በኢትዮጵያ ለንግድ ትርዒት ተብሎ የታሰበ አመቺ መሠረተ ልማት ባለመኖሩ የንግድ ዘርፉ ላይ ፈተና መደቀኑን የአዲስ አበባ የንግድና የዘርፉ ማኅበራት ምክር ቤት አስታወቀ፡፡
ምክር ቤቱም ይህንን ያለው ታኅሳስ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረገው የውይይት መድረክ ነው፡፡ በወቅቱም በተለይ የኮሮና ወረርሽኝን ተከላክሎ ሊያሠራ የሚችል የቦታ ይዞታ ባለመኖሩ፣ ዘርፉ ከውጭ አገሮች ማግኘት የሚገባውን ገቢ እያጣ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ እንደገለጹት፣ በንግድ ሥራ ማስፋፊያ ዘርፉ ላይ ያለው የማስተዋወቅ ተግባርና የዕውቀት ውስንነት እንዲሁም ወጥ የሆነ የሕግ መመርያ አለመኖሩ በዘርፉ ላይ ትልቅ ችግር እየፈጠረ ይገኛል፡፡
የንግድ ትርዒት ሰፋ ያለ ሥራ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ መንግሥት ትኩረት በመስጠት የቦታ ይዞታዎችን በማመቻቸትና የንግድ ዘርፉን በማሳደግ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚጠበቅበት አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡
የንግድ ትርዒቶች ለብዙ ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ እንደሆነና ኢዮጵያም ካለችበት ኢኮኖሚያዊ ዝቅተት ወጥታ ወደፊት አንድ ዕርምጃ የምታድግበት ኢንዱስትሪ መሆኑን ዋና ጸሐፊው አስረድተዋል፡፡
የንግድ ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የተለያዩ መዋቅሮችን በመዘርጋት እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን አስታውሰው በዘርፉ ላይ ትልቅ የቤት ሥራ እንደሚገጥማቸው ጠቁመዋል፡፡
የአፍሪካ የንግድ ትርዒት ፓርትነር ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አክሊለ በለጠ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን በንግድ ትርዒት ላይ በትንሹ ልታገኝ የሚገባትን 2.9 ሚሊዮን ዶላር በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት አጥታለች፡፡
በወረርሽኙ ምክንያት 700 የሚሆኑ አዘጋጆች የንግድ ትርዒቱን ከማዘጋጀት መቆጠባቸውንና ለትልቅ ኪሳራ መዳረጋቸውን በተለይም በሥራቸው የሚገኙ ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው መፈናቀላቸውን አቶ አክሊለ አክለዋል፡፡
መንግሥት እንደ ሌሎች የኢንዱስትሪ ዘርፎች ለንግድ ትርዒቶች ድጋፍ ባለመስጠቱ በዘርፉ ያሉ ባለሙዎች ለኪሳራ መዳረጋቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
የንግድ ሥራን ውጤታማ ለማድረግ አንዱ የሆነው የንግድ ትርዒት በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ማጥ ውስጥ በመግባቱ፣ በዘርፉ ላይ ተዋናይ የሆኑ አዘጋጆች ትልቅ ችግር እንደገጠማቸው በውይይቱ ላይ ተገልጿል፡፡