Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ነባሩ የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ የፖለቲካ መጠቀሚያ እንደ ነበር ተገለጸ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  አዋጁን ለመተካት የቀረበው ረቂቅ አሁንም ክፍተቶች ያሉበት መሆኑ ተጠቁሟል

  ባለፉት 18 ዓመታት በአወዛጋቢነቱ የሚጠቀሰው የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ የፖለቲካ መጠቀሚያና የንግዱን ኅብረተሰብ እርስ በርስ እንዲጋጭ ሲያደርግ እንደነበር የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ ገለጹ፡፡

  አቶ ጌታቸው እስካሁን በሥራ ላይ ያለውን የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 341/95ን በአዲስ ለመተካት በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ለመምክር በተዘጋጀው መድረክ ላይ የነበረው አዋጅ እጅግ በርካታ ችግሮች የነበሩበት ከመሆኑም በላይ ደካማ ንግድ ምክር ቤቶች እንዲፈጠሩ ያደረገ ጭምር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

  ኢሕአዴግም አዋጁ መጠቀሚያ ስለማድረጉ የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ ‹‹የኢሕአዴግ መንግሥት የግሉን ዘርፍ አሳድጋለሁ ብሎ የተንቀሳቀሰ ቢሆንም፣ የሥርዓቱን ደጋፊዎች ባለሀብቶች ለመፍጠር ባደረገው እንቅስቃሴ የንግድ ምክር ቤቶችን ሚና ከጨዋታ ውጭ አድርጓል፤›› በማለትም ችግር እንደነበረበት አመልክተዋል፡፡

  ለዚህ በርካታ ምክንያቶች ሊጠቀሱ የሚችሉ መሆኑን በመግለጽም፣ የፓርቲ ወገንተኝነትና የፓርቲ ኩባንያዎች ለማስፋፋት እንዲቻል፣ ገበያውንም ሆነ የንግድ እንቅስቃሴውን በቁጥጥር ሥር በማዋል ከፖሊሲና ደንብ አኳያ የነፃ ንግድ ውድድር ሥርዓት ጥያቄ እንዳይኖር ምክር ቤቶችን ለይስሙላ እንዲደራጁ ማድረጉንም አስታውሰዋል፡፡

  ለዚህም መሣሪያ በመሆን ካገለገሉት ዕርምጃዎች አንዱ ላለፉት 18 ዓመታት የቆየው አዋጅ 341/95 እንደነበረ መግለጽ፣ ይህ አዋጅ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱ ተስማምተው እንዳይሠሩ ሁልጊዜ በንትርክ እንዲቆዩ በማድረግ ችግሩን ስለማባባሱም ያስታውሳሉ፡፡

  አዋጁ የንግድ ምክር ቤቶችን ከማጠናከር ይልቅ የፖለቲካ ጠቀሜታ እንዲኖረው ታስቦ የወጣ በመሆኑ፣ የግሉ ዘርፍ እንዲቀጭጭ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

  ኢሕአዴግ የተፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ እንዳይኖራቸው የንግድ ምክር ቤቶችን ሲያጣጥል እንደነበር የሚጠቅሱት ዋና ጸሐፊው፣ የተፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ እንዳይኖራቸው አባላት የሌላቸው፣ የማይሠሩና እውነተኛ ላልሆኑ ስም በመስጠት የግል ዘርፉ ወደፊት እንዳይራመድ ምክንያት እንደነበርም በማውሳት የነበሩትን ችግሮች በተለየ መልክ አብራርተዋል፡፡

  በሕግ አግባብነት ያልተመሠረቱ፣ በልዩ ልዩ ስም የሚንቀሳቀሱ የሥርዓቱ ደጋፊዎችን በመፍጠር ሕገ መንግሥቱ የፈቀደውን በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት እያጣቀሰ ነጋዴዎችን በልዩ ልዩ ስም በማደራጀት፣ የንግዱ ኅብረተሰብ በአንድ ላይ ተደራጅቶ እንዳይንቀሳቀስና በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የንግድ አካላት እንዳይስማሙ፣ ተቀባይነትና ተደማጭነት እንዳይኖራቸው አድርጓል ሲሉም ኢሕአዴግን ወቅሰዋል፡፡

  እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ተደማምረው በርካታ አባላት ከምክር ቤቱ እንዳሸሹ፣ በመሸሻቸው ምክንያትም 99 በመቶ የሚሆኑት የአገሪቱ ንግድ ምክር ቤቶች ለአባሎቻቸው አገልግሎት ለመስጠትና ሠራተኛ ለመቅጠር ከማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውም የዚሁ አዋጅና የቀደመው ኢሕአዴግ ውጤት መሆኑን አመላክተዋል፡፡

  አብዛኛዎቹ ንግድ ምክር ቤቶች ከአባሎቻቸው የሚሰበስቡት ከ100 ሺሕ ብር የማይበልጥ ሆኖ የመገኘቱ ሚስጥርም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡  

  አሁንም የተዋጣለት ሕግ ማውጣት ተገቢ ስለመሆኑ ያመለከቱት ዋና ጸሐፊው፣ ይህ ባይሆን ችግሩ የከፋ ስለመሆኑ ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡  

  ‹‹ምክር ቤቶቻችን ለውጡ ከመጣላቸው ግንባር ቀደም ተቋማት መካከል ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥት በአገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲውና በአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ለግሉ ዘርፍ የሰጠው ትኩረትም ተገቢ መሆኑን እናምናለን ብለዋል፡፡

  ይህንን የብልፅግና ራዕይ ተግባራዊ ሆኖ ለማየት የግሉን ዘርፍ በርካታ ችግሮች ማቃለል የሚጠየቅ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ ወቅቱንና ጊዜውን ያገናዘበ የሕግ ሥርዓት መዘርጋትና ጠንካራ አደረጃጀት እንዲኖር ማድረግ ተቀዳሚው ይሆናል፡፡

  ለግሉ ዘርፍ መከበር የሚሠራ ነፃ ውድድር ያለበት የንግና ኢንቨስትመንት እንዲጎለብት የሚያደርግ ተቋም መፍጠር ተገቢ ነው፡፡ ይህንን ዓይነት ተቋም ኖሮ ነፃነቱ የተጠበቀ የንግድ እንቅስቃሴ ማረጋገጥ ካልተቻለ፣ ኩባንያዎች ወደ ውጭ አገር ሄደው መሥራትን እንደ አማራጭ እንዲመለከቱ ማድረጉ አይቀሬ ነው የሚል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡  

  አዋጁ ባለሀብቱ አገሬ ብሎ የሚሠራበት፣ የሚዳኝበት ብቃት ያለው አገልግሎት እንዲሰጠው የሚያስችል መሆን አለበት ያሉት ዋና ጸሐፊው፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የንግድ ቀጣና ፈራሚና በቅርብ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን መንግሥትን የያዘውን በጎ አቅጣጫ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የሕግ ማዕቀፎች ቁጥጥር ከማድረግ ተላቀው የግሉ ዘርፍ በነፃነት የሚንሸራሸርበት የንግድና የኢንቨስትመንት ሜዳ መቅረጽ ያስፈልጋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡ለውይይት የቀረበው ረቂቅም፣ ከዚህ ቀደም የነበረውን የሚያስተካክል ወደፊትም የሚጠቅም መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

  ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ባለፈው ሳምንት ይፋ በተደረገው ረቂቅ አዋጁ ላይ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሰሞኑን ባዘጋጀው መድረክ ላይ፣ ብዙዎቹ የንግድ ኅብረተሰቡ ተወካዮች ረቂቅ አዋጁ አሁንም ሊሻሻሉ የሚገባቸው አንቀጾችን ይዟል ብለው ተሟግተዋል፡፡ የረቂቁን ዝግጅት በተመለከተ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተሰጠውን ማብራሪያ ተከትሎ የንግድ ኅብረተሰቡ ተቃውሞ ካነሳባቸው ጉዳዮች አንዱ፣ በረቂቅ ሕጉ አባልነትና የውጭ ጉዞዎችን በተመለከተ የተቀረፁት አንቀጾች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በተለይ የውጭ ጉዞን በተመለከተ የከተማ ንግድ ምክር ቤቶች ብሔራዊውን ወይም የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትን ይሁንታ ማግኘት እንደሚገባቸው መግለጹ አግባብ አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡ ይህ አንቀጽ የከተማ ንግድ ምክር ቤቶችን ጥረት የሚገታ አላስፈላጊ አንቀጽ ነው በማለት የሞገቱት የንግድ ምክር ቤቱ አባላት፣ የከተማ ንግድ ምክር ቤቶች ነፃነት የሚገፋ በመሆኑ መሻሻል ይኖርበታል ብለዋል፡፡

  በየውጭ ጉዞን በተመለከተ አስተያየት ከሰጡት መካከል የቀድሞው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አያሌው ዘገየ ይገኙበታል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ አሁን በረቂቁ ላይ እንደተቀመጠው የውጭ ጉዞዎችን አገራዊው የንግድ ምክር ቤት መፍቀድ አለበት የሚለው አንቀጽ ችግር የሚፈጥር መሆኑ ነው፡፡

  የከተማ ንግድ ምክር ቤቶች በፈጠሩት ግንኙነት ያዳበሩት አሠራር በመኖሩ አገራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ሳይፈቅድ የውጭ ጉዞ አይካሄድም መባሉ አግባብ እንዳልሆነና ባይሆን ‹‹ያሳውቁ›› በሚል ቢተካ የሚል ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

  በተመሳሳይ የቀድሞው የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ኤልያስ ገነቲ የአቶ አያሌውንና በተመሳሳይ አስተያየት የሰጡትን በመደገፍ የከተማ ንግድ ምክር ቤቶች በውጭ ጉዞ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትን ማስፈቀድ አለበት የሚለው አንቀጽ ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ፣ ምክር ቤቶቹ በፍፁም ፈቃድ መጠየቅ የለባቸውም ብለዋል፡፡ ይህ አንቀጽ ከተቀመጠ ነገሮችን እንደሚያወሳስብም ያላቸውን ሥጋት አመልክተዋል፡፡

  በአዲሱ ረቂቅ ሌላው ከንግዱ ኅብረተሰብ ሊስተካከል ይገባል ተብሎ ብዙ ያነጋገረው ጉዳይ የንግድ ምክር ቤቶች አባልነት በግዴታ ይሁን ተብሎ የተጠቀሰው ነው፡፡

  በዕለቱ በረቂቁ ዝግጅቱ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ተወካይ፣ አባልነት እንዴት ይሁን? በሚለው ላይ የተለያዩ አማራጭ ታይተው አባልነት በግዴታ ይሁን የሚለው ሊቀመጥ ችሏል፡፡

  ይህም ከሆነባቸው ምክንያቶች አንዱ ንግድ ምክር ቤቶች ያላቸው አባላት ቁጥር ማነስ ነው፡፡ ስለዚህ አባልነትን በአስገዳጅነት ማስቀመጥ እንደ አማራጭ የተወሰደ ሆኗል፡፡

  ይሁንና በዕለቱ የተገኙ የንግድ ምክር ቤቱ አባላት ውስጥ አንዳንዶች በዝግጅት ይሁን በሚሉና በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ሆኖ ይቀጥል የሚል የተለያዩ አስተያየቶች የተሰነዘሩ ሲሆን፣ አንዳንዶች ደግሞ አባልነቱ በእጅ አዙር አስገዳጅ ይሁን የሚሉ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ይህም በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው ንግድ ምዝገባና መሰል ሥራዎች በንግድ ምክር ቤቶቹ በኩል ሆነው ከዚያ በዚያ መሠረት የንግድ ኅብረተሰቡ በተዘዋዋሪ አካል እንዲሁ ማድረግ የሚለውም ሐሳብ ቀርቧል፡፡

  በዚህ አባልነት ጉዳይ ላይ ሌላው የተሰነዘረው ሐሳብ ኩባንያዎች በአስገዳጅነት አባል ይሁኑ ግለሰቦች ደግሞ በፈቃደኝነት ላይ በተመሠረተ መልኩ አባል ይሁኑ የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡ ሌላው አደረጃጀቱን በተመለከተ ከቀደመው የተለየ አይደለም የሚለው ሐሳብ አንዱ ሲሆን፣ ይህም ጉዳይ እንደገና ይታይ የሚል ሐሳብ ቀርቧል፡፡

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ 20 ሺሕ አባላት ያሉት መሆኑን የገለጹት የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ፣ በአንፃራዊነት ሲታይ ትልቁ የአገሪቱ የንግድ ምክር ቤት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

  የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት 70 ከሚሆኑ ዓለም አቀፍ አቻ ማኅበራት ጋር በንግድና ኢንዱስትሪ በትብብር እየሠራ የሚገኝ ሲሆን፣ ከበርካታ የልማት አገሮች ጋር በመሆን የልማት ፕሮጀክቶች በመተግበር ላይ ነው፡፡

  በዚህ ረቂቅ አዋጅ ለከተማ ንግድ ምክር ቤቶች ተገቢ ትኩረት ያለመሰጠቱ ብዙዎችን ማሳሰቡ አልቀረም፡፡ የውይይት መድረኩ ግብዓት ለማሰባሰብ የተዘጋጀ በመሆኑ በረቂቁ ላይ ማሻሻያ ይደረጋል የሚል እምነት ያላቸው ወገኖች ረቂቅ አዋጁ እንዳለ እንዲፀድቅ ከተደረገ በቀደመው አዋጅ እንደታየው አሁንም ለግል ዘርፉ ዕድገት ጋሬጣ ይሆናል ብለዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች