Thursday, June 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያን ከጂቡቲ የሚያገናኝ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ለመዘርጋት ጨረታ እንደሚወጣ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን ከጂቡቲ የሚያገናኝ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ለመዘርጋት፣ ዓለም አቀፍ ጨረታ እንደሚወጣ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ። 

ሚኒስቴሩ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ የጋዝ ማስተላለፊያ መስመሩ በሶማሌ ክልል የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ለውጭ ገበያ ለማጓጓዝ የሚውል ነው። 

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ አቶ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ የሚዘረጋው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ፣ በውጭ ኩባንያ የሚገነባ ቢሆንም ንብረትነቱም ሆነ የሚተዳደረው በመንግሥት እንደሚሆን ገልጸዋል። 

በሶማሌ ክልል የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ በድሬዳዋ ለሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ በግብዓትነት ለመጠቀም ፕሮጀክት የተቀረፀ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ ያለውን የተፈጥሮ ጋዝ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱን ተናግረዋል።

በዚህ ዕቅድ መሠረትም ፖሊጂሲኤል የተባለ የቻይና ኩባንያና ኒውኤጅ የተባለ ሌላ የእንግሊዝ ኩባንያ የተፈጥሮ ጋዙን የማልማት ሥራ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የእንግሊዝ ኩባንያ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ከሚኒስትሩ የተገኘው መረጃ የሚያመለክት ሲሆን፣ የቻይናው ኩባንያ ፖሊጂሲኤል የተወሰነ መዘግየት እንደሚታይበት ጠቁመዋል።

በሶማሌ ብሔራዊ ክልል በኦጋዴን ቤዚን በካሉብና ሂላላ አካባቢዎች የሚገኘው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት የማልማት ሥራ ላይ የሚገኘው ፖሊጂሲኤል የተሰኘው የቻይና ኩባንያ፣ የተፈጥሮ ጋዙን ወደ ጂቡቲ ለማጓጓዝ የሚያስችል የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ለመገንባት ጥረቶችን ሲያደረግ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ኩባንያው 750 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ወደ ጂቡቲ ለመዘርጋት አቅዶ የነበረ ሲሆን፣ ለዚህም አራት ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያስፈልገው ገልጾ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ የኩባንያው ፍላጎትና ጥረት እንጂ በውል የታሰረ እንዳልነበር ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል። 

ሚኒስትሩ የጋዝ ማስተላለፊያ መስመሩን በመንግሥት እንደሚዘረጋና ጋዙን የሚያለሙ ኩባንያዎች የሚያመርቱትን የተፈጥሮ ጋዝ መንግሥት በሚዘረጋው ሎጂስቲክስ (የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ) ተጠቅመው ለገበያ ማቅረብ እንደሚችሉ ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያና የጂቡቲ መንግሥታት ሁለቱን አገሮች የሚያገናኝ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ለመዘርጋት ያደረጉት ስምምነት፣ ከዓመት በፊት በፓርላማ መፅደቁ ይታወሳል። 

በሶማሌ ክልል የተገኘው የተፈጥሮ ጋዝ በድሬዳዋ ለሚገነቡ የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ግብዓት እንደሚሆን የገለጹት ሚኒስትሩ፣  በድሬዳዋ የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ከተስማማው ኦሲፒ የተባለ የሞሮኮ ኩባንያ በተጨማሪ ሌሎች ስመጥር ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸዋል።

ማዳበሪያ ለማምረት መሠረታዊ ግብዓቶች ከሆኑት መካከል የተፈጥሮ ጋዙ በሶማሌ ክልል፣ ሰፊ የፖታሺየም ክምችት ደግሞ በአፋር ክልል በመኖሩ ድሬዳዋ ለማዳበሪያ ፋብሪካ ማዕከልነት እንደተመረጠች ገልጸዋል። 

በቅርቡም በድሬዳዋ የማዳበሪያ ፋብሪካ ለማቋቋም ፍላጎት ካሳዩ የውጭ ኩባንያዎች እንደሚገለጹና ወደ ስምምነት እንደሚገባም ተናግረዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች