Friday, June 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ወጋገን ባንክ 1.1 ቢሊዮን ብር አተረፈ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ 16 የግል ባንኮች አንዱ የሆነው ወጋገን ባንክ፣ በተጠናቀቀው 2012 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 1.1 ቢሊዮን ብር ማትረፍ መቻሉን አስታወቀ፡፡

 ባንኩ ታኅሳስ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. በሒልተን አዲስ አበባ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ፣ በባንኩ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተፈራ ሞላ በኩል የቀረበው ሪፖርት በሒሳብ ዓመቱ የተለያዩ ተግዳሮቶች የነበሩበት ቢሆንም ባላቸው የትርፍ ምጣኔውን በማሳደግ የሒሳብ ዓመቱ መጠናቀቁን አሳይቷል፡፡  

‹‹ምንም እንኳን በበጀት ዓመቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ላይ በፈጠረው መቀዛቀዝ ምክንያት በብድር አከፋፈልና አሰባሰብ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ተከትሎ የብድር ወለድ ምጣኔ ቅናሽ የተደረገበት ቢሆንም፣ ባንኩ ከታክስ በፊት 1.1 ቢሊዮን ብር ትርፍ መዝግቧል›› ያሉት ምክትል የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢው፣ ይህ ትርፍ ከ2011 የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ47 በመቶ ዕድገት ያሳየ መሆኑንና ባንኩ በ2012 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ያስመዘገበው ትርፍ 342 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡

የባንኩን የ2012 የሒሳብ ዓመት ክንውን በተመለከተ የቀረበው ሪፖርት፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ባንኩ የሰበሰበው የደንበኞች ተቀማጭ ገንዘብ መጠን በ2011 የሒሳብ ዓመት ከነበረው የ28 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ወደ 30.1 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በባንኩ ደንበኞች የተከፈቱ የቁጠባ ሒሳቦች ብዛትም የ38 በመቶ ጭማሪ 1.8 ሚሊዮን ብር መድረሱን ምክትል ቦርድ ሰብሳቢው ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ባንኩ በተለያዩ የብድር ዘርፎች ለደንበኞች የሰጠው አጠቃላይ የብድር መጠንም በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ 23.7 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ከ2011 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸም 16.5 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር፣ የ44 በመቶ ጭማሪ ስለማሳየቱ የባንኩ መረጃ አመልክቷል፡፡

ከባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው፣ በሒሳብ ዓመቱ ከተሰጠው ብድር  ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው የወጪ ንግድ ነው፡፡

በሒሳብ ዓመቱ ከጠቅላላ ብድር ውስጥ የወጪ ንግድ ዘርፍ 31 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ሲይዝ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ለአገር ውስጥ ንግድ የሰጠው ብድር ነው፡፡ ይህም 19 በመቶ ድርሻ ያለው ነው፡፡

የወጋገን ባንክ የተከፈለ ካፒታል 2.9 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ጠቅላላ ካፒታሉም ወደ 5.1 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡ በተያያዘም የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 38.2 ቢሊዮን ብር መድረሱም ተገልጿል፡፡  

በተመሳሳይ ባንኩ በኤሌክትሮኒክ ባንኪንግ አማካይነት ለደንበኞቹ የሚሰጠውን አገልግሎት ተደራሽነት ለማሳደግ፣ በመላው ኢትዮጵያ 297 የኤቲኤምና 273 የክፍያ መፈጸሚያ (ፖስ) ማሽኖችን በመትከል እንዲሁም የሞባይል፣ የኢንተርኔትና የወኪል ባንክ አገልግሎቶችን በማስፋፋት ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡

ባንኩ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንጻርም በተጠናቀቀው 2012 በጀት ዓመት መንግሥት ስላከናወናቸው ተግባራት በሪፖርቱ ያካተተ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት በሒሳት ዓመቱ የሚካሄዱ የልማት ሥራዎችን ለመደገፍና የኮሮና በሽታን ለመከላከል የሚደረገውን አገር አቀፍ ጥረት ለማገዝ ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉ አስታውቋል፡፡ የወጋገን ባንክ ባለአክሲዮኖች ቁጥር 3,998 የደረሰ ሲሆን የባንኩ ሠራተኞች ቁጥር ባንኩን ወክለው በሚሠሩ ድርጅቶች ስር የሚተዳደሩትን ጨምሮ 7,709 መድረሱ ተገልጿል፡፡

 በ2012 በጀት ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች 43 ተጨማሪ ቅርንጫፎችን በመክፈት አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 383 አድርሷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የወጋገን ባንክ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ መንግሥተአብ ገብረ ኪዳንን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የቦርድ አባላት ያልተገኙበት መሆኑ ታውቋል፡፡ በዕለቱ ከአሥሩ ዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ውስጥ አራቱ ብቻ መገኘታቸው የተገለጸ ሲሆን ቀሪዎቹ የቦርድ አባላት በተለያዩ ምክንያቶች ያልተገኙ ቢሆንም፣ የንግድ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ጠቅላላ ጉባዔው ተካሂዷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የምርጫ  ሕግ በሚፈቅደው መሠረትም ባለፈው ዓመት በተመረጡ አስመራጮች ኮሚቴ መሠረት የሥራ ጊዜያቸውን ባጠናቀቁ የቦርድ አባላት ምትክ አዲስ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ ተካሂዷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች