የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች በአገር ግንባታና በብሔራዊ መግባባት ሒደት ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት መስማማታቸውን አስታወቁ፡፡
የታሪክ ምሁራንና የታሪክ ጸሐፊያን የምክክር መድረክ ከታኅሳስ አጋማሽ ጀምሮ ለአራት ቀናት በቢሾፍቱ ከተማ ያካሄደውን ስብሰባ ታኅሳስ 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲያጠናቅቁ፣ እንደ አንድ የዕውቀት ማኅበረሰብ ተቀራርበው ለመሥራት ከዚህ ቀደም የነበረውን የሙያ ማኅበራቸውን ዳግም ለማቋቋም መስማማታቸውን አስታውቀዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች የኩሪፍቱ ስምምነት-2013›› በሚል አስተባባሪ ኮሚቴው ታኅሣሥ 20 ቀን በሰጠው መግለጫ እንዳመለከተው፣ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበርን ዳግም መመሥረት ካስፈለገበት አንደኛው ምክንያት የታሪክ ሙያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡበትን ጫናና ተፅዕኖዎች ለመቋቋም፣ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የተሳሳቱ የታሪክ ትርክቶችን ለማረምና በተጨባጭና በአሳማኝ የታሪክ ማስረጃዎች ላይ የተመሠረተ ሳይንሳዊ የታሪክ አጻጻፍ ሥልትን የተከተሉ የታሪክ ኅትመቶችን ለማውጣት ነው፡፡
በሌላ በኩል ባለሙያዎቹ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት ተዘጋጅቶና ተተችቶ በየካቲት 2012 ዓ.ም. የፀደቀው የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ (Ethiopian History and the Horn) ኮመን ኮርስ ለምን እንዳልተተገበረ ሚኒስቴሩን የሚጠይቅና፣ የተዘጋጀው ሞጁል ለዩኒቨርሲቲዎች ተሠራጭቶ ትምህርቱ የሚጀመርበት ሁኔታ እንዲመቻች እንሠራለን ብለዋል፡፡
በታሪክ ትምህርትና በፖለቲካ መካከል ያለውን ጤናማ ትስስር ለማዳበር፣ ፖለቲከኞች በታሪክ ትምህርት ላይ የሚያሳድሩትን ጤናማ ያልሆነ ጫና ለማስተካከልና ችግሩን በሒደት ለመፍታት ተከታታይ ውይይት ለማካሄድ የታሪክ ምሁራኑ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የተሠሩ ሥራዎችን አጠናቅሮ የምክክር መድረክን፣ ውሳኔዎችና ስምምነቶች የሚያስፈጽሙና በኃላፊነት የሚያስተባብሩ 12 አባላትን መሰየማቸውን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ገልጸዋል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር፣ በዴስቲኒ ኢትዮጵያ አመቻችነት በተካሄደው የምክክር መድረክ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ 60 የኢትዮጵያ የታሪክ ምሁራንና የታሪክ ጸሐፊያን መሳተፋቸው ታውቋል፡፡
ከአስተባባሪ ኮሚቴ አባላት መካከል የታሪክ ኤሜሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ የመቀለ ዩኒቨርሲቲ የቅርስ ጥናት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ በከሪ (ዶ/ር)፣ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ጥጋብ በዜ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም በታሪክ የፒኤችዲ ተማሪ ጽጌረዳ ወልደ ብርሃን ይገኙበታል፡፡