በተለምዶ ሰማያዊ ላዳ ታክሲዎች የሚባሉ ተሽከርካሪዎች፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ በአዲስ እንደሚተኩ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ 10,500 የላዳ ታክሲዎች ባለንብረቶች መኖራቸውንና አስተዳደሩ ባመቸላቸው ዕድል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተገኘ የብድር አገልግሎት መሠረት የሚቀየሩ መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በድሉ ሌሊሳ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የብድር አገልግሎቱ የመጀመርያ ክፍያ 20 በመቶ መሆኑን የገለጹት አቶ በድሉ፣ ጠቅላላ ክፍያው በአምስት ዓመታት ውስጥ እንዲያጠናቅቁ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
ባለንብረቶቹ በአንድ ዓመት ውስጥ የሚቀይሩት አዲስ መኪና ዓይነቶች በአገር ውስጥ የሚገጣጠሙ ተሽከርካሪዎች መሆናቸውን ምክትል ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
አቶ በድሉ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን ገጽታ ለማስተካከል የላዳ ታክሲዎችን በዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን ለመቀየር ነው፡፡
ከታኅሳስ 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዝግ የቁጠባ ደብተር በአምስት ቅርንጫፎች እንዲከፍቱ የሚያደርግ ሲሆን፣ የቅየራው የመጀመርያው ምዕራፍ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበባ ላዳ ታክሲዎች 185 ማኅበራት ያሏቸው ሲሆን፣ ማኅበራቱ ተወካዮች ሰብሳቢ አቶ ቢኒያም መለስ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አጠቃላይ የብድር ስምምነቱ የመኪናው ዓይነት ከታወቀ በኋላ የሚደረግ ይሆናል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ቃል በገቡት መሠረት ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን የገለጹት አቶ ቢንያም፣ የወለዱን ምጣኔን በተመለከተ 9.5 በመቶ መሠረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሚቀየሩት ተሽከርካሪዎች በላዳ ታክሲ አሽከርካሪዎች ምርጫ መሠረት 80 በመቶ የሚሆኑት ባለ አምስት ወንበር እንደሚሆኑና 20 በመቶዎቹ ደግሞ ባለ ሰባት ወንበር መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የላዳ ታክሲዎችን በአዲስ የመተካት እንቅስቃሴው በቅርቡ የሚጀመር ሲሆን አዲስ የሚተካው ተሽከርካሪም ዘመናዊና ለከተማ ውበት ማራኪ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡