Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የእኛ አገር ትልቁ ድክመት የውጭ አገር ምርቶች ማራገፊያ መሆናችን ነው›› አቶ አስፋው አበበ፣ የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ዋና ዳይሬክተር

ኢትዮጵያ ያሏትን ሀብቶች በአግባቡ መጠቀም አልቻለችም፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቷ አንድ ዕርምጃ ከፍ እንዲል ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ቢገኝም፣ የውጭ አገር ምርቶችን በገፍ ከማስገባት ብዙም አልተቆጠበችም፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለሥልጣን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ ይገኛል፡፡ አቶ አስፋው አበበ የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ሥራቸውን በተመለከተ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ባለሥልጣን ከተመሠረተ አራት ዓመት አልፎታል ምን ያህል ተጉዟል?

አቶ አስፋው፡- የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የተመሠረተው በ2008 ዓ.ም. ላይ ነው፡፡ አምራቾች ከታች ተነስተው ወደ ትልቅ ደረጃ እንዲደርሱ የተሻለ የማምረቻ ቦታ እንዲያገኙና ፍላጎታቸው የተመጣጠነ እንዲሆን የሚሠራ ተቋም ነው፡፡ ተቋሙም በክልሎች ላይ መዋቅሮችን በመዘርጋት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እንዲያድግ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም በክልሎች ላይ የተበጣጠሰ አሠራር ሲሠራ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ችግሩን ለመፍታት የተቀናጀ ሥራ ለመሥራት ዕቅዶችን ይዘናል፡፡ በሚፈለገው ደረጃ ባይሆንም በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ፣ በእንጨት፣ በብረታ ብረት፣ በኬሚካል ሥራዎች  ላይ ጥሩ ውጤቶችን ማየት ጀምረናል፡፡ ስኬታችን ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ማሳያ እንዲሆን ከዚህ በፊት የነበሩትን ተግዳሮቶችን በመቅረፍና ቀጣይ የሚሠሩት ሥራዎች ላይ ትኩረት በመስጠት እየሠራን እንገኛለን፡፡ ከባለድርሻ አካላት ጋርም ተቀናጅቶ በመሥራትና ክልሎችም ለአምራቾች ድጋፍ እንዲያደርጉ እየሠራን ነው፡፡ ይህም  ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጀምሮ ከከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ አስፋው፡- ከአገልግሎት አንፃር የፋይናንስና የክህሎት ተቋማትን ከገበያ ጋር በማስተሳሰር ለአነስተኛና መካከለኛ አምራቾች ዕድሎችን በማፈላለግ ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ ውስጥ ማስገባት እንዲቻልና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እየሠራን እንገኛለን፡፡ የፋይናንስ እጥረት በሚገጥማቸው ጊዜ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙ እያደረግን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የልማት አጋሮችና ከመንግሥት ጋር በመሆን በዘርፉ ሥር ለሚገኙ ተቋማት በርካታ ድጋፎችን እያደረግን እንገኛለን፡፡ ተቋሙ ወደ ሥራ ከገባ ጊዜ ጀምሮ 276 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዕርዳታ ተገኝቷል፡፡ ከዚህ ውስጥም 126 ሚሊዮኑ ዶላሩ ሥራ ላይ ውሏል፡፡ በተያዘው ዓመትም የተረፈውን ከሚመለከታቸውው አካላትና ከክልሎች ጋር በመሆን ሥራ ላይ እንዲውል በማድረግ ላይ ነን፡፡ ይህንን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ሌላ ተጨማሪ 100 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ ለአምራቾች ድጋፍ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ማሽነሪና ሥራ ማስኬጃ ብድሮችን ለአምራቾች በተፈለገው መልኩ ለማቅረብ እየሠራን ነው፡፡ ይህ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በመቀነስ አገር ውስጥ ማምረት የሚቻልበትን መንገድ ሰፊ ያደርጋል፡፡ በርካታ የቆዳ ውጤቶችም ወደ ተለያዩ አገሮች መላክን ጨምሮ ሌሎች ምርቶችን በብዛት በማምረት የገበያ ትስስሩን በተገቢው መልኩ ማስቀጠል ላይ ሰፊ ሥራ ለመሥራት ዕቅዶችን ይዘናል፡፡ ይኼም የሚሆነው በዘርፉ ላይ ያሉትን ችግሮች በመዳሰስ፣ በማኅበረሰቡም ሆነ በአምራቹ ዘንድ ግንዛቤን በመፍጠርና ንቅናቄ በማድረግ ይሆናል፡፡  

ሪፖርተር፡- በዘርፉ ላይ ምን ዓይነት ችግሮች አሉ?

አቶ አስፋው፡- በእርግጥ ከዚህ በፊት በዘርፉ ላይ የተለያዩ ችግሮች ነበሩ፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሰፋ ያለ በመሆኑና ለአምራቾች ከግብዓት አኳያ ብዙም ድጋፍ ሲደረግላቸው ባለመቆየቱ ነው፡፡ በአንድ ተቋም ድጋፍ ብቻ ግን ችግሩ አይፈታም፡፡ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት፣ የገበያ ትስስርና በዚህ ሥር ላሉት አምራቾች የክህሎት ሥልጠና ተቋሙ ብቻ የሚሠራ መሆን የለበትም፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አንዱን አሟልተህ አንዱን የምትተው ከሆነ የሚሠሩትን ሥራዎች መሬት ማውረድ አይቻልም፡፡ ችግሩን ለመፍታትም የተናበበ አደረጃጀት ከመፍጠር አንፃር ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ በመሄድ ቅንጅታዊ አሠራሮችን ለመሥራት ዕቅዶችን ይዘናል፡፡ በዘርፉ ላይ ትልቅ ችግር የሆነው በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በሰዎች በኩል ጥያቄ ሲያስነሳ የነበረው የመሥሪያ ቦታ አለመኖሩ ነው፡፡ የመሥሪያ ቦታ ይዞታውም እንደ ማንኛውም የሥራ ዕድል ፈጠራ የሚሠራ ሼድ ባለመሆኑ ምክንያት በዘርፉ ላይ መጓተት ታይቷል፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ሼድ ለመሥራትም ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚጠይቅ ዘርፉ ላይ ክፍተት ማየት ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ችግር ውስጥ ሆነውም ውጤታማ የሆኑ አምራቾች ነበሩ፡፡ ወደፊትም ዓውደ ርዕይና ባዛር ላይ ሊታዩ የሚችሉ በርካታ አዳዲስ ሥራዎች መፍጠር ተችሏል፡፡ አምራቾቹንና አርሶ አደሩን በማስተሳሰር የግብርና ዘርፍ በተፋጠነ መልኩ እንዲያድግ እየተሠራም ይገኛል፡፡ ወደፊትም በአካባቢው ቢያንስ አንድ ኢንዱስትሪ እንዲኖር የሚሠራ ይሆናል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ሰፊ የገበያ ትስስር መፍጠር ይቻላል፡፡ በቅርቡም የአፍሪካ ቀጣና የገበያ ትስስር ኢትዮጵያ ትፈራረማለች፡፡ በዚህም ነፃ የገበያ ትስስርም ላይ አምራች ካልሆንንና የምናቀርበው ከሌለ ትልቅ ቦታ መድረስ አንችልም፡፡ ይህንንም ችግር ለመቅረፍና ሚዛናዊ አሠራር ለመሥራት ያሉንን አቅሞች በሙሉ መጠቀም ይገባል፡፡ የአምራቾቹን ቁጥርን በማብዛት ኢንዱስትሪውን ሰፋ ባለ መልኩ በመሥራት ጠንካራ የሆነ አሠራር ለመዘርጋት ዕቅዶችን ይዘናል፡፡ አብዛኛው ኢንዱስትሪም ሙሉ ጊዜውን እንዲያመርት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየተሠራ ይገኛል፡፡   

ሪፖርተር፡- ከክልሎች ጋር ያላችሁ ትስስር ምን ይመስላል?

አቶ አስፋው፡- ከዚህ በፊት ትልቅ ክፍተት የሆነብን ክልሎች ተናበውና ተቀናጅተው ባለመሥራታቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ መር ኮሚቴ በማዋቅር ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ክልሎች ድረስ በመሄድ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ እየሠራን እንገኛለን፡፡ ጥሬ ዕቃዎችም ለአምራቾች በአግባቡ እንዲደርሳቸው ለማድረግ ከክልሎች ጋር በጋራ እየሠራን ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በክልሎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የአሠራር ችግር የታየበት በመሆኑ ዘርፉ ላይ ብዙም ሳይሠራ ተቆይቷል፡፡ ችግሩ አሁን በተወሰነ መልኩ እየተቀረፈ ቢሆንም፣ ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ ይህ ካልሆነ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ትልቅ ማጥ ውስጥ የሚገባ ይሆናል፡፡ ብዙ ጊዜም የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው በሰው ዘንድ ባለመታወቁ ምክንያት ዘርፉ ላይ ዕድገት ማሳየት አልተቻለም፡፡  

ሪፖርተር፡- በሥራችሁ ውስጥ ምን ያህል አነስተኛና መካከለኛ አምራቾ አሉ?

አቶ አስፋው፡- በአሁኑ ወቅት በእጃችን ሥር ያሉ 20 ሺሕ የሚሆኑ አምራቾች ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ውስጥም 15,500 የሚሆኑት አነስተኛ ሲሆኑ፣ 4,500 የሚሆኑት ደግሞ መካከለኛ አምራቾች ናቸው፡፡ ይህም ቁጥር በየዓመቱ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ፣ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ በማሳደግ የዕድገት ሰንሰለቱን ማስረዘም ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም አልፎ በንግድ፣ በአገልግሎት፣ በአርብቶ አደር፣ በአርሶ አደር፣ በኮንስትራክሽንና ዳያስፖራዎች እንዲሁም ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡ ባለሀብቶችን ወደ አነስተኛና መካከለና ማኑፋክቸሪንግ እንዲገቡ የማድረግ ዕይታ በየክልሉ እንዲኖር የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ የሼድ አቅርቦቶችን ከማመቻቸት አንፃር ሰፊ ሥራ ከተሠራ ይኼ ቁጥር በየዓመቱ ዕጥፍ እየሆነ የሚሄድበት ዕድል ይፈጠራል፡፡ በዚህ መንገድም ከተሠራ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የምንሸጋገርበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ የአገሮችን የኢኮኖሚ ዕድገት በምናይበት ጊዜም በማኑፋክቸሪንጉ ላይ ሰፊ ሥራ በመሥራታቸው የመጣ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ የእኛ አገር ትልቁ ድክመት የውጭ አገር ምርቶች ማራገፊያ መሆናችን ነው፡፡ ይኼንንም መቀየርና መቀልበስ ከተቻለ ምርቶቻችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታይ ማድረግ ይቻላል፡፡ በዚህ ዙሪያም ላይም የሌላ አገር ተሞክሮን ለመውሰድ እያንዳንዱ ሰው አጀንዳው አድርጎ መሥራት አለበት፡፡  

ሪፖርተር፡- መንግሥትስ ምን ዓይነት ድጋፍ ያደርግላችኋል?

አቶ አስፋው፡- የማኑፋክቸሪንግ ጉዳይን ትኩረት በመስጠት መንግሥት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገልን ይገኛል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም መንግሥት ካወጣቸው ፖሊሲዎች አንዱ አገር በቀል ኢኮኖሚ ላይ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ ዘርፍ ላይ ሰፋ ያለ ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡ ለኢንዱስትሪ ዕድገትም ብድር ከማመቻቸት አንስቶ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረስ የተለያዩ መዋቅሮች ታች ድረስ እንዲዘረጋ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡ እያንዳንዱ ክልልም ኃላፊነት ወስዶ እንዲሠራ መንግሥት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህም ወደፊት የኢንዱስትሪ ዘርፍ እየጠነከረ እንዲመጣ ያደርገዋል፡፡ ከውጭ የሚገባው ምርትም 18 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ወደ ውጭ የምንልከው ምርት ሦስት ቢሊዮን ነው፡፡ ይህንንም ለመለወጥ የምንችለው ማኑፋክቸሪንግ ላይ ትኩረት አድርገን ስንሠራ ብቻ ነው፡፡ አገር ውስጥም በቀላል ሁኔታ ማምረት የምንችላቸውን ምርቶች ከሌሎች አገሮች የማምጣት አባዜን መቀነስ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያም የብዙ ነገሮች መገኛ በመሆኗ ያሉንን ሀብቶች በመጠቀም ኢንዱስትሪውን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ከመንግሥትም ባለፈ ባለሀብቶች ዘርፉ ላይ ትኩረት በመስጠት ያላቸውን አቅም መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡ ይኼ ከሆነም ወደፊት በኢኮኖሚ ላይ አንድ ዕርምጃ ከፍ ማለት ይቻላል፡፡ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ያሉትን ምርቶች ማሳደግና ዘመናዊ አሠራርን ማስተማር ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ለአምራቾቹ ግብዓት ከማቅረብ አኳያ ያለውን ሥራ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ አስፋው፡- ከዚህ በፊት የግብዓት አቅርቦትን በተመለከተ ሰፊ ክፍተት ነበር፡፡ አሁን ላይ ይህን አሠራር በመቀየር የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢ ድርጅት ማቋቋም ተችሏል፡፡ ድርጅቱ ለኢንዱስተሪዎች ጥሬ ዕቃ ማቅረብ እንዲችል የሚሠራ ነው፡፡ ይህም ድርጅት 1,884 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ በሁሉም ክልሎች የሚገኝ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ለማኑፋክቸሪንግ የሚውል ግብዓቶችን በማሟላት ሰፊ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ከዚህ በፊትም እንደዚህ ዓይነት የተሟላ አገልግሎት አይሰጥም ነበር፡፡ አሁን ላይም ይህን ሥራ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግና ምርቶቻችንን ገበያ ላይ ለማዋል እየተሠራ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣይስ ምን ለመሥራት ታስቧል?

አቶ አስፋው፡- በቀጣይ የመጀመርያ ሥራችን የሚሆነው በዘርፉ ላይ ያሉትን ችግሮች መቅረፍና ለማኅበረሰቡም ሆነ ለአምራቾች ስለሥራው ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡ ግብርናም ዘመናዊ በሆነ መንገድ ሊያድግ የሚችለው ከማኑፋክቸሪነግ ጋር ትስስር ከተፈጠረ ነው፡፡ በግብርናው ላይ ከዚህ በፊት ያልተለመዱ አሠራሮችን በመጠቀም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የውጭ ምርት ማራገፊያ ከመሆን ወጥተን የራሳችን አገር ምርት ተጠቃሚ የምንሆንበት መንገድ ለማመቻቸት በዘርፉ ላይ ሰፊ ሥራ የምንሠራ ይሆናል፡፡ የግንዛቤ ችግርም በመኖሩ ምክንያት ጥራት ባለው መልኩ ያመረቱ አምራቾች የሌላ አገርን ስም በመጠቀም ገበያ ላይ ሲያውሉም ይታያል፡፡ ይህም በኅብረተሰቡ በኩል ያለው የግንዛቤ እጥረት በመሆኑ ነው፡፡ ይህንንም ለመቅረፍና የአገር ውስጥ ምርቶችን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ መንግሥም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሰፋ ያለ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...