Friday, March 31, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የፖለቲካው ምኅዳር ብቃት ከሌላቸው ግለሰቦችና ስብስቦች ይፅዳ!

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ በስፋት መገኘት የነበረባቸው ምሁራንና ልሂቃን በጉልበተኞች ምክንያት፣ ‹‹ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ›› ብለው መሸሻቸው ኢትዮጵያን በእጅጉ ጎድቷታል፡፡ በእነሱ ምትክ ደግሞ ሥልጣንና ጥቅም ብቻ የሚያነፈንፉ አቅመ ቢሶችና ተጧሪዎች መብዛት ያደረሰው ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ በሠለጠነ መንገድ በመነጋገር ፋንታ ማስፈራራትና ቃታ መሳብ የነገሠበት ብቃት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ከመድረኩ በመገለላቸው ነው፡፡ የተሻሉ ሐሳቦችን ማመንጨት የሚችሉ ባለምጡቅ አዕምሮዎች ወደ ጎን ተገፍተው በጡንቻቸው የሚያስቡ ብኩኖች በመብዛታቸው ምክንያት፣ ስሜታዊነትና ሥርዓተ አልበኝነት የፖለቲካ ምኅዳሩ መገለጫዎች ሆነዋል፡፡ ምክንያታዊነት ጠፍቶ በስሜት መነዳት የጎለበተው፣ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራው ዝግጅቱም ሆነ ብቃቱ በሌላቸው ሰዎች ስለሚመራ ነው፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እየተገፈፉ ንፁኃን የሚገደሉት፣ የሚታሰሩት፣ የሚሰቃዩትና የሚፈናቀሉት ጉልበተኞች ምኅዳሩን አጥብበው አፈና በማብዛታቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ያለ አቅማቸው ሥልጣን ላይ በመጎለት የአገር አጥፊዎች ተላላኪዎች በመበራከታቸው ነው፡፡

በተቃራኒው ጎራ ከተሠለፉት ውስጥ ብዙዎቹ መርህ ሳይሆን ኩርፊያ ያገናኛቸው በመሆናቸው፣ ከለቅሶና ከማጉረምረም ያለፈ ተሰጥኦ አልነበራቸውም፡፡ የዚያኑ ያህል ደግሞ የጉልበተኞች መናጆ በመሆን የሚጣልላቸውን ፍርፋሪ የሚለቃቅሙ ብዙ ነበሩ፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የደረሰበት ውሳኔ የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ምን ያህል ብልሹ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ከመሥፈርት ደረጃ በታች በመውረድ ጭምር ባደረገው ማጣራት 26 ፓርቲዎች ከ35 በመቶ በላይ የመሥራች ፊርማቸው ትክክል የሆኑትን ሲቀበል፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተብዬዎቹ ምን ያህል የወረዱ እንደሆነ ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ በዚህም መሠረት 26 የፖለቲካ ፓርቲዎች ከ35 በመቶ በታች ሆነው መሰረዛቸው ተገልጿል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ተጨማሪ ሁለት ፓርቲዎች እንደተሰረዙ ቦርዱ አስታውቋል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ማብራሪያ እንዲሰጡ ወይም አሟልተው እንዲያቀርቡ የተወሰነና የማጣራት ሒደታቸው ያልተጠናቀቀ 40 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተዘርዝረዋል፡፡ የማጣራት ሒደታቸው የተጠናቀቀ ነገር ግን የቴክኒክ መሥፈርቶች የቀሯቸው ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ማንነትም ተመልክቷል፡፡ በምርጫ ቦርድ መረጃ መሠረት በአጠቃላይ 73 የፖለቲካ ፓርቲዎች በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ከሆነ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሥልጡን የሆነ የፖለቲካ ፉክክር የሚደረግበት ነው ለማለት ያዳግታል፡፡

ምንም እንኳ መደራጀት ሕጋዊ መብት ቢሆንም፣ በዚህ በሠለጠነ ዘመን በእንዲህ ዓይነት የተዝረከረከ ሁኔታ ውስጥ መገኘት ተገቢ አይደለም፡፡ በዚህ አሳዛኝ ቁመና ላይ ተሁኖ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት መቅረብም ማሳፈር አለበት፡፡ ምክንያቱም ለዚህ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ ብቁ አይደሉምና፡፡ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ በከፍተኛ ዕውቀት፣ አቅምና ብቃት የሚመራ ነው፡፡ አማራጭ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የሚቀረፁት መንገድ ላይ ሳይሆን፣ ችሎታውና ልምዱ ባላቸው የተለያዩ የዕውቀት ባለቤቶች ነው፡፡ የፓርቲ አመራሮች፣ አባላትና ሌሎች የተለያዩ መስኮች ባለሙያዎች በውይይትና በክርክር የሚያዳብሩዋቸው ናቸው፡፡ የሕዝብን ቀልብ ለመሳብና ድምፁን ለማግኘት በከፍተኛ ጥንቃቄ በጥናት ላይ ተመሥርተው የሚቀረፁ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች፣ በጠንካራ አመራሮች የሚመሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውጤት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ስንት የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ደረጃ ይዘጋጃሉ ተብሎ ጥያቄ ቢቀርብ፣ የአንድ እጅ ጣቶች እንደሚያክሉ ያጠራጥራል፡፡ ከ100 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ በሚነገርባት አገር ውስጥ፣ በዚህ መጠን ለፓርቲ ፖለቲካ ያልተዘጋጁ የመብዛታቸው ሚስጥር ግልጽ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው በፖለቲካ ፓርቲዎቹ ውስጥ ሥራ አጦችና ተጧሪዎች መብዛታቸውን ነው፡፡

እስቲ የትኞቹ ፓርቲዎች ናቸው ወጣቶችን ሲያደራጁና ንቃተ ህሊናቸውን ሲያዳብሩ የሚታዩት? የትኞቹ ፓርቲዎች ናቸው አማራጭ ፖሊሲዎችን ይዘው አደባባይ የሚታዩት? የትኞቹ ፓርቲዎች ናቸው እንወክለዋለን ከሚሉት ሕዝብ ጋር የውይይት መድረኮች የሚያዘጋጁት? ምን ያህሎቹ ናቸው በሕጉ መሠረት የመሥራች ጉባዔ ለማድረግ የሕዝብ ድጋፍ ማሰባሰብ የቻሉት? ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች ጥያቄዎችን መመለስና በተግባር እንቅስቃሴያቸውን ማሳየት የሚችሉት በጣም ጥቂት ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ቁጥራቸው ከአንድ እጅ ጣት የሚያንስ፡፡ አባላቶቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን ለሕጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር ቁመና ለማድረስ የሚተጉ በጣም ትንሽ ናቸው፡፡ የተቀሩት ግን ምን እንደሚሠሩና ምን እንደሚፈልጉ አይታወቅም፡፡ ፍላጎታቸው ሥልጣንና ጥቅም ቢሆንም እንዴት ለማግኘት እንዳቀዱ አይታወቅም፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን በኩርፊያ ተጀቡነው የለመዱትን ለቅሶ ሊቀመጡ ይፈልጉ እንደሆነም ግልጽ አይደለም፡፡ በተናጠልም ሆነ በስብስብ ሕዝብ ፊት ሲቀርቡ የረባ አጀንዳ ይዘው አይቀርቡም፡፡ አማራጫችሁ የታለ ሲባሉ ‹ሕዝባችን ምን እንደምናደርግለት ያውቃል› እያሉ የተለመደውን ብልጣ ብልጥነት ለማሳየት ይሞክራሉ፡፡ ጠንከር ተደርገው ሲያዙ የባከነ ዕድሜያቸውን እየቆጠሩ በሚያውለበልቡት ዓርማ ሊያታልሉ ይፍጨረጨራሉ፡፡

እንወክለዋለን የሚሉት ሕዝብ እንዴት ከድህነት አረንቋ ውስጥ እንደሚወጣ፣ ሰብዓዊ ክብሩ ተጠብቆ እንዴት ማደግ እንዳለበትና በአጠቃላይ ለአገሪቱ መፃዒ ዕድል ምንም የሚያቀርቡት የበሰለ ጥናት የላቸውም፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩን ያጣበቡት ራሳቸውን ከድህነት ለማላቀቅ የሚጋጋጡ ግለሰቦችና ቡድኖች እንጂ፣ ለአገር ዕድገትና ለሕዝብ ኑሮ መለወጥ የሚተጉ ሰብዓዊነት የሚሰማቸው አይደሉም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው እነዚህ ወገኖች በቃችሁ መባል ያለባቸው፡፡ መጪው ምርጫ ቢያንስ ለአቅመ ፖለቲካ ያልደረሱ ግለሰቦችና ስብስቦች እንደሚራገፉበት ተስፋ ቢደረግም፣ የኢትዮጵያ መድበለ ፓርቲ ሥርዓት መጎልበት ያለበት ጥራት ባላቸው ውስን የፖለቲካ ፓርቲዎች መሆን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ቀደም ተለጣፊ በመሆን በምርጫ ወቅት ግርግር ፈጥረው የሚሰወሩ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነበሩ፡፡ እነሱ ዋነኛ ሥራቸው ለገዥው ፓርቲ አጃቢ በመሆን መደነጋገር መፍጠር እንጂ የረባ ቢሮ እንኳ አልነበራቸውም፡፡

በምርጫ ቦርድና በገዥው ፓርቲ በሚመደብ የድጎማ በጀት ግርግር ፈጥረው የሚሰወሩ ፓርቲዎች እየተቆጠሩ፣ የሕዝብ ድጋፍ የነበራቸው ባለራዕይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመድረክ ተገፍተው በርካታ ችግሮች መፈጠራቸው አይዘነጋም፡፡ ኢትዮጵያ ከእነዚህ አምታቾች መገላገል አለባት፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ የፖለቲካው የጨዋታ ሕግ የገባቸው ምርጥ ፓርቲዎች መናኸሪያ መሆን ይኖርበታል፡፡ ዴሞክራሲን በሚገባ ለመለማመድና ሥርዓቱን ዕውን ለማድረግ የሚቻለው፣ ቁጥራቸው በጣም ያነሰ ጠንካራ ክልላዊም ሆኑ አገራዊ ፓርቲዎች ሲኖሩ ነው፡፡ እንደ ማስ ስፖርት ቡድኖች በየመንደሩ ፓርቲ መፈልፈል ለመሥራቾቻቸውና ለአንጋቾቻቸው ፍላጎት ካልሆነ በስተቀር፣ እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝብ ፋይዳ የለውም፡፡ በሰጥቶ መቀበል የሚያምኑ፣ ለውይይትና ለድርድር ዝግጁ የሆኑ፣ በሥነ ምግባር የታነፁ፣ ለዘመኑ አስተሳሰብ የሚመጥኑ፣ በዕውቀትና በልምድ የጎለመሱ፣ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ክብርና ፍቅር ያላቸውና የመሳሰሉትን የሚያሟሉ ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካው ምኅዳር ውስጥ በስፋትና በምልዓት መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ከሴረኞች፣ ከዕውቀት አልባዎችና ዘመኑን ከማይመጥኑ ግለሰቦችና ስብስቦች የሚገላገለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ ብቃቱና ፍላጎቱ ያላቸው ኢትዮጵያውን ጠፍንጎ ከያዛቸው ሥጋትና ፍርኃት ውስጥ ይውጡ፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩም ብቃት ከሌላቸው ግለሰቦችና ስብስቦች ይፅዳ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

አገር የሚገቡ የግል ዕቃዎችን በሚገድበው መመርያ ምክንያት በርካታ ንብረቶች በጉምሩክ መያዛቸው ተገለጸ

በአየር መንገድ ተጓዦች ወደ አገር የሚገቡትን የግል መገልገያ ዕቃዎች...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

ሒጂራ ባንክ የ143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዘገበ

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ...

አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...

አይ የእኛ ነገር!

የዛሬው ጉዞ ከጀሞ ወደ ፒያሳ ነው፡፡ መንገዱ ለሥራ በሚጣደፉ፣...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሰላም ዕጦትና የኑሮ ውድነት አሁንም የአገር ፈተና ናቸው!

ማክሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ ጥያቄዎቹ በአመዛኙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ...

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...