Wednesday, May 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፓርላማው የሰጣቸውን ዕድል አስፈጻሚዎች ስለነፈጓቸው ለኪሳራ ሊዳረጉ መሆናቸውን ተሽከርካሪ አስመጪዎች ተናገሩ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ድጋሚ ዕድል የተሰጠው ከፈቃድ ጋር በተያያዘ እንጂ ላስመጪዎች አይደለም›› ገንዘብ ሚኒስቴር

ከየካቲት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል ከፀደቀው የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ቁጥር 1186/2012 ጋር በተያያዘ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) የሰጣቸውን ዕድል አስፈጻሚ የመንግሥት ተቋማት ስለነፈጓቸው፣ ለኪሳራ ሊዳረጉ መሆናቸውን የኢትዮ ተሽከርካሪ አስመጪዎች ባለቤቶች ማኅበር አስታወቀ፡፡

ማኅበሩ እንደሚናገረው የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ከመፅደቁና በሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት የባንክ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡ ነጋዴዎች (አስመጪዎች)፣ በቀጣይ ስድስት ወራት ሲያስገቡ ኤሳይስ ታክስ የሚሰላባቸው በነባሩ የኤሳይስ ታክስ አዋጅ ቁጥር 307/2002 ድንጋጌዎች መሠረት መሆኑ አዲስ በፀደቀው አዋጅ ቁጥር 1186/2012 አንቀጽ 43(3) መደንገጉን አስታውሷል፡፡

እንደ አስመጪዎቹ ገለጻ አዲሱ አዋጅ በሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት የባንክ ፈቃድ አግኝተው የበርካታ ተሽከርካሪዎችን ግዥ ፈጽመው ለማስገባት በሒደት ላይ እያሉ፣ የዓለም አቀፍ ክስተት የሆነው የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ተከሰተ፡፡ የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ የየብስም ሆነ የአየር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ገደብ ስለተጣለበት፣ ከተለያዩ አገሮች የገዟቸውን ተሽከርካሪዎች ከገዙባቸው ከተሞች ወደ ወደብ ማንቀሳቀስ እንኳን አልቻሉም፡፡ የመርከቦችም እንደፈለጉት አለመገኘት ከወደብ ወደ መሀል አገር ለማንቀሳቀስ ካለመቻላቸውም በተጨማሪ፣ ከነባሩ ወደ አዲሱ አዋጅ ለመሸጋገር ተሰጥቶ የነበረው የስድስት ወራት የመሸጋሪያ ጊዜ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት በመቅረታቸው ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ለታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ደብዳቤ መጻፋቸውን ኢትዮ የተሽከርካሪዎች አስመጪ ባለቤቶች ማኅበር ገልጿል፡፡

ማኅበሩ ያጋጠመውን ውጥረትና አስቸጋሪ ሁኔታ በመግለጽ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ገንዘብ ሚኒስቴር ሁለት ደብዳቤዎችን አከታትሎ መጻፉንም ጠቁሟል፡፡ ማኅበሩ በጻፈው ደብዳቤ እንደገለጸው ተቋማቱ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የተፈጠረበትን አጣብቂኝ ተመልክተው የመሸጋሪያ ጊዜውን እንዲያራዝሙለት መሆኑን አክሏል፡፡

አስመጪዎቹ ግምታቸው ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን የገዙት ቤታቸውንና ሌሎች ንብረቶቻቸውን አስይዘው ከባንክ ተበድረው መሆኑን የጠቆመው ማኅበሩ በየቀኑ እየቆጠረ ያለው የባንክ ወለድ ራሳቸውን አዙሮት እያለ፣ በተገኘው አጋጣሚ ወደ አገር ውስጥ ያስገቧቸውና በአገሪቱ ወደቦች የሚገኙትን ተሽከርካሪዎች፣ የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን ‹‹መቀረፅ ያለባቸው በአዲሱ አዋጅ ነው›› በማለት ለጨረታ እንዳቀረበባቸውም (አዳማ ጉምሩክ) አስረድቷል፡፡ የያዟቸውን ሠራተኞችና የሚያስተዳድሯቸው ቤተሰቦቻቸውን ላለመበተን የመንግሥትን ቀና ምላሽ እየጠበቁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ መንግሥትም ከሌላው ማኅበረሰብ የተለየ ውለታ እንዲያደርግላቸው ሳይሆን የዓለም ክስተት የሆነው ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በፈጠረው ችግርና ከእነሱም አቅም በላይ መሆኑን ተገንዝቦ ለጨረታ የቀረቡትን ተሽከርካሪዎች እንዲያስቆምላቸው፣ ከአዲሱ  አዋጅ በፊት የፈጸሙት ግዥ መሆኑን በመመልከት በነባሩ አዋጅ መክፈል ያለባቸውን ኤክሳይስ ታክስ እንዲከፍሉና ተሽከርካሪዎቻቸውን እንዲረከቡ አቅጣጫ (ትዕዛዝ) እንዲሰጥላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢ በአቶ ጴጥሮስ ወልደ ሰንበት ፊርማ ወጪ በተደረገ ደብዳቤ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር የአስመጪዎችን ችግር መርምሮ ምላሽ እንዲሰጥ ማሳሰቢያ ደርሶት እንደነበር ማኅበሩ አስታውሷል፡፡

ቦርዱ ለሚኒስቴሩ በጻፈለት ደብዳቤ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ተመልክቶና መንግሥት ለሌሎች ዘርፎች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን በማስታወስ ለኢትዮ ተሽከርካሪዎች አስመጪ ባለሀብቶች ማኅበርም ተገቢ ምላሽ በአሥር ቀናት ውስጥ እንዲሰጥና ምላሹን እንዲያሳውቀው ቢያሳስበውም፣ ‹‹አኔን አይመለከተኝም›› ከማለት ባለፈ መፍትሔ ሊሰጣቸው እንዳልቻለም ተናግረዋል፡፡

ገቢዎች ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን እንደማይመለከታቸውና የሚመለከተው ገንዘብ ሚኒስቴር መሆኑን በተደጋጋሚ በመግለጻቸው፣ ማኅበሩና አባላቱ ምልልሳቸውን ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ማድረጋቸውንም አስረድተዋል፡፡

ማኅበሩ ለገንዘብ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ እንደገለጸው በኮቪድ-19 ምክንያት በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ እንደ ልብ መንቀሳቀስ ባለመቻሉና የአየር ትራንስፖርት በመታገዱ፣ የገዟቸውን ተሽከርካሪዎች ከከተሞች ወደ ወደብ ማንቀሳቀስ ባለመቻላቸው  ወደብ ላይ የደረሱትንም መርከቦች በወቅቱ ባለመገኘታቸው መጫን ባለመቻላቸው፣ መዳረሻ ወደብ (ጂቡቲ ወደብ) ላይ የደረሱትንም ማምጣት ባለመቻላቸው በአገሪቱ በተፈጠረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ምክንያት ገበያቸው በመቀዛቀዙ የጉምሩክን ቀረጥ በወቅቱ ሊከፍሉ ባለመቻላቸው፣ ተሽከርካሪዎቹን በወቅቱ አገር ውስጥ ማስገባት አለመቻላውን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያመጣው ቀውስ መሆኑን መንግሥትም ስለሚረዳ፣ ሚኒስቴሩ ተረድቷቸው አገር ውስጥ የገቡ፣ በተለያዩ ወደቦች የሚገኙ ተሽከርካሪዎችን በነባሩ አዋጅ የሚተመንባቸውን ኤክሳይስ ታክስ እንዲከፍሉና ከፍተኛ የወደብ ኪራይ (ዲመሬጅ) እየቆጠረባቸው የሚገኙ ተሽከርካሪዎችን እንዲያስገቡ መጠየቃቸውን ሰነዶች ያሳረዳሉ፡፡

ገንዘብ ሚኒስቴር በሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ መነሻ በኩል በሰጣቸው አጭር ምላሽ አዲሱ አዋጅ ከፀናበት ቀን በፊት በተገኘ የባንክ ፈቃድ ግዥ የፈጸሙ በስድስት ወራት የመሸጋገሪያ ጊዜ ውስጥ ሲያስገቡ በነባሩ ሕግ እንደሚቀረጡ ተናግሮ፣ ከመሸጋገሪያ ጊዜው ውጭ ለማራዘም ሚኒስቴሩ በሕግ ሥልጣን እንዳልተሰጠው በመግለጽ አቤቱታቸውን ሳይቀበለው መቅረቱንም ተናግረዋል፡፡ ሁለም ዜጋ የሚገዛበትን ሕግ የሚያወጣው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰጣቸውን ዕድል አስፈጻሚው በመንፈጉ እነሱን ለኪሳራ፣ ሠራተኞቻቸውን ለሥራ አጥነትና ቤተሰቦቻቸውን ለጎዳና ሊዳረጉ ጫፍ ላይ በመድረሳቸው መንግሥትና የሚመለከተው አካል እንዲደርስላቸው ተማፅነዋል፡፡

የኢትዮ ተሽከርካሪዎች አስመጪ ባለቤቶች ማኅበር ያቀረበውን አቤቱታ በሚመለከት ሪፖርተር ገንዘብ ሚኒስቴርን ጠይቆ አጭር ምላሽ ተሰጥቶታል፡፡ የሚኒስቴሩ ሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሰመሪታ ሰዋሰው እንደገለጹት አስመጪዎቹ በተሰጣቸው ጊዜ ማስገባት ነበረባቸው፡፡ ፓርላማው ሁለተኛ ዕድል የሰጠው ላስመጪዎች ሳይሆን ከላይሰንስ (ፈቃድ) ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች እንጂ ላስመጪዎች አይደለም፡፡ ‹‹ተሽከርካሪ አስመጪዎች ሌሎች አስመጪዎች እንደሚያደርጉት ከፍለው ማስገባት አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች