Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጫ ከቶኪዮ ኦሊምፒክ በኋላ እንዲደረግ ወሰነ

የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጫ ከቶኪዮ ኦሊምፒክ በኋላ እንዲደረግ ወሰነ

ቀን:

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በኮቪድ-19 ምክንያት ያራዘመውን ምርጫ ከቶኪዮ ኦሊምፒክ መልስ እንዲካሄድ ወሰነ፡፡ አገሪቱ በስፖርቱ ዘርፍ ሊኖራት የሚገባውን የተወዳዳሪነት አቅም ማጎልበት የሁሉም ድርሻ ሊሆን እንደሚገባ በጉባዔው ተመልክቷል፡፡

ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው እሑድ ታኅሣሥ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በሐዋሳ የሲዳማ ባህል ማዕከል ባካሄደው መደበኛ ጉባዔ፣ ኢትዮጵያ በሮም ኦሊምፒክ በአበበ ቢቂላ ባዶ እግር የጀመረውችን አሸናፊነት ለማስቀጠል ትውልዱ ላይ መሥራት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ሌሎች አገሮች ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን እንድታገኝ ሁሉም በትብብር መንፈስ የስፖርቱን ተፈጥሯዊ ቦታ ጠብቆ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል ተብሏል፡፡

ጉባዔው ኢትዮጵያ የአኖካን ጉባዔ ባስተናገደችበት ማግስት ከመደረጉም በላይ፣ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ለቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ፣ ከ120 በላይ አትሌቶች እንዲመረጡ አድርጎ ዝግጅት በጀመሩበት ወቅት መሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ ልዩ እንደሚያደርገውም ተነግሯል፡፡ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር)፣ ጉባዔው በስፖርት ምክር ቤቱ በተቀመጡ ውሳኔዎች መሠረት በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ በጥልቀት መክሮ አቅጣጫዎችን እንዲያስቀምጥ በመክፈቻ ንግግራቸው ጠይቀዋል፡፡

ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ለክልሎችና ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህ ጉባዔ ኢትዮጵያ በቶኪዮ 2020 የአበበ ቢቂላን ገድል ለመድገም ዝግጅት እያደረገች በምትገኝበት ወቅት መሆኑ ታሳቢ ሊደረግ ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በዚህ የአሊምፒክ መድረክ አሸናፊ መሆን እንደማይቻል ጭምር አሳስበዋል፡፡

ስፖርት ማኅበራዊ ትስስርን በእጅጉ የሚፈጥር መሆኑን በመግለጽ፣ የኦሊምፒክ መርሆዎችን ታሳቢ በማድረግ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ፕሬዚዳንት፣ በጉባዔው አባላት አልፎ አልፎ የሚነሱ አስተያየቶች የዓለም አቀፍ ተቋማትን መርህና አሠራርን የተከተሉ መሆን እንደሚገባቸው ማሳሰባቸው አልቀረም፡፡

ኦሊምፒክን ጨምሮ በአገሪቱ በሚደረጉ ተመሳሳይ ጉባዔዎች ለኢትዮጵያውያን አብሮነትም ሆነ ለስፖርቱ ዕድገት የማይበጁ አስተያየቶች የሚደመጥበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ 45ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይም ሲስተዋል ነበር፡፡ ይህንኑ የተረዱ የሚመስሉት የሲዳማ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ደስታ ሊዳሞ፣ ‹‹ስፖርት ለሰላም፣ ለወዳጅነት፣ ለአንድነት፣ ለወንድማማችነትና ለብልፅግና ትልቅ መሣሪያ መሆኑን ከግምት በማስገባት፣ ጉባዔውም በዚህ ልክ አስቦ ኢትዮጵያ በስፖርት አሸናፊነቷን በአትሌት አበበ ቢቂላ የጀመረችውን ገድልና የአሸናፊነት መንፈስ በቅብብሎሽ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በብስለትና በዕውቀት መነጋገር ይኖርበታል፤›› በማለት በስፖርቱ ዘርፍ የሚስተዋለው የአሠራር ክፍተት እንዲሁም አለመተማመን መስተካከል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የስፖርት ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) በበኩላቸው ለጉባዔው ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፣ ጉባዔው ለስፖርቱ ዕድገት የሚበጅ ሐሳብ አምጪ ሊሆን ይገባል፡፡ በተጨማሪም የኦሊምፒክ ስፖርት ዋና ግብ ሕዝቦች በጋራ በአንድ መድረክ የሚገናኙበት ታላቅ መድረክ እንደሆነም ተናግረው፣ ለዚህ ኢትዮጵያ በሚገባት ልክ መዘጋጀት እንደሚገባት ጭምር አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ይህን ተገንዝባ አባል ሆና ረዥም ዓመታትን እንዳስቆጠረች በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በተለይም በስፖርቱ አኩሪ ድሎች መመዝገባቸው በጉባዔው ከተነሱት አስተያየቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ይህን በሌሎች ስፖርቶች መድገም ለምን እንዳልተቻለ መለስ ብሎ ራስን መጠየቅ እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ፣ ቀደም ሲል ስፖርቱን በበላይነት ሲመሩ ቆይተው በአሁኑ ወቅት በሌላ ክልላዊ መንግሥታዊ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ አመራሮች በጉባዔው ፊት ቀርበው ዕውቅና የተሰጣቸው ናቸው፡፡

ከእነዚህ አመራሮች መካከል የቀድሞ ወጣቶችና ስፖርት በኋላም የስፖርት ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ርስቱ ይርዳውና በወቅቱ ምክትላቸው የነበሩት አቶ ተስፋዬ ይገዙና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...