የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ሞዴስና የሕፃናት ንፅህና መጠበቂያ (ዳይፐር) ላይ የቀረጥና የታክስ ማሻሻያ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ገቢ ምርቶች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ለማስቻልና የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች እንዲበረታቱ በመሠረታዊ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች በተለይም በወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ምርቶች ላይ የቀረጥና ታክስ ማሻሻያ ማድረጉን ያስታወቀው ሚኒስቴሩ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ከውጭ ሲገቡ ቀድሞ ከነበረው ከፍተኛ የታክስ ምጣኔ 30 ከመቶ ዝቅ ተደርጎ ታክሱ 10 በመቶ ብቻ እንዲሆን መወሰኑን ገልጿል፡፡
የቀረጥና የታክስ ማሻሻያ የተደረገው ሴት ተማሪዎች በንፅህና መጠበቂያ (ሞዴስ) ማጣት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡና በሥራ ላይ ያሉ ሴቶችን የሥነ ልቦና ጭንቀት እንዳይደርስባቸው ለማድረግ ያለመ መሆኑን ተገልጿል፡፡
የአገር ውስጥ ምርትን በማጎልበት፣ የዋጋ ቅነሳ እንዲኖር ማስቻል፣ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ችግር ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመፍታትና ጥራት ያላቸው ምርቶች እንዲመረቱ በማድረግ ተደራሽ እንዲሆን ነውም ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ የሴቶች የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ (ሞዴስ) አምራች ኢንዱስትሪዎች ስምንት መሆናቸውን ገንዘብ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያሰፈረው መረጃ ያሳያል፡፡