Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ የሀብት መጠኑን በ56 በመቶ ማሳደጉን ገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ አጠቃላይ የሀብት መጠኑን በ56 በመቶ በማሳደግ 31.8 ቢሊዮን ብር ማድረሱንና በ2012 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 781 ሚሊዮን ብር እንዳተረፈ አስታወቀ፡፡

ባንኩ የ2012 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙን በተመለከተ ይፋ ባደረገው መረጃ፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የታየው ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተለዋዋጭ ችግር የፋይናንስ ዘርፉን ከባድ ፈተና ውስጥ ቢከተውም፣ የባንኩ የሒሳብ ዓመት አፈጻጸም ውጤታማ ነበር ብሏል፡፡

በዚሁ መረጃ መሠረት፣ በበጀት ዓመቱ ማብቂያ ላይ 9.7 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ የተሰበሰበ ሲሆን፣ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ወደ 26.1 ቢሊዮን ብር በማሳደግ ካለፈው ዓመት በ59 በመቶ ዕድገት ያለው አፈጻጸም ለማስመዝገብ ስለመቻሉም ጠቅሷል፡፡

የባንኩ ደንበኞች ቁጥርን በ2012 ሒሳብ ዓመት 1.2 ሚሊዮን ደንበኞች ማድረስ ስለመቻሉ የሚገልጸው ባንኩ የሒሳብ ዓመት የባንኩ ደንበኞች ቁጥር 794 369 እንደነበር አመልክቷል፡፡

ከብድር አቅርቦት አኳያም ባንኩ በሒሳብ በበጀት ዓመቱ 8.3 ቢሊዮን ብር ብድር በመስጠት አጠቃላይ የብድር ክምችት መጠኑን ወደ 19.1 ቢሊዮን ብር ማሳደግ ችሏል፡፡ በ2012 የሰጠው የብድር መጠንም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ64.2 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው ተብሏል፡፡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በፈጠረው ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ጥንቃቄ የተሞላበት የብድር አሰጣጥ ሥርዓት ተግባራዊ በመደረጉም ጤነኛ ያልሆኑ ብድሮች መጠን ብሔራዊ ባንክ በሚያዘው መሠረት ከአምስት በመቶ በታች እንዲሆን ማድረግ ስለመቻሉም የባንኩ መረጃ ያሳያል፡፡

የባንኩ የካፒታልና መጠባበቂያ ገንዘብ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ36 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ 3.5 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ የሚያመለክተው የባንኩ መረጃ፣ የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ ካለፈው ዓመት በ40 በመቶ ወይም 621.1 ሚሊዮን ብር ዕድገት በማሳየት 2.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል ብሏል፡፡

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 3.1 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ ይህ ዓመታዊ ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ892.2 ሚሊዮን ብር ወይም የ40.2 በመቶ ብልጫ እንደነበረውም አመልክቷል፡፡ በዓመቱ ከተገኘው ጠቅላላ ገቢ ውስጥ ከብድር ወለድ የተገኘው ገቢ የ86.1 በመቶ ድርሻን በመያዝ ለዕድገቱ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደነበረው ተገልጿል፡፡ ቀሪው ደግሞ ወለድ ነክ ካልሆኑ ገቢዎች የተሰበሰበ ነው፡፡

ከወጪ አኳያም በሒሳብ ዓመቱ 2.3 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ወጪ ያወጣ ሲሆን፣ ይህ ወጪ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር፣ የ807 ሚሊዮን ወይም የ53 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሆኗል፡፡

እንዲህ ያለው የባንኩ የሥራ አፈጻጸም በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ከግብር በፊት 781 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገብ እንዳስቻለው ባንኩ ገልጾ፣ ይህ ትርፍ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ12 በመቶ ብልጫ እንዳለው አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት ለባለአክሲዮኖች ከእያንዳንዱ አክሲዮን የ33.6 በመቶ ወይም የአንድ አክሲዮን ዋጋ 336 ብር ትርፍ አስመዝግቧል፡፡

በልዩ ልዩ የባንክ አገልግሎቶቹ ያሳየው አፈጻጸም መልካም ቢሆንም፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝት ከዕቅድ አንፃር ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየበት መሆኑንም ባንኩ ጠቅሷል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ 169.6 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡

ባንኩ በ2012፣ 33 አዳዲስ ቅርንጫፎች በመክፈት አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ወደ 262 ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የባንኩ አገልግሎቶች ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ ‹‹አንበሳ ሄሎ ካሽ›› የተሰኘ የወኪል ባንኪንግ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝም ገልጿል፡፡ እስከ ሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ 2,868 ወኪሎችን በመላው ኢትዮጵያ መልምሎ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ ከ428 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ደንበኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ላለፉት ዓመታት የራሱ የሆነ ሕንፃ እንዲኖረው የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ እንደነበር ጠቅሶ፣ ይህንንም ተከትሎ ባንኩ በአዲስ አበባ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ G+8 ሕንፃ መግዛቱን አመልክቷል፡፡ በተመሳሳይ በትግራይ ክልል በመቐለ ከተማ ከዚህ ቀደም በሊዝ የተረከበውን ሕንፃ ግንባታ በማካሄድ ላይ ይገኛልም ብሏል፡፡ በመቀሌ ከተማ የገዛውን ጅምር ሕንፃ ባንኩን ሊገልጽ በሚችል መልኩ በአማካሪ ዲዛይን አሠርቶ ግንባታ ለመጀመር ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ስለመሆኑም አስታውቋል፡፡ ባንኩ ሀብቱን ከማሳደግ አኳያ በተያዩ ክልል ከተሞች የባንኩን ገጽታ በሚገልጽ መልኩ የተለያዩ ሕንፃዎችን ለመገንባት የረዥምና የአጭር ጊዜ ዕቅድ ነድፎ በመሥራት ላይ ይገኛልም ተብሏል፡፡

አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ አጠቃለይ የሠራተኞች ቁጥር 5,480 የደረሰ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ19 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በቀጣይም የባንኩን ስትራቴጂክ ግቦች ለማሳካት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በተለይም በአይቲ መሠረተ ልማትና ሴኪዩሪቲ ላይ ያተኮሩ ቁልፍ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ የሚሠራ መሆኑንም ገልጿል፡፡  

ባንኩ ቅዳሜ ታኅሳስ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ጠቅላበላ ጉባዔውን ያካሄደው የባንኩ የደይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንስዔ ባልተገኙበት ነው፡፡ ባንኩ ቅዳሜ ታኅሳስ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሣዔ ባልተገኙበት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች