በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተከሰቶ የነበረው የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ በተያዘው ዓመት ይገኛል ከተባለው አጠቃላይ 384 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ውስጥ፣ እስከ አንድ በመቶ ወይም 3.8 ሚሊዮን ኩንታል ያህል ቅናሽ ሊያመጣ እንደሚችል የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የአንበጣ መንጋው በ25 ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እስካሁን ያደረሰው ጉዳት የመጀመሪያ ግምታዊ ሥሌት እንደሆነ የገለጹት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን፣ ከመኸር ሰብል ምርት በተጨማሪ በእንስሳት መኖ ላይም ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ አስረድተዋል።
በመጀመሪያ ዙር የአንበጣ መንጋው ጉዳት ያደረሰባቸው አካባቢዎች አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ሶማሌ ክልሎችና የድሬዳዋ አስተዳደር እንደነበሩ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ወረርሽኙ መከሰቱን ጠቁመዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት በመጀመርያ ዙር ተከስቶ የነበረውን የአንበጣ መንጋ ወረርሽን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጣር የተቻለ ቢሆንም፣ በሁለተኛ ዙር በሶማሌ ክልል ድንበር አካባቢ ሠፍሮ የነበረውና በኬንያ በኩል በተለይም በደቡብ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 18 ዞኖች ተከስቷል ብለዋል።
በእነዚህ በተጠቁሱት ሥፍራዎች 195 ሺሕ ሔክታር የአንበጣ ወረርሽኝ ያረፈበትን ሰብል ጨምሮ፣ 13 የርጭትና የዳሰሳ አውሮፕላኖች በመጠቀም ከ395 ሺሕ ሔክታር በላይ በአዝዕርትና በሰብል የተሸፈነ መሬት ላይ ኬሚካል መረጨቱን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከ2014 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የስንዴ ምርት በማቆም፣ በአገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን እየተሠራ ያለውን ሥራ የአንበጣ መንጋ እንዳያስተጓጉል በከፍተኛ ሁኔታ እየተሠራ እንደሆነም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
የመስኖ ልማትን ለመደገፍ የሚያግዙ የግብርና ማሽነሪዎችን መንግሥት ከውጭ እያመጣ እንደሆነና በአገር ውስጥም ዘመናዊ ማሽነሪዎች ማምረት መጀመሩን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ከ12 ሺሕ በላይ አርሶ አደሮች ስንዴ በማምረት ላይ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
በተያዘው ዓመት ከ260 ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት በሁለት ዙር ለማልማት ታቅዶ፣ 90 ሺሕ ሔክታር የሚጠጋ መሬት ስንዴ በመብቀል ላይ እንደሆነም አስታውቀዋል።
ስንዴን በመስኖ ለማልማት በሚፈለገው መጠን አስፈላጊ የሆኑ መሣሪያዎችም እየቀረቡ እንደሆነና በተያዘው ዓመት አገሪቱ በየዓመቱ ከምታስገባው ወደ 20 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ስንዴ ውስጥ፣ ግማሹን በአገር ውስጥ የማምረት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደሆነ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።