Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሕገወጥ ዕርድ ምክንያት የከተማ አስተዳደሩ በዓመት 1.5 ቢሊዮን ብር እንደሚያጣ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሕገወጦች ተደራጅተው በሚያከናውኑት የቁም እንስሳት ዕርድ፣ የከተማ አስተዳደሩ በየዓመቱ 1.5 ቢሊዮን እንደሚያጣ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት አስታወቀ፡፡

ድርጅቱ ይህን ያስታወቀው፣ ‹‹በበዓል ወቅት ሕገወጥ እንስሳት ዕርድን እንከላከል›› በሚል ርዕስ ማክሰኞ ታኅሳስ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት የመሰብሰቢ አዳራሽ ለመገናኛ ብዙኃን የጋዜጣዊ መግለጫ በተሰጠበት ወቅት ነው፡፡

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ዋና ሥራ አስኪጅ አቶ ሰይድ እንድሪስ በመግለጫው ወቅት እንደተናገሩት፣ በከተማዋ ከሕገወጥ ዕርድና ከሥጋ ዝውውር ጋር በተያያዘ የቆየ ችግር አለ፡፡ ሦስት መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን ድርጅቱ እንደለየም ገልጸዋል፡፡ አንደኛው ከግብር ሥወራ ጋር የሚገናኝ ሲሆን፣ የእንስሳት ንግድ ከቁርጥ ግብር ጋር የተገናኘ በመሆኑ፣ ፍትሐዊ ገቢ መንግሥት እንዳያገኝ አድርጎታል፡፡ ሁለተኛው የቄራዎች አገልግሎት በየአካባቢው ተደራሽ አለመሆን ሲሆን፣ ሦስተኛው የኅብረተሰቡ በሕገወጥ መንገድ የታረዱ ከብቶችን ሥጋ የመጠቀም ልምድ ከፍተኛ መሆኑ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በሕገወጥ መንገድ የሚታረዱ ሥጋዎችን ለመቆጣጠር የተለያዩ የክትትልና የጥናት ሥራዎች ተከናውነዋል ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ዘመናዊ ቄራ ለመገንባት የበጀት ድጋፍ ካደረገለት የፈረንሣይ ልማት ድርጅት ጋር የአዋጭነት ጥናት እንዳደረገ ጠቁመዋል፡፡ በጥናቱም እንደታየው ከ90 እስከ 96 በመቶ በግና ፍየል በሕገወጥ መንገድ እየታረዱ ለገበያ እንደሚቀርቡ፣ ከ25 እስከ 30 በመቶ ትልልቅ እንስሳት እንዲሁ በሕገወጥ ዕርድ ለገበያ እንደሚቅርቡ ጥናቱ አመላክቷል ብለዋል፡፡ እነዚህ ሕገወጥ ተግባራት ወደ መደበኛው አገልግሎት ቢመጡ፣ ከተማዋ ከፍተኛ ገቢ መሰብሰብ እንደምትችል በጥናቱ ተገልጿል ሲሉ አቶ ሰይድ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዓመት የአርሶ አደርና ግብርና ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት፣ እንዲሁም የሰላምና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ዝርዝር ጥናት እንዳደረጉ የገለጹት አቶ ሰይድ፣ ሕገወጥ ማረጃ ቦታዎች የት ናቸው? መቼ ነው የሚታረድባቸው? እንዴትስ ነው ተጓጉዘው የሚሠራጩት? የትኞቹ ልኳንዳ ቤቶች ናቸው ተቀባዮቹ? የሚለው በግልጽ ተለይተዋል ብለዋል፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እስከ አራትና አምስት ኮከብ ሆቴሎች ድረስ የሕገወጥ ሥጋ ተጠቃሚ ናቸው ያሉት አቶ ሰይድ፣ ትልቅ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ሊከናወን ይገባል ብለዋል፡፡

በተለዩት የማረጃ፣ የማጓጓዣና የመሸጫ ቦታዎች ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመተባበር ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጎ ከ138 ልኳንዳ ቤቶችና ሆቴሎች 21,000 ኪሎ ግራም ሥጋ፣ 450 በግና ፍየሎች በየጉራንጉር ለዕርድ እንደተዘጋጁ ተይዘዋል ተብሏል፡፡

በሕገወጥ ዕርድ ለገበያ የሚቀርብ ሥጋ እንደ አባ ሰንጋ ላሉ ወዲያውኑ ለሞት የሚዳርጉ በሽታዎቸ ማጋለጡ እንዳለ ሆኖ፣ ከዘርፉ የሚገኝ የትርፍ ግብር፣ ተጨማሪ እሴት ታክስና የሌሎች ተረፈ ምርቶች ገቢ የከተማ አስተዳደሩ እንዳያገኝ አድርጓል የሚሉት አቶ ሰይድ፣ አሁን ሕገወጥ አራጆቹ በመሣሪያና በፋይናንስ በመደራጀት ጭምር ለከተማው ሥጋት የሆኑበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡

በቀጣይ ከሰላምና ፀጥታ ቢሮ፣ ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮና ከከተማው ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመሆን የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ሁሉንም ሕገወጥ ድርጊቶች በርካቶች የሚከናወኑባቸው ቦታዎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ የሚገልጹት የዋና ሥራ አስኪያጁ፣ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በእነዚህ ድርጊቶች ላይ የሚገኙ ግለሰቦች ቀድመው ከችግሩ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡       

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች