Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየገና ባዛር በኮቪድ-19 ጥላ ሥር

የገና ባዛር በኮቪድ-19 ጥላ ሥር

ቀን:

አምና የገና ዋዜማን በማስመልከት በተለያዩ ቦታዎች የውጭና የአገር ውስጥ ነጋዴዎችን ያሳተፉ ባዛሮች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ ገና ሊደርስ ሳምንት ያህል ሲቀረው ይበልጥ ከደመቁት ባዛሮች ጥቂቶቹ በተለይም በየጎዳናው በነጭ ድንኳን የተከናወኑት እስከ ጥምቀት ዘልቀው ነበር፡፡ በየክፍላተ ከተሞች የተደራጁ የአነስተኛና ጥቃቅን ነጋዴዎችም በፒያሳ፣ በአራት ኪሎ፣ በሜክሲኮ፣ በአዲሱ ገበያ፣ በጀሞና በተለያዩ የከተማዋ ሥፍራዎች የተለያዩ ቁሳቁሶችንና ምግቦችን ለገበያ አቅርበዋል፡፡

የመገበያያ ቦታዎቹ ከመገበያየት በተጨማሪ የበዓሉ ድምቀትም ናቸው፡፡ ከመገበያያ በኋላ ትከሻና ወገብ በሚነሽጡ ሙዚቀኞች ምሽቱን በማድመቅም ለብዙዎች መዝናናትን የፈጠሩ ናቸው፡፡

ባዛሮች ሲከፈቱ በዓልን ይንተራሱ እንጂ ለመገበያየት የሚመጡ ተገልጋዮች ለበዓል ብቻ ሳይሆን ረዘም  ላለ ጊዜ የሚሆኑ ምግቦችን፣ የፅዳት ዕቃዎችንና ሌሎችንም የሚሸምቱበት ነው፡፡ በእነዚህ ቦታዎች ከምግብ ውጭ የእንጨት ሥራዎች፣ ኤሌክትሮኒክ፣ የወጥ ቤት ዕቃዎች፣ ጌጣጌጦች፣ አልባሳትና ጫማዎችን የአገር ውስጥና የውጭ አገር ነጋዴዎች ይዘው ብቅ ስለሚሉ ለሸማቹና ለነጋዴ ጥሩ ዕድል መፍጠራቸውም እሙን ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ለዓመታት ሲካሄዱ የነበሩ ባዛሮች ግን ዓምና መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ ለዓመት ያህል ተቋርጠዋል፡፡ ዘንድሮ ግን ኮሮናን እየተጠነቀቁ ማከናወን ይቻላል በሚል በኮቪድ ወቅት የመጀመርያው የገና ባዛር ተጀምሯል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የተዘጋጀው ባዛር እንደቀደመው በጉልህ የደመቀ ባይሆንም እየተካሄደ ነው፡፡

እንደ ቀድሞው የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ውስጥ ባይከናወንም በኦሮሞ ባህል ማዕከል፣ በመቻሬ ሜዳና በአነስተኛና ጥቃቅን በተደራጁ ነጋዴዎች ደግሞ  በፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ ሜክሲኮ፣ እስታዲየምና የተለያዩ ቦታዎች ላይ አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ፣ የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለሥልጣን ባዛሮች ክፍት ሆነዋል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ባዛሮች ለሕዝብ ክፍት ቢደረጉም በእነዚህ የመገበያያ ቦታ በተለይም ብሪታንያና ደቡብ አፍሪካ መልኩን ቀይሮ ከመጣው የኮሮና ወረርሽኝ ጥንቃቄ አንፃር ሲታይ እምብዛም ተገልጋዮች ሲጠነቀቁ አላስተዋልንም፡፡  

ባደጉ አገሮች የቫይረሱ መስፋፋት ምክንያት ከሆኑ ቦታዎች ውስጥ መገበያያ ቦታዎች ቢሆኑም፣ በኢትዮጵያ በእነዚህ ሥፍራዎች ልቅነት ይታያል፡፡ በኢትዮጵያ ኮሮና ከተከሰተ በኋላ የመገበያያ ባዛሮች (ኤግዚቢሽኖች) ትምህርት ቤቶች፣ ስብሰባዎችና ሌሎችም ገደብ የተጣለባቸው ቫይረሱን በቀላሉ ለማሠራጨት ዕድል ስለሚፈጥሩ ነበር፡፡

ሆኖም መንግሥት እንቅስቃሴዎችን ያገደበት፣ አፍና አፍንጫ ሸፍኑ ያለበትን ምክንያት ኅብረተሰቡ የተቀበለው አይመስልም፡፡ በተለይ በአፍላ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ለበሽታው ቁብ የሰጡት አይመስልም፡፡ በየኤግዚቢሽኑ ሥፍራዎች ማድረግ ስለሚገባቸው ሰው እስኪነግራቸው የሚጠብቁ መኖራቸውን ታዝበናል፡፡ ‹‹ኖ ማስክ ኖ ሰርቪስ›› የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ያላደረገ አገልግሎት አያገኝም የሚል መመርያ ተግባራዊ ቢደረግም ከአገልግሎት ሰጪውም ሆነ ከተቀባዩ ይህንን የማይተገብሩ ተመልክተናል፡፡ የአፍና አንፍጫ መሸፈኛ አድርገዋል ለመባል ያህል አፍንጫቸውን አጋልጠው አፋቸውን ብቻ የሚሸፍኑ ማየቱም የተለመደ ሆኗል፡፡

አንዳንድ አገሮች የወረርሽኙ ሥርጭት ደግሞ በማገርሸቱ የእንቅስቃሴ ገደብ በድጋሚ መተግበር መጀመራቸው ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ የአዲሱ ኮሮና ወረርሽኝ እስካሁን ይኑር አይኑር ይፋ ባይደረግም፣ እንደ ሌሎች አገሮች ሥጋት ውስጥ መግባቷ አይቀሬ ነው፡፡ በተለይም ወረርሽኙ እንዲስፋፋ ዕድል የሚከፍቱ እንቅስቃሴዎች ዋጋ እንዳያስከፍሉ ጤና ሚኒስቴርና የጤና ባለሙያዎች ሥጋታቸውን በተደጋጋሚ እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

የበዓል ግብይቶችን በተለይ ባዛሮችን በተመለከተ ሪፖርተር በየቦታው ተዘዋውሮ ለመቃኘት ሞክሯል፡፡ ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ መቻሬ ሜዳና የኦሮሚያ ባህል ማዕከል እንዲሁም በፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለሥልጣን የተዘጋጀው ባዛር ካየናቸው ቦታዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በእነዚህ ሥፍራዎች የኮሮና ወረርሽኝ መኖሩን እንኳን ግምት ውስጥ ያስገባ ግብይት የሚፈጽሙ ጥቂቶች ናቸው ለማለት ይቻላል፡፡

የቫይረሱን አሳሳቢነት ግምት ውስጥ አስገብተው የሚንቀሳቀሱት ቁጥር እጅግ አነስተኛ መሆናቸውን ዓይተናል፡፡ በመገበያያ ቦታዎቹ የእጅ መታጠቢያ ከአንዳንዶቹ  ቦታዎች ውጪ የሌለ ሲሆን፣  አንዳንዶች ደግሞ በሚሸጡበት ቦታ ላይ የእጅ ሳኒታይዘር ለደንበኞቻቸው የሚሰጡም እንዳሉ ቃኝተናል፡፡

በሌላ በኩል ነጋዴዎቹ ምንም ዓይነት የፊት ጭምብል ሳይጠቀሙ ደንበኞቻቸውን ሲያስተናግዱ እንዲሁም ገበያተኞቹም በተመሳሳይ የፊት ጭምብል ሳይጠቀሙ ሲገበያዩ ታዝበናል፡፡ እንቅስቃሴው በአብዛኛው በቸልተኝነት የተሞላ ነው፡፡

የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ንቅናቄን ግምት ውስጥ ያላስገባ እንቅስቃሴ በመዲናዪቱ መበራከቱ ሀቅ ነው፡፡ እንደ ማኅበረሰብ ለወረርሽኙ ያለው ጥንቃቄ እጅግ እየወረደ መምጣቱ እንዳለ ሆኖ፣ በተለይም መንግሥት መግታት (መከላከል) የሚችላቸውን እንቅስቃሴዎች በግድ ተግባራዊ እንዲያደርግ በባዛሮች አካባቢ ያገኘናቸው ነግረውናል፡፡

ለዚህም እንደ ምክንያትነት ያነሱት በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ያላቸው አንድና አንድ አማራጭ ቅድመ መከላል መሆኑን ነው፡፡ ጥንቃቄ ማድረግ የነጋዴው፣ የሸማቹ እንዲሁም የመገበያያ ቦታዎችን የሚያዘጋጀው አካል መሆኑን ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል በመቻሬ ሜዳ መገበያያ ባዛር መግቢያው ላይ የሚደረገው ጥንቃቄ ጥሩ የሚባል ቢሆንም፣ በነጋዴዎችና በተገልጋዮች በኩል የሚታየው ግን አስጊ መሆኑን ሪፖርተር ለማየት ችሏል፡፡

በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ከታኅሣሥ 19 ጀምሮ እስከ ጥር አጋማሽ ድረስ ተከታታይ ሃይማኖታዊ (የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ንግሥ፣ የልደትና የጥምቀት) በዓላት የሚከበርበት በመሆኑ የኮሮና ሥርጭት እንዳይባባስ ሁሉም የበዓሉ አክባሪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

አማኞችና ሁሉም ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ሥፍራ ሲገኙ በተለይም ለአምልኮና ለፀሎት ወደ ቤተ እምነታቸው ሲሄዱና በዚያ ቦታ ሲሆኑ፣ አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው መክሯል፡፡

ኮሮና ቫይረስ ተጨባጭ የጤና ችግር መሆኑን በመረዳት ለአፍታም ቢሆን መዘናጋት እንደማይገባ ጉባዔው አሳስቧል፡፡

 የቫይረሱ ዋነኛ የመተላለፊያ መንገድ አካላዊ ቅርርብና ንክኪ ከመሆኑ አንፃር ሰዎች ርቀታቸውን እንዲጠብቁ፣ ከመጨባበጥና ከንክኪ እንዲቆጠቡና በሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር እንዲተገብሩም ጠይቋል፡፡

ጤና ሚኒስቴርም ለስድስት ወራት ያህል ሥራ ላይ የሚቆይ  አስገዳጅ ድንጋጌዎችን ያካተተ የኮቪድ-19 ቁጥር 30 መመርያ አውጥቷል፡፡ ከድንጋጌዎቹ መካከል የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) ማድረግን፣ እጅን በሳሙናና በውኃ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መታጠብን፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ይገኝበታል፡፡

በመመርያው ሥር የተካተቱትን ድንጋጌዎች በመተግበር ኮቪድ-19 የሚያስከትለውን ጉዳት መከላከልና መቀነስ እንደሚቻልም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡ ነገር ግን መመሪያው ያን ያህል ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ እስከ ታኅሳስ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ 1,800,236 ሰዎች የኮቪድ ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን፣ ከነዚህ 124,264 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ናቸው፡፡ ከበሽታው ያገገሙ 112,096 ሲሆኑ 1,923 ሰዎች ደግሞ መሞታቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...