Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኅብረተሰቡን  በስፖርቱ የመሳተፍና የመጠቀም ፍላጎት ማርካት እንዳልተቻለ ተገለጸ

የኅብረተሰቡን  በስፖርቱ የመሳተፍና የመጠቀም ፍላጎት ማርካት እንዳልተቻለ ተገለጸ

ቀን:

የኢትዮጵያን የስፖርት ውጤታማነት ለማጎልበት በየደረጃው ሰፊ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም በጊዜ ሒደት እያደገ የመጣውን የኅብረተሰቡን በስፖርት የመሳተፍና የመጠቀም ፍላጎት በሚገባው ልክ ማሟላት እንዳልተቻለ አገር አቀፍ የስፖርት ምክር ቤት ገለጸ፡፡ ምክር ቤቱ ማክሰኞ ታኅሣሥ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ባካሄደው አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔው፣ ችግሩ በዋናነት በአደረጃጀት፣ በአሠራርና በማስፈጸም ረገድ ሰፊና የሚታይ የአቅም ውስንነት መሆኑን ተመልክቷል፡፡

ስፖርቱን በበላይነት ለመምራትና ለማስተዳደር ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለበት መሆኑ የሚነገርለት ይህ ብሔራዊ የስፖርት ምክር ቤት፣ ‹‹ስፖርት ለሁሉም፣ ሁሉም ለስፖርት›› በሚል መሪ ቃል ባካሄደው ጉባዔው፣ ስፖርቱን ሕዝባዊ መሠረት ከማስያዝ አንፃር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ በተለይ  የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ራሱን ችሎ በአክሲዮን እንዲደራጅ የጀመረው አበረታች ጅምር፣ በሌሎችም የስፖርት ዘርፎች ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ዘመኑንና ጊዜውን የዋጀ መልካም ጅምር ነው ብሎታል፡፡

ብሔራዊ የስፖርት ምክር ቤቱ የተቋቋመው በ1990ዎቹ መጀመርያ ላይ ቢሆንም በተሰጠው ኃላፊነት ልክ ምንም ሳይፈይድ ስሙን ብቻ ይዞ ከሁለት አሠርታት በላይ ዕድሜ ማስቆጠሩ የሚታወስ ነው፡፡

በአዲስ መልክ ዓምና ሥራውን አንድ ብሎ የጀመረው ምክር ቤቱ፣ በወቅቱ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራባቸው ከተቀመጡለት የልማት ተግባራት መካከል፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመሩ ስታዲየሞች ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲጠናቀቁ ማድረግ አንዱ ሲሆን፣ በተለይ በፌዴራል ደረጃ በመገንባት ላይ የሚገኘው ብሔራዊ ስታዲየም የሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ እንዲጀመር በማድረግ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ርብርብ  እየተደረገ መሆኑ ኮሚሽነር ኤልያስ ሽኩር ለምክር ቤቱ ማስረዳታቸው የስፖርት ኮሚሽን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስነብቧል፡፡     

ኮሚሽነሩ ከብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ ጎን ለጎን ለስፖርቱ ዕድገት አሉ ተብለው የታመነባቸውን ችግሮች ለመቅረፍ በአገራዊ የለውጥ ጉዞ የተቃኘ አገራዊ የስፖርት ሪፎርም ፕሮግራም ተዘጋጅቶ በየደረጃው በማወያየት የትግበራ ምዕራፍ መጀመሩን ጭምር መናገራቸው ተመልክቷል፡፡

ከትግበራ ምዕራፎቹ መካከል ስፖርቱን በቢዝነስ ሞዴል እንዲመራ ከማድረግ አኳያ በተለይ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አማካይነት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ ራሱን በአጭር ጊዜ ውስጥ አደራጅቶ፣ ውድድሩን የቴሌቪዥን መብትና የውድድር ስያሜ መሸጥ መቻሉ ስፖርቱ ላይ ትልቅ ተስፋና መነቃቃት እንዲፈጠር ማድረጉ ለምክር ቤቱ ተብራርቷል፡፡

ኮሚሸነሩ የውድድሩ መሸጥ በዋናነት ለዓመታት የመንግሥት ጥገኛ ሆነው የቆዩት ክለቦች ራሳቸውን በፋይናንስ አቅም እንዲያጠናክሩ፣ ለተጨዋቾችና በዋናነት ታዳጊ ወጣት ተጨዋቾች በመላው ዓለም የመተዋወቅ ዕድላቸው እንዲሰፋ ከማድረጉም በላይ መልካም ገጽታን ለማስተዋወቅ ተጨማሪ ዕድል የሚፈጥር፣ ተግባሩም ለሌሎች የስፖርት ማኅበራት አርዓያነት ያለው ተግባር በመሆኑ ጅምሩን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ማለታቸው ታውቋል፡፡

የስፖርት ምክር ቤቱ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባርን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1097/2011 አንቀጽ 32/4/ሠ/ ላይ፣ ስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ማኅበራት ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ መመርያ የማውጣት፣ በፌዴራል ደረጃ የሚቋቋሙ የስፖርት ማኅበራትን የመመዝገብ፣ አስፈላጊውን ድጋፍ የመስጠት ሥልጣን እንዲሁም ከላይ በተጠቀሰው አንቀጽ መሠረት የሚወጡ ደንቦችንና መመርያዎችን የማፅደቅ ኃላፊነት የተሰጠው ስለመሆኑ ጭምር ከስምምነት መድረሱ ተነግሯል፡፡ 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኰንን የብሔራዊ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) የምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችና የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ወ/ሮ አበባ ዮሴፍ በሕዝብ ተወካዎች ምክር ቤት የሴቶች፣ ሕፃናት፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) እና ሌሎችም የስፖርት ማኅበራት ፕሬዚዳንቶችና የሥራ ኃላፊዎች በምክር ቤቱ ስብሰባ የታደሙ ስለመሆናቸው ጭምር ተነግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...