በአዲስ አበባ ከተማ ለኅብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል የሚረዳ የኔትወርክ መሠረተ ልማት ሲስተሞችን አጠናቆ ወደ ሥራ ማስገባቱን የከተማዋ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶችን ታኅሣሥ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ሥራ አስጀምረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ሰርሞሎ እንደገለጹት፣ በአራዳ፣ በቂርቆስና በኮልፌ ቀራንዩ ክፍለ ከተሞች ላይ 240 ሚሊዮን ብር ወጪ በማውጣት ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ የኔትወርክ፣ የሴኪዩሪቲ፣ የኢንተርኔት፣ የአይፒ ኤክሰስ፣ የወረፋ ማስጠበቂያ ሲስተም፣ የዳታ ሴንተር፣ የከተማ አቀፍ ሜይል ሲስተም ሌሎች መሰል ቴክኖሎጂና መሠረተ ልማቶችን ሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም በ18 ወረዳዎች ላይ 46 ሚሊዮን ብር ወጪ በማውጣት የኔትወርክ ዝርጋታ ፕሮጀክቱን በማጠናቀቅ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች ላይም በመብራት መቆራረጥና የኔትወርክ ችግር እንዳይኖር የአገልግሎት አሰጣጡ የተፋጠነ እንዲሆን ከኢትዮ ቴሌኮምና ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በጋራ ተቀናጅተው የሚሠሩ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የከተማዋን የኔትወርክ ዝርጋታ የተፋጠነና የተቀላጠፈ ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን ያወሱት አቶ አብርሃም የከተማ ሴክተሮችንና ክፍለ ከተሞችን ለማስተሳሰር እንዲሁም ሲስተሞችን አበልፅጎ ለመተግበር እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ለኅብረተሰቡ የሚሰጠው አገልግሎት ለማሻሻልና የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ ዕውን ለማድረግ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግም ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ዓለም በቴክኖሎጂ ሥልጣኔ የበለፀገች በመሆኑ ያሉንን አቅሞች በመጠቀም ካደጉት አገሮች እኩል ተርታ የምንሠለፍበት ጊዜ አሁን ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
የአገልግሎት መስጫ የዲጂታል የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶች መተግበር የአገልግሎት ፈላጊው አካል ጊዜን ከመቆጠብ እንግልትን ከማስቀረቱም ባለፈ ሙስናንና ብልሹ አሠራሮችን ለመከታተል ፋይዳው የጎላ መሆኑን ወ/ሮ አዳነች ሳይገልጹ አላለፉም፡፡