በሕጋዊ አሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ስም በሕገወጥ መንገድ ተቀናጅተው ከሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር፣ የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረሩ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረያ የሚሠሩ የኢሚግሬሽን ኃላፊዎችና ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ፡፡
በኤጀንሲዎች ስም በሕገወጥ መንገድ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱት ግለሰቦች (ደላሎች) ሕጋዊ መስፈርቶችን አሟልተው ከአገር መውጣት ካልቻሉ ዜጎች ከፍተኛ ገንዘብ በመቀበልና በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቅርንጫፍ ከሚሠሩ የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ አመራሮችና ሠራተኞች ጋር በመካፈል፣ ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ከአገር እንዲወጡ ሲያደርጉ መቆየታቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ያወጣው መግለጫ ያስረዳል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከትናንት በስቲያ ታኅሳስ 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋር በጋራ ባደረገው የተቀናጀ ክትትል፣ በወንጀል ድርጊቱ በመሳተፍ የተጠረጠሩ 21 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ የኢሚግሬሽን አመራሮችና ሠራተኞች በሕገወጥ መንግድ በአሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ሥም ተደራጅተው ከሚንቀሳቀሱ ሕገወጦች ጋር በጥቅም ተሳስረው ሲሠሩ መቆየታቸውን የሚጠቁሙ መረጃዎችን አግኝቷል፡፡ ለጥቅም ትስስሩ ከፍተኛ ኔትወርክ እንዳላቸው ጠቁሞ፣ በሦስት ተጠርጣሪዎች ቤት ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻም ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ፣ የተለያዩ የባንክ ደብተሮችና ሰነዶች መገኘታቸውን ገልጿል፡፡ በኤጀንሲዎቹ ስም ለሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ቤት የሌሎች ሰባት ሰዎች ፓስፖርቶች መያዛቸውንም አክሏል፡፡ በአጠቃላይ በተጠርጠሪዎች ቤት በተደረገ ፍተሻ 37 የባንክ ደብተሮችና ለሕገወጥ ሥራቸው የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ ቁሳቁሶች መያዛቸውንም ጠቁሟል፡፡ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ውስጥ 16ቱ ተጠርጣሪዎች የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ አመራሮችና ሠራተኞች መሆናቸውን፣ አምስቱ ደግሞ የአሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ሠራተኞች መሆናቸውንም ተናግሯል፡፡ ቀሪዎቹ ተጠርጣሪዎች በኤጀንሲዎቹ ስም ሕገወጥ ተግባራት ሲፈጽሙ የነበሩ መሆናቸውንም ገልጿል፡፡