በተጠናቀቀው የ2012 የሒሳብ ዓመት ከግብርና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ የቻለው ዘመን ባንክ፣ ካፒታሉን በ150 በመቶ በማሳደግ አምስት ቢሊዮን ብር እንዲሆን የባንኩ ባለአክሲዮኖች ውሳኔ አሳለፉ፡፡
ዘመን ባንክ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን ታኅሳስ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሄደበት ወቅት ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት፣ እስካሁን ከነበረው የተፈቀደ የሁለት ቢሊዮን ብር ካፒታል ውስጥ 1.8 ቢሊዮን ብሩ ተከፍሏል፡፡
የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ዘበነ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የባንኩን ካፒታል በ150 በመቶ በማሳደግ አምስት ቢሊዮን እንዲሆን በተወሰነው ውሳኔ መሠረት፣ ተጨማሪ ካፒታሉ በሦስት ዓመታት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡
ባንኩ ካፒታሉን ለማሳደግ ካስተላለፈው ውሳኔ ባሻገር የ2012 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙን በተመለከተ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አበበ ድንቁ (ፕሮፌሰር) አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ባንኩ አትራፊ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አፈጻጸሞች ውጤታማ እንደነበር አመልክተዋል፡፡
የባንኩን አፈጻጸም በተመለከተ ከቀረቡት አኃዛዊ መረጃዎች ውስጥ በሒሳብ ዓመቱ 2.8 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ የቻለ ሲሆን፣ ይህ የተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ከቀዳሚው ዓመት (2011) የ24 በመቶ ዕድገት በማሳየት 14.4 ቢሊዮን ብር መድረሱ አንዱ ነው፡፡
በ2012 ሒሳብ ዓመት ያገኘውን አጠቃላይ ገቢ 2.15 ቢሊዮን ብር ማድረስ የቻለው ዘመን ባንክ፣ ይህ ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ570 ሚሊዮን ብር ወይም የ36 በመቶ ዕድገት ያሳየ ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንካቸው ከሚያገኙ የውጭ ምንዛሪ 30 በመቶ ለባንክ እንዲያስገቡ ባስቀመጠው መመርያ መሠረት፣ ዘመን ባንክ በሒሳብ ዓመቱ 116.8 ሚሊዮን ዶላር ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ስለማድረጉም የቦርድ ሰብሳቢው ባቀረቡት ሪፖርት ጠቅሰዋል፡፡
ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ የሰጠውን ብድር በተመለከተም የብድር አቅርቦቱ ወደ 9.7 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱን አስታውቋል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ28 በመቶ ወይም የ2.1 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ ባንኩ ከሰጠው አጠቃላይ ብድር ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ የያዘው ለአምራች ዘርፍ የተሰጠው ሲሆን፣ ይህም 24.6 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡ ለአገር ውስጥ ንግድና አገልግሎት 20 በመቶ፣ ለሆቴልና ቱሪዝም 14.4 በመቶ እንዲሁም ለኤክስፖርት የግብርና ውጤቶችን ጭምር 13.3 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይዘዋል፡፡
የባንኩን የብድሮች ጤናማነት ለማረጋገጥ በተሠራው ተከታታይ ሥራ የተበላሹ ብድሮችን በተመለከተ ከተሰጠው ማብራሪያ መረዳት እንደተቻለው፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት የነበረውን የተበላሸ ብድር ማለትም 2.78 በመቶ ወደ 1.99 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል፡፡ ከዚህ ቀደም ለረዥም ጊዜ በተበላሸ ብድር ቋት ውስጥ ተከማችተው በፍርድ ቤትና በክትትል ላይ በነበሩ ብድሮች ላይ በተደረገ ክትትል 63 ሚሊዮን ብር ለማስከፈል መቻሉን የገለጹት ሰብሳቢው፣ ይህም የባንኩን የተበላሹ ብድሮች መጠን እንዲቀንስ አስችሏል ብለዋል፡፡
በ2012 ዓ.ም. የሒሳብ ዓመት ከግብርና ለሠራተኞች ከተከፈለው ማበረታቻ ክፍያ በፊት 1.04 ቢሊዮን ብር ትርፍ ያስመዘገበ መሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰር አበበ፣ ይህም በዕቅድ ተይዞ ከነበረው 808.5 ሚሊዮን ብር አንፃር ሲታይ የ29 በመቶ ጭማሪ የታየበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የትርፍ ምጣኔው ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀርም የ59 በመቶ ወይም የ388 ሚሊዮን ብር ዕድገት ያሳየ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ገንዘብ ላይ የገቢ ግብር 259.2 ሚሊዮን እንዲሁም ሕጋዊ መጠባበቂያና ሌሎች ተቀናሾች ከተቀነሱ በኋላ የሚቀረው 739 ሚሊዮን ብር ወደ ትርፍ ማቆያ ሒሳብ ተሸጋግሯል ብለዋል፡፡
ትርፍ በአንድ አክሲዮን በአማካይ ሲሠላ 462 ብር ወይም 46.2 በመቶ ያህል ሆኗል፡፡ ይህ የትርፍ ድርሻ ምጣኔ በኢንዱስትሪው ውስጥ በ2012 ከተመዘገቡት በከፍተኛነት ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ ነው፡፡
ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ባንኩ ለደንበኞቹ ያደረገውን ድጋፍ በተመለከተ፣ ለደንበኞች አቅም የፈቀደውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ የችግሩን መጠን ለመቀነስ ተገቢውን ጥረት ስለማድረጉ የቦርድ ሰብሳቢው አመልክተዋል፡፡ በዚህ ለደንበኞች እንደየዘርፉና የደረሰውን ተፅዕኖ ታሳቢ በማድረግ ከ0.5 እስከ ሦስት በመቶ የወለድ ቅነሳ ያደረገ ሲሆን፣ የአበባ አምራች ዘርፍ የደረሰበትን ከፍተኛ ጉዳት ከግምት በማስገባት ለሦስት ወራት ይከፈል የነበረውን ወለድ ጭምር በመሠረዝ ለደንበኞች ያለውን አጋርነት ያሳየበት ነው ተብሏል፡፡ ከዚህም ሌላ ከመንግሥት የቀረበለትን የድጋፍ ጥሪ በመቀበል በሽታውን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት አምስት ሚሊዮን ብር የለገሰ ሲሆን፣ ከተወሰኑ አገልግሎት ዘርፍ ከሚሰበሰበው ገንዘብ ላይ ለደንበኞቹ የ75 በመቶ ቅናሽ በማድረግ ቀሪውን 25 በመቶ በመሰብሰብ ለጤና ጥበቃ የሕክምና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ድጋፍ የሚውል 2.7 ሚሊዮን ብር በተጨማሪ ልገሳ ስለማድረጉም አመልክተዋል፡፡
የቦርድ ሰብሳቢው በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት እንደተግዳሮት የሚታዩ ክስተቶችንም ያስታወሱበት ነበር፡፡ በተለይ በዓመቱ ውስጥ ፈተና የነበረው በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ተከስቶ የነበረው የገንዘብ እጥረት ነው፡፡ ባንኩ ማኔጅመንቱን በተገቢው ሁኔታ በመቆጣጠር ተፅዕኖን በቀላሉ ማለፍ ከቻሉ ጥቂት ባንኮች ውስጥ አንዱ ለመሆን ስለመብቃቱ ገልጸዋል፡፡
‹‹ከባንክ ሥራዎች ውስጥ አንዱና ከፍተኛ ትኩረት የሚሻው የገንዘብ ፍሰት አስተዳደር ነው፡፡ ይህም በአግባቡ ካልተተገበረ በደንበኞች ዘንድ የሚፈጠር እምነት ማጣት ብቻ ሳይሆን የተቋሙን ህልውና ጭምር አደጋ ውስጥ ይከታል፡፡ ለወደፊቱም የባንኩ ብድርና የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ስለመተግበራቸው ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ ይሆናል፤›› ያሉት ሰብሳቢው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዚህ ረገድ ፈጥኖ ዕርምጃ በመውሰድ ኢንዱስትሪውን የታደገበትን አካሄድ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
ባንኩ ቅዳሜ ታኅሳስ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ አዳዲስ የቦርድ አባላት ምርጫ አከናውኗል፡፡ ዘመን ባንክ በአሁኑ ጊዜ የሠራተኞችን ቁጥር 998 አድርሷል፡፡
ባንኩ ኪዮስኮችን ጨምሮ ቅርንጫፎቹን ወደ 52 ከፍ ያደረገ ሲሆን፣ ይህም በተያዘው በጀት ዓመት በተወሰነ መልኩ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ተብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ብዛታቸው 68 በሆኑ አውቶማቲክ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች አማካይነት በቀን ወደ 598 ሺሕ ብር በዓመት ወደ 218.4 ሚሊዮን ብር የክፍያ አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን፣ በዚሁ የአገልግሎት መስጫ ማሽን የቪዛና ማስተር ካርድ አገልግሎት ለተጠቃሚዎች በመስጠት ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ማጎልበቻነት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡