ኮቪድ-19 ዓለምን እያሸበረ፣ የሰው ሕይወትን እየቀጠፈና የሥርጭት አድማሱን እያሰፋ በመጣበት ዘመን አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ብቅ ሲሉ ታይተዋል፡፡ ከእነዚህም ፈጠራዎች መካከል ከንክኪ ነፃ የሆነ የእጅ መታጠቢያ ይገኝበታል፡፡ ሳኒታይዘር፣ ፌስ ማስክ (የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ) እና ፌስ ሺልድ (የፊት መሸፈኛ) ከፈጠራ ሥራዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ፌስ ማስክና ፌስ ሺልድ እጅን በሳሙና ከመታጠብ አሊያም በአልኮልና ሳኒታይዘር ከማፅዳት ጎን ለጎን ኮቪድ-19ን ለመከላከል ወሳኝ ናቸው፡፡ ሆኖም በተለይ ለሕክምና ባለሙያዎች ፌስ ሺልድ ወሳኝ ነው፡፡ ለቫይረሱ ካላቸው ተጋላጭነት አንፃር መላ አካላቸውን መሸፈን አላባቸው፡፡ ለዚህም ተመራጩ ፌስ ሺልድ ነው፡፡ ፌስ ሺልድ ኮቪድ ለበረታባቸው ያደጉ አገሮች ብርቅ ባይሆንም፣ በኢትዮጵያ በተለይ ቫይረሱ በገባባቸው የመጀመርያዎቹ ጊዜያት ብርቅ ነበር፡፡ የጤና ባለሙያዎች አልተሟላልንም ከሚሉት የኮቪድ መከላከያ አልባሳትም አንዱ ነበር፡፡ አሁን ግን ፌስ ሺልድ በአገር ውስጥ የሠሩ አሉ፡፡ በእንደነዚህ ዓይነት ሥራዎች ከተሠማሩትም መካከል ቢሊ ግርማ አንዷ ናት፡፡ ቢሊ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ናት፡፡ የፈጠራ ሥራዎቿን አስመልክቶ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯታል፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ ፈጠራ ሥራው እንዴት ገባሽ?
ቢሊ፡- በኮቪድ-19 ሳቢያ ትምህርት ለአሥር ወራት ያህል ተቋርጦ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ቤት ውስጥ እጅና እግርን አጣጥፎ መቀመጥ እንደ መስነፍ ነው፡፡ አንድ ሰው ስንፍና ከተጫነው ደግሞ የማሰብ ችሎታው እየወረደ ይሄዳል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ ችግር ለመላቀቅ አንድ ቋሚ የሆነ ቁም ነገር መሥራት አለብኝ ብዬ ተነሳሳሁ፡፡ ትኩረቴንም በፌስ ሺልድ ላይ አደረኩ፡፡ ለትኩረቴም መነሻ የሆነኝ የሕክምና ተማሪ እንደ መሆኔ መጠን በኮቪድ-19 ሕክምና ላይ የተመደቡ የጤና ባለሙያዎች የሚያደርጉት አስተዋጽኦና ራሳቸውን ከቫይረሱ ለመከላከል ያለው ክፍተት ሁል ጊዜ በአዕምሮዬ መመላለሱ ነው፡፡ በየሕክምና ተቋማት የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ከሚያፈቅሯቸው ቤተሰቦቻቸው ተለይተውና ለራሳቸው ደኅንነት ቅድሚያ ሳይሰጡ ኮቪድ-19ን ለመዋጋት በየፊናቸው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የብዙ ወገኖችን ሕይወት ታድጓል፡፡ ይህም ወደፊት በታሪክ ተመዝግቦ እንደሚቆይና በአርዓያነትም እንደሚታይ እረዳለሁ፡፡ በዚህ ወቅት ከጎናቸው ቆሜ መስዋዕት ለማድረግ ነባራዊው ሁኔታ ባይፈቅድልኝም ቢያንስ በፈጠራ ሥራዬ ተጠቅሜ ፌስ ሺልድ በማምረት ዕገዛ ማድረግ አለብኝ ብዬ ሥራውን ለማከናወን ተነሳሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ፌስ ሺልድና ፌስ ማስክ ልዩነታቸውን ብትነግሪን?
ቢሊ፡- ሁለቱም የጤና ባለሙያዎች ከልዩ ልዩ በሽታ ወይም ቫይረስ ራሳቸውን ለመከላከል ከሚጠቀሙባቸው የግል የበሽታ መከላከያ መሣሪያዎች መካከል የሚመደቡ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ፌስ ሺልድ በጭንቅላት በኩል የሚጠልቅና አስከ አገጭ መጨረሻ ድረስ ያሉትን ወይም ከአንገት በላይ ያሉትን አካሎች ከንክኪ የሚከላከል ነው፡፡ ፌስ ማክስ ግን አፍና አፍንጫን ብቻ የሚሸፍን ሲሆን ይህ በሽታን ወይም ንክኪን የመከላከሉን ተግባር ሙሉ አያደርገውም፡፡ ምክንያቱም ቫይረሱ በዓይንም ሊገባ ይችላል፡፡ በተለይ በቀዶ ሕክምና ወቅት ደም ተፈናጥቆ ወደ ግንባርና ዓይን ውስጥ ሊረጭ እንዲሁም በወሊድ ጊዜ በአዋላጅ ነርሷ ላይ ደም በተመሳሳይ መልኩ ሊፈናጠቅ ይችላል፡፡ መምህራን ፌስ ማስክ አድርገው ሲያስተምሩ ድምፃቸው ላይሰማ ይችላል፡፡ የቾክ ብናኝም ዓይናቸው ውስጥ የመግባት ዕድል ይኖረዋል፡፡ ይህንን ለመከላከል ፌስ ማስኩ አይችልም፡፡ ፌስ ሺልድ ግን ይህን ሁሉ የመከላከል ብቃት አለው፡፡
ሪፖርተር፡- ፌስ ሺልድ ከጤና ሙያተኞች ባሻገር ሌሎች ማኅበረሰቦች ያለው ፋይዳና አገልግሎት እስከ ምን ድረስ ነው?
ቢሊ፡- ፌስ ሺልድ አገልግሎቱ ለጤና ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን፣ ተቀራርበው አገልግሎት ለሚሰጡ (ፀጉር፣ የውበት ሳሎን፣ ወዘተ) ሰዎችም አስተካካዮች ይጠቀማሉ፡፡ በተረፈ ፌስ ማስክ ቀደም ሲል ከውጭ ነበር የሚገባው አሁን ግን በአገር ውስጥ በስፋት እየተመረተ ነው፡፡ ፌስ ሺልድ ግን ከውጭ እየገባ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ፌስ ሺልድን ለመሥራት የተጠቀምሽበት ጥሬ ዕቃ ምንድነው? ደረጃስ ወጥቶለታል?
ቢሊ፡- ፌስ ሺልዱ የተሠራው ከነጭ ፕላስቲክ ነው፡፡ ፕላስቲኩ ደግሞ ፊት ላይ ጉዳት እንዳያመጣ በስፖንጅ ተደግፏል፡፡ ማንጠልጠያ ፕላስቲክም ተበጅቶለታል፡፡ በዚህ መልኩ ከተሠራ በኋላ ተገቢውን ፈቃድ ለማግኘት ጉዳዩ የሚመለከተውን መንግሥታዊ አካል ጠይቄ ነበር፡፡ ፈቃድ የምንሰጠው ደረጃ ለወጣላቸው ምርት ብቻ ነው አሉኝ፡፡ ደረጃ ለማውጣት ወደ ደረጃ መዳቢ ኤጀንሲ አቀናሁ፡፡ ኤጀንሲውም የዚህ ዓይነቱ ፌስ ሺልድ እስካሁን ደረጃ አልወጣለትም፡፡ ደረጃ ባይወጣለትም እንዲሁ አገልግሎት ላይ ሊውል ይችላል አሉኝ፡፡
ሪፖርተር፡- ሌላ ጥረት አላደረግሽም?
ቢሊ፡– ኢንተርኔት ውስጥ ገብቼ ከፍተኛ ጥረት አድርጊያለሁ፡፡ በዚህም በውጭ አገር ለጤና ባለሙያዎች ከተለያዩ በሽታዎች ራሳቸውን መከላከል የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ዓይነት መሣሪያዎች እያመረቱ በዕርዳታ የሚያቀርቡ ግለሰቦችን አግኝቻለሁ፡፡ በዚህ መልኩ ካገኘኋቸው ግለሰቦች ኒውዮርክ የሚገኝ አንድ አርቲስት ይገኝበታል፡፡ ፌስ ሺልድ ሠርቼ ነበር ደረጃ ግን አልወጣለትም፡፡ እናንተ ዘንድ ይህ ጉዳይ እንዴት ዕየታየ ነው? የሚል መልዕክት ላኩለት፡፡ እሱም ‹ድንገተኛ ሁኔታ ወይም በድንገት የተከሰተ ስለሆነ ደረጃ ስለመውጣቱ ሁኔታ አንድም የጠየቀኝ አካል የለም፡፡ ዋናው መከላከሉና ምንም ነገር አለማስገባቱ ነው› የሚታየው አለኝ፡፡ ካናዳም ላለ አንድ ሰው መልዕክት እንዲሁ ላኩለት፡፡ እሱም ‹አሁን ኢመርጀንሲ ስቹዌሽን [ድንገት የተከሰተ ወረርሽኝ] ስለሆነ ደረጃው ላይ ትኩረት የሚያደርግ የለም፡፡ የሚታየው ጠቀሜታው ላይ ብቻ ነው› ብሎ ነገረኝ፡፡ የተለዋወጥኩትን መልዕክት ሁሉ ለደረጃ መደቢ ኤጀንሲ ነገርኳቸው፡፡ እነሱም ‹በእርግጥ ድንገተኛ ችግርን ላይ ነው ያለነው፡፡ ስለዚህ ኮቪድ-19 ከወጣ በኋላ ደረጃ የመውጣቱ ጉዳይ ይታያል እስከዚያው በዚሁ መገልገል ይቻላል› ብለው ነገሩኝ፡፡
ሪፖርተር፡- በቀን ስንት ፌስ ሺልድ ማምረት ትችያለሽ? ያመረትሽውን ፌስ ሺልድ ለጤና ተቋማት በዕርዳታ የሰጠሽበት ሁኔታ አለ?
ቢሊ፡- አዎ! ለቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ግምታቸው 4,000 ብር የሆኑ 50 ፌስ ሺልድ በዕርዳታ አበርክቻለሁ፡፡ እየተጠቀሙበት መሆኑም ተገልጾልኛል፡፡ በቀን እስከ 50 ፌስ ሺልድ ማምረት እችላለሁ፡፡ አሁን ግን ገበያ በማፈላለግ ላይ ነኝ፡፡ በዚህም የተነሳ በብዙኃን መገናኛና በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ምርቱን እያስተዋወኩ ነው፡፡ ይህንን የተመለከቱና የሰሙ አንዳንድ ሰዎች ስለዋጋውና አጠቃቀሙ ይጠይቁኝ ነበር፡፡ አሁን ሰው ኮቪድ-19 ላይ ትኩረት አደረገ እንጂ ከኮቪድ-19 ውጪ ሊያገለግል እንደሚችል ግንዛቤው አልሰረፀም፡፡ ፌስ ሺልድ ለተለያዩ አገልግሎቶችና ጠቀሜታ እንዳለው ለማስረዳት ሞክሬያለሁ፡፡ ኮቪድ-19 ከወጣም በኋላ መጠቀም እንችላለን፡፡
ሪፖርተር፡- በሥራሽ ላይ የረዱሽ ወይም የተባበሩሽ አካላት አሉ?
ቢሊ፡– በጣም እየደገፉኝ፣ እየረዱኝና እያበረታቱኝ ያሉት ቤተሰቦቼ ናቸው፡፡ ፕሮሞሽን በመሥራት ላይ ደግሞ የሕክምናው ኮሌጅ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ትብብር አድርገውልኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ፌስ ሺልድ የማምረቱ ሥራ በትምህርትሽ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አያሳድርብሽም ወይ?
ቢሊ፡- ምንም ዓይነት ተፅዕኖ አያሳድርብኝም፡፡ ቀደም ሲል በጠቀስኩት ምክንያት ትምህርት ተቋርጧል፡፡ የተቋረጠው ትምህርት ሲጀመር ደግሞ ሠራተኛ ቀጥሬ ፌስ ሺልድ የማምረቱ ሥራ እንዲቀጥል አደርጋሉ፡፡ ለዚህም ራሴን አዘጋጅቻለሁ፡፡
ሪፖርተር፡-ምቹ የሆነ የመሥሪያ ቦታ አዘጋጅተሻል?
ቢሊ፡- አዎ! በዚህ በኩል ችግር የለብኝም፡፡
ሪፖርተር፡- በሕክምናው ዘርፍ ምን ለመሆን ነው ፍላጎትሽ?
ቢሊ፡- ዶክተር ከሆንኩ በኋላ የቀዶ ሕክምና ሐኪም መሆንና የራሴን የግል ሆስፒታል ማቋቋም እፈልጋለሁ፡፡