Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊእውን የሆነው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት

እውን የሆነው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት

ቀን:

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በኢትዮጵያ መንቀሳቀስ ከጀመሩ አያሌ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ከረዥም ዓመታት እንቅስቃሴያቸው አንጻር የተጫወቱት ሚና ሲታይ ግን ጉልህ እንዳይደለ ይወሳል፡፡ በተለዋወጡ መንግሥታት ውስጥም ለዕድገትና ልማት የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚያስችላቸውም ምቹ ሁኔታ እንዳልነበራቸውም በየጊዜው የተሰማ ነው፡፡

በተለይ ከ2000 ዓ.ም. ወዲህ የነበሩት ዓመታት የብዙዎቹ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ህልውና ፈተና ውስጥ የወደቀበት፣ ከፊሎቹ መንቀሳቀስ ተስኗቸው የከሰሙበት፣ ያሉትም ቢሆኑ በእጅጉ የተዳከሙበት፣ ችግርና እንግልት የተፈራረቀባቸው እንደነበር የትናንት ትዝታ ነው፡፡

ካለፉት ሁለት ተኩል ዓመታት ጀምሮ ያለው ሁኔታ ሲዳሰስ ደግሞ ኢትዮጵያ በበርካታ የለውጥ ዕርምጃዎች (ሪፎርም) ውስጥ መገኘቷ በገሃድ እየታየ ነው፡፡ ሪፎርሙ በተለይ ስር የሰደደ መዋቅራዊ ችግሮች የነበረባቸውንና የሕግ ማዕቀፍ ለውጥ የሚጠይቁትን ዘርፎች ሲለይ ቀዳሚ ትኩረት ያገኘው የሲቪል ማኅበረሰብ ዘርፍ ሆኖ ተገኝቷል፡፡  

በዚህም የተነሳ እስካሁን ለታዩት ተግዳሮቶች ዋነኛ መንስዔ ሆኖ የቆየው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 621/2001 በሪፎርሙ ተሽሮ ለዘርፉ መጎልበት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሎ የታመነበት አዲስ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 በመውጣቱ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ በዚህም አዋጅ አንቀጽ 85 መሠረትም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ ምክር ቤት በኢትዮጵያ መመሥረቱም በይፋ ተበስሯል፡፡

ታኅሣሥ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ በይፋ የተበሰረው ይህ ምክር ቤት 3000 የሲቪል ማኅበራትና ድርጅቶችን በአባልነት አቅፏል፡፡ ወደ ሥራ እንዲገባ የሚያስችለውም መተዳደሪያ ደንብ አለው፡፡ በ25 አንቀጾች ተደራጅቶ ከተዘጋጀው ከዚሁ መተዳደሪያ ደንብ ለመረዳት እንደተቻለው የምክር ቤቱ ዋና ጽሕፈት ቤት አዲስ አበባ ከተማ ሲሆን የሥራ ቋንቋውም አማርኛና እንግሊዝኛ ነው፡፡

ጽሕፈት ቤቱ በክልሎችና በከተማ አስተዳድሮች አመቺ የሆኑ አደረጃጀቶች ይኖሩታል፡፡ እንደ አስፈላጊነቱም ሌሎች የሥራ ቋንቋዎችም በሥራ ላይ ሊውሉ ይችላሉ፡፡ ድርጅታዊ መዋቅርን በተመለከተ ደግሞ ጠቅላላ ጉባዔ፣ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ ሴክሬታሪያትና እንደ አስፈላጊነቱ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የሚዋቀሩ ንዑሳን ኮሚቴዎች እንዲሁም ሌሎች በጠቅላላ ጉባዔ የሚወሰኑ መዋቅር ሊኖረው እንደሚችል ከመተዳደሪያ ደንቡ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ለጋሽ ድርጅቶች ከአገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ሊኖራቸው የሚችለውን መስተጋብር ማጠናከር፣ ድርጅቶቹ በሰላምና በዴሞክራሲ ዕሴት ግንባታ ውስጥ እንዲሳተፉ ማስተባበርና ማቀናጀት የምክር ቤቱ ቀዳሚ ዓላማ መሆኑንም በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ተመልክቷል፡፡

‹‹የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከአፈጣጠራቸው ስንነሳ ፖለቲካዊም ሆነ ትርፍን መሠረት ያደረገ ዓላማ ስለማይኖራቸው ሚዛንን በማስጠበቅ ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ፣ ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራትን በማከናወን የአገርን ብልጽግና እንዲያፋጥኑ ይጠበቃል፤›› የሚሉት የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ናቸው፡፡

በተለይም የነቃና በነፃነት የተደራጀ፣ በሐሳብ ልዕልና የሚያምን፣ አገራዊ ክብርን የሚያስጠብቅ፣ በራሱ የሚተማመን አምራች ዜጋን በማፍራት ረገድ ዘርፉ ከፍተኛ አበርክቶት እንደሚኖረው መታመኑን ዋና ዳይሬክተሩ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በተቋማዊ ሪፎርም ስኬትና አዲሱን አዋጅ ተከትሎም የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ከ1150 በላይ አዳዲስ ድርጅቶችን ኤጀንሲው መዝግቦ ዕውቅና እንደሰጠ፣ ይህም ሁኔታ የሲቪክ ምህዳሩ ስለመስፋቱና ስለ ዘርፉ መነቃቃት እንደ አንድ ማሳያ ሊቀርብ እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ተስፋዬ ዳባ ‹‹በአገራችን የሠለጠነ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲሰፍን፣ በክርክርና በሐሳብ የበላይነት የሚያምን፣ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን የሚጠየፍ ትውልድ ለመፍጠር እንዲሁም አገራችን ወደ ቀደመው ገናናነት እንድትመለስ ለማድረግና የነቃ፣ የተደራጀ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እየተካሄደ ባለው እንቅስቃሴ ላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚና በእጅጉ የላቀ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ከፖለቲካ አሠራር ገለልተኛ የሆነ፣ ከተፅዕኖ የተጠበቀና ብቃት ያለው ማኅበረሰብ መፍጠር፣ እንዲሁም ውጤታማ የሆነ የመንግሥት መዋቅርና አደረጃጀት እንዲኖር በማድረግ ረገድ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ብዙ አስተዋጽኦ እንደሚጠብቅ አቶ ተስፋዬ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ምክር ቤቱ ዘንድሮ የሚካሄደውን አገራዊ ምርጫ ፍጹም ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና የሕዝብ አመኔታ የተቸረው እንዲሆን ለማድረግ፣ ምርጫውንም በመታዘብና ስለዴሞክራሲ ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡

የክርስቲያን በጎ አድራጎት ልማት ድርጅቶችን ማኅበራት ኅብረት (ሲሲአርዲኤ) ዋና ዳይሬክተርና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መድረክ ሰብሳቢ ንጉሡ ለገሠ (ዶ/ር) የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተጠናክሮ ማየት ለእኛ ብቻ ሳይሆን የአጋሮቻችንም ጭምር የዘወትር ፍላጎት ነው ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...