Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ብሔራዊ ባንክ የት ነው ያለኸው?

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ውጤታማ ናቸው የሚለው መረጃ በተለያየ መንገድ ይገለጻል፡፡ በተለይ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚያደርገው ቁጥጥር ትርጉም ያለው ለውጥ እንዳመጣም ይታመናል፡፡

ዛሬ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ሥራ ላይ የሚገኙት የብሔራዊ ባንክ የመቆጣጠሪያ ሥልቶች ባይኖሩ፣ የምናያቸው የፋይናንስ ተቋማት አሁን ለደረሱበት ደረጃ ላይበቁ ይችሉ እንደነበር ብዙዎች የሚስማሙት እውነት ነው፡፡ የእነዚህ ፋይናንስ ተቋማት ጤናማነት ሲገለጽ በዋናነት የሚቀመጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ነው፡፡

ኢንዱስትሪውን የሚጎረብጡ መመርዎች የመኖራቸውን ያህል የባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መስመር እንዳይስቱ፣ ለአገር ውድቀት ሰበብ እንዳይሆኑ ሲተገበር የቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የመቆጣጠሪያ ሥልት ለኢንዱስትሪው ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ሊባልም ይችላል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አሳሪ የሚባሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕጎች ተሻሽለዋል፡፡ በተለያየ ደረጃ ማሻሻያ የተደረገባቸው መመርያዎችና ሕጎች ከ70 በላይ ደርሰዋል፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት የሥራ መሪዎችና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አመራሮች በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበው ለኢንዱስትሪው ዕድገት በሚበጁ አጀንዳዎች ላይ የመወያየት ዕድል ሁሉ እስከመፍጠር መድረሱ በራሱ እንደ መልካም የሚታይ ዕድል ነው፡፡

በአጭሩ ቁጥጥሩ እንዳለ ሆኖ ይብዛም ይነስም የመደማመጥ ዓውድ ተፈጥሯል፡፡ እኔ የበላይ ነኝ ብሎ እንደ ቀድሞው ጫና ያሳድራል ብሎ ለመግለጽ አይቻልም፡፡ እንዲያውም ብሔራዊ ባንክ እንዲህ ያለ ዕርምጃ ወሰደ እየተባሉ ይነገሩ የነበሩ ዜናዎች ያለመሰማታቸው በራሱ ለውጡን ያሳያል፡፡ ኢንዱስትሪው በተረጋጋ ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ እየተደረገ ነው፡፡

ኢንዱስትሪውን የበለጠ ጤናማ ለማድረግና የተሻለ እንዲሆን ግን አሁንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ግድ ይላል፡፡ ጊዜ የሚወልዳቸውን ችግሮች በመገንዘብ ተስማሚ የሆነ አሠራር መዘርጋት የሚያስፈልግ ይሆናል፡፡ ጡንቻዬን እዩልኝ ለማለት ሳይሆን አግባብ ባለው ሁኔታ ኢንዱስትሪው ውስጥ ሊፈጠር የሚችውን ችግር በመፈተሽ መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ሥራዎችን መሥራት አለበት፡፡

ይህንን ለማለት የወደድኩት ከሰሞኑ አንድ የግል ባንክ በ2012 በጀት ዓመት ያገኘውን ትርፍ ለባለአክሲዮኖች ማከፋፈል እንደማይችል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕገዳ ከመጣሉ ጋር ተያይዞ ችግር መኖሩ ይታያል ብዬ ስላመንኩ ነው፡፡

ባለፉት 25 እና 26 ዓመታት ውስጥ የአንድ ባንክ ትርፍ ክፍፍል ድርሻ እንዲታገድ ከብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ ሲሰጥ የመጀመርያ ባይሆንም፣ አንድ ሁለት ጊዜ በጊዜያዊነትም ቢሆን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተላለፉ ትዕዛዞች ነበሩ፡፡

ከሰሞኑ እንደተሰማው ደቡብ ግሎባል ባንክ የበጀት ዓመቱ የትርፍ ክፍፍል እንዳይፈጸም ብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ የሰጠው ባንኩ በተለያዩ ጊዜያት በተከፈተ ኤልሲ የተፈቀደ የውጭ ምንዛሪ ከኢትዮጵያ ውጭ ሊከፈል ለሚገባው ኩባንያ በወቅቱ ካለመከፈሉ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

በወቅቱ ክፍያው አለመከፈሉ ደግሞ ባንኩን ለተጨማሪ ወጪ ይዳርገዋል፡፡ እዚህ ላይ ግን መታሰብ ያለበት ባንኩ መክፈል የሚገባውን ክፍያ አለመፈጸሙ ባንኩ ላይ የሚፈጥረው ጫና እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ነገሩን ከፍ ካደረግነው ደግሞ እንደ አገር የኢትዮጵ ገጽታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡  

ያለው ችግር ግን የአንዱ የደቡብ ግሎባል ባንክ ብቻ ችግር አለመሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ባንኮች ውስጥ የሚታይ ነው፡፡ ዛሬ የደቡብ ግሎባል ባንክ አፍጥጦ ወጣ እንጂ፣ ችግሩ የሰነበተ ስለመሆኑም እየተሰማ ነው፡፡ ባንኮች የሚገባንን ክፍያ ሊፈጽሙልን አልቻሉም ያሉ የውጭ ኩባንያዎች ለአቤቱታ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ መሰማቱ አዲስ አይደለም፡፡ እንዲያውም ለብሔራዊ ባንክ ሳይቀር አቤት ያሉ እንዳሉም ይገለጻል፡፡ ስለዚህ ችግሩ አለ ማለት ነው፡፡ ችግሩ የሁሉም ነው፡፡ ችግሩ ለአገርም ሥጋት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ጉዳይ ሊያሳስብ እንደሚገባና ብሔራዊ ባንክ ይህን ክፍተት በትኩረት መመልከት እንዳለበት የሚያመለክት ነው፡፡ እስካሁን ለዚህ ጉዳይ ለምን መፍትሔ አላበጀም የሚለው ጥያቄም አንድ ያደርገናል፡፡

አንድ ኤልሲ ተከፍቶለት ግብይቱ ተፈጽሞ ወደ አገር የገባ ምርት ሒሳብ መወራረድ ያለበት በ90 ቀናት ወይም በሦስት ወራት ውስጥ ነው፡፡ አሁን በብዙ ባንኮች እየታየ ነው የሚባለው ግን በሦስት ወራት መክፈል ያለበት ክፍያ ሳይከፈል ዓመታት እያስቆጠረ እየሆነ ነው፡፡ ይህ እየታወቀ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በወቅቱ ዕርምጃ አለመውሰዱ ያመጣው ችግር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ማንኛውም ባንክ በሌለው የውጭ ምንዛሪ የሚከፈተው ኤልሲ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ክፍያ ለሚፈልገው የውጭ ኩባንያ ካልተከፈለ የአገርንም ስም ያስነሳል፣ እየተነሳም ነው፡፡

ክፍያው ሳይፈጸም ከሦስት ወራት በላይ ሲሆን ብሔራዊ ባንክ ምን ይጠብቅ ነበር? የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ባንኮች በወቅቱ ላለመክፈል ከሥር ከሥር ብዙ ኤልሲ እየከፈቱ መዝለቃቸው ዋነኛ ምክንያት ሲፈተሸ አንድ ሁለት ገፊ ምክንያቶች ልብ እንዲባሉ ያስገድዳል፡፡ ይህም ባንኮች ለከፈቱት ኤልሲ በወቅቱ ክፍያ ላለመክፈታቸው አንዱ ምክንያት የባንኮች ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔያቸው ከፍ ለማድረግ ታሳቢ በማድረግ ጭምር የሚሠራ መሆኑ ነው፡፡ አልሲውን በመክፈት የሚገኘውን ኮሚሽን ትርፋቸውን ለማሳደግ ይጠቁሙበታል መባሉ ለጆሮ ደስ አይልም፡፡ ለእነርሱም አደጋ መሆኑን እያወቁ ማድረጋቸው ደግሞ ለምን ያሰኛል፡፡

ብዙ ጊዜ ባንኮች ወደ በጀት ዓመቱ መጨረሻ፣ በሌላቸው የውጭ ምንዛሪ ኤልሲ ከፍተው በኮሚሽን የሚያገኙትን ገቢ እንደ አንድ የትርፍ ማሳደጊያ የሚጠቀሙበት ዋና ምክንያት ደግሞ ወደ ችግሩ ሁለተኛ ገፊ ምክንያት ይወስደናል፡፡ ለምን እንዲህ ይፈርጃሉ ከተባለም በሁሉም ባንች ባለአክሲዮኖች ከፍ ያለ ትርፍ አገኘን ለማለት ነው፡፡

ዛሬ ላይ ደግሞ ባለአክሲዮኖች የኢንዱስትሪውን ፈተና ከግምት ባለማስገባት የትርፍ ክፍፍላቸው ሲያንስ ስላልሠራችሁ ነው፣ ለምንድነው ትርፋችን የሚቀንሰው ብለው የሚሞግቱ በመሆኑ ይህንን ፍራቻ ስህተቶች ሲፈጽሙ እናያለን፡፡

ይህ እጅግ ከፍተኛ አደጋ ነው፡፡ ባለአክሲዮኖች በእርግጥም ትርፍ ይሻሉ፡፡ ሁሌም ግን ትርፍ ላይኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ የባለአክሲዮኖችም ጫና የራሱ ምክንያት አለው ሊባል ይችላል፡፡

ከእነዚህ ገፊ ምንያቶች ባሻገር ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዙ ያሉ ችግሮች ዋነኛ መንስዔ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ ከውጭ የሚገባ መርፌ ሳይቀር ዶላር ይፈልጋል፡፡ ባንኮች እንደ ምንም ካገኙዋት የውጭ ምንዛሪ ላይ ደግሞ ብሔራዊ ባንክ 30 በመቶ የእኔ ድርሻ ነው ብሎ ባወጣው አስገዳጅ መመርያ መሠረት ይቀበላቸዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ችግር በሆነበት አገር 30 በመቶ መውሰድ ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህም የራሱ የሆነ ተፅዕኖ አለው፡፡ ሲጠቃለል ግን የኢትዮጵያ ባንኮች ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዙ አሠራሮቻቸው ተገደውም ሆነ ሆን ብለው እየፈጸሙዋቸው ነው ይባላል፡፡ ይህ እንደ አገር አደጋ እየሆነ ስለመምጣቱ አጥብቆ መናገር ተገቢ ይሆናል፡፡

ምክንያቱም ብዙዎቹ ባንኮች ለውጭ ኩባንያዎች እንዲከፍሉ ግድ የሆነባቸውን ክፍያ ባለመፈጸማቸው፣ ከኢትዮጵያ ባንኮች ጋር መሥራት አንፈልግም እስከ ማለት የደረሱበት ሁኔታ ይሰማል፡፡ ይህ መስተካከል ካልቻለ አደጋው የበረታ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በዓለም የግብይት ሥርዓት ውስጥ የአገር ስም እየተነሳ ነው ማለት ነው፡፡ ውሎ አድሮ የሚፈለግ ምርት ወደ አገር እንዳይገባ እንቅፋት ይሆናልና ችግሩ ገዝፎ የማንወጣው ችግር ውስጥ ከመግባት በፊት ብሔራዊ ባንክ ሁኔታውን መርምሮ መስመር ማስያዝ አለበት፡፡

አሁን ላይ ችግሩ የአንድ ወገን ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ስለመሆኑ እየታየ ነውና ድብብቆሹን በማቆም ተነጋግሮ መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል፡፡

ሌላው ጉዳይ ለውጭ ኩባንያዎች መከፈል ያለበት የውጭ ምንዛሪ በዘገየ ቁጥር የሚባክነው የውጭ ምንዛሪ ብዙም ሳይታሰብበት የቆየ ነው፡፡ በመከራ የሚገኝን ሀብት በአግባቡ ከመጠቀም አኳያ አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪን የሚመለከቱ ሕግጋቶቻችንን ብሎም አሠራሮችን በመፈተሽ ነገሮችን ማስተካከል ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡

ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ አለ የሚባለው ችግር እንደ አገርም ሲታሰብ አደገኛ መሆኑን በማሰብ ብሔራዊ ባንክን በነካ እጅህ ማለት ያስፈልጋል፡፡ አለህ ወይ? ብሎ መጠየቅም ግድ ይላል፡፡      

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት