሷል፡፡ ይህ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ዕድገት 20 በመቶ የጨመረ መሆኑን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

ከዚህ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ 95.6 በመቶ ወይም 51.1 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ከመደበኛው የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበ ገንዘብ ሲሆን፣ 4.4 በመቶ ወይም 2.4 ቢሊዮን ብር የሚሆነው የተቀማጭ ገንዘብ የተሰበሰበው ደግሞ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መሆኑን የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ አመልክተዋል፡፡ ባንኩ አምና ብቻ ከ148 ሺሕ በላይ አዳዲስ ከወለድ ነፃ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ሒሳብ መክፈቱም ተጠቅሷል፡፡  

ባንኩ ውጤታማ ሆኜበታለሁ ብሎ ያመለከተው ሌላው ክንውን፣ በሒሳብ ዓመቱ ለተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች ያሠራጨው የብድር መጠን የ13.3 በመቶ ዕድገት በማሳየት 17.4 ቢሊዮን ብር ለብድር ያዋለ መሆኑን ነው፡፡ ይህም አጠቃላይ የባንኩን የተከማቸ ብድር መጠን 42.6 ቢሊዮን ብር አድርሶታል፡፡    

ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ የተለያዩ ማኅበራዊ ኃላፊነቶችን ለመወጣት ከ92.4 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በ2012 የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ ገቢ መጠኑን በ40 በመቶ ያሳደገ ሲሆን፣የ7.288 ቢሊዮን ብር ገቢም አግኝቷል፡፡ ዓመታዊ ወጪው ደግሞ 5.5 ቢሊዮን ብር መድረሱ ታውቋል፡፡

ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት 562.8 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ ይህ ገቢ ከ2011 የሒሳብ ዓመት ገቢ በአምስት በመቶ ጭማሪ ያሳየ ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አዳዲስ ደንበኞችም የዳሸን ባንክ ኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን አካውንት ከፍተዋል፡፡ የባንኩ የካርድ ተጠቃሚዎች ቁጥርም ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ደርሷል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ25.5 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡

ዳሸን ባንክ በኢንዱስትሪው ውስጥ ቀዳሚ ከሚባሉ ባንኮች ሊያስቀምጡት ከቻሉት ውስጥ የሀብት መጠኑን በ21 በመቶ በማሳደግ 86.2 ቢሊዮን ብር ማድረሱ ይገኝበታል፡፡ ይህ የሀብት መጠን በ2011 የሒሳብ ዓመት 56.2 ቢሊዮን ብር እንደነበር የባንኩ ሪፖርት ያሳያል፡፡

ዳሸን ባንክ ባለፈው ዓመት በመላ ኢትዮጵያ ያሉትን የቅርንጫፎቹን ቁጥር ወደ 423 አሳድጓል፡፡ ባንኩ ታህሳስ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ፣ የባንኩን ካፒታል በ2012 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ ከነበረው 3.47 ቢሊዮን የተከፈለ ካፒታል፣ ወደ 5.5 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች