Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከስያሜው ጀምሮ ውዝግብ እየፈጠረ ያለው የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የግል ንግድ ዘርፍ ታሪክ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶችን ከሦስት አሥርታት ወዲህ በመምራት ከሚታወቁት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ አቶ ብርሃነ መዋ፣ አቶ ሰለሞን አፈወርቅና አቶ ክቡር ገና ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ በንግድ ምክር ቤቶቹ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮችም ይሆናል ያሉትን ሐሳብ በመሰንዘር ይታወቃሉ፡፡

በንግድ ኅብረተሰቡ ዘንድ የሚታወቁት የቀድሞዎቹ የንግድ ምክር ቤቶቹ ፕሬዚዳንቶች በተለያዩ ወቅቶች የንግድ ምክር ቤቱን በመሩበት ወቅት ተግዳሮቶችን አስተናግደዋል፡፡ ፈታኝ የሚባሉ ሒደቶችን ከማሳለፋቸውም በላይ የንግድ ኅበረተሰቡን ጥያቄና ፍላጎት በመያዛቸው ከመንግሥት ወገን በበጎ ያልታዩ ነበሩ፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ የፖለቲካ አጀንዳ አለው በማለት የተፈረጀበት ወቅትም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ በየጊዜው ከመንግሥት በኩል የሚፈጠሩ ጫናዎችም መሥራት የሚፈልጉትን ለመሥራት እንዳላስቻላቸው ሲገልጹ ነበር፡፡ በተለይ ከመንግሥት የነበረው ጫና ቀላል እንዳልነበርም ይታወሳል፡፡   

እነዚህ አንጋፋ የንግድ ምክር ቤቶቹ የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች ኃላፊነታቸውን ለተተኪዎቻቸው ካስረከቡ በኋላ ከንግድ ምክር ቤቶቹ ርቀው የቆዩ ሲሆን፣ ከትናንት በስቲያ ግን አራቱም በአንድ መድረክ የተገናኙበት አንገብጋቢ መድረክ ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ፕሬዚዳንት መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር)ን ጨምሮ የቀድሞዎቹን ፕሬዚዳንቶች ባልተለመደ ሁኔታ በአንድ መድረክ እንዲገናኙ ግድ ያለው ደግሞ፣ ለዓመታት የግሉ ንግድ ዘርፍ ሕመም ሆኖ በቆየው የንግድ ምክር ቤቶች አደረጃጀት ላይ የተዘጋጀው አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ላይ ለመምከርና የተሻለ ሐሳብ ለማመላከት ነው፡፡

ሰኞ ታኅሳስ 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ከተካሄደው መድረክ ከተሳተፉ ከቀድሞ ፕሬዚዳንቶች፣ ዋና ጸሐፊዎችና የሁሉም አባል ንግድ ምክር ቤቶች ፕሬዚዳንቶች አስተያየት መገንዘብ የተቻለው፣ እስካሁን ሥራ ላይ የነበረው የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እጅግ የበዙ ችግሮች ያሉበት፣ ለአደረጃጀት የማያመች፣ የግል ዘርፉን የማይመጥን እንደነበር ነው፡፡ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው የመክፈቻ ንግግር የተጀመረው የዕለቱ ፕሮግራም ላይ ከቀረቡት የተለያዩ ሐሳቦች ውስጥ የተወሰነው በሚከተለው መንገድ ቀርቧል፡፡  

ነባሩ አዋጅና የአሁኑ ፕሬዚዳንት ምልከታ

አሁን በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ በተመለከተ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በንግግራቸው ያካተቱት ይገኝበታል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ኢንጂነር መላኩ እዘዘው፣ ‹‹ሁላችንም በጥልቀት እንደምናውቀው፣ በአወዛጋቢነቱ የሚጠቀሰው የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ የንግዱን ኅብረተሰብ የትብብር መንፈስ ያቀዛቀዘና ለእርስ በርስ መናቆር በር የከፈተ ጭምር መሆኑ አይዘነጋም፤›› ብለዋል፡፡

አዋጁ ንግድ ምክር ቤቶች እንዲጠናከሩና እንዲያብቡ ከማስቻል ይልቅ፣ የግሉ ዘርፍ እንዲቀነጭር፣ ብሎም በጠንካራ አባላትና ገቢ እንዳይጠናከር ማድረጉን አክለዋል፡፡

ነባሩ አዋጅ የንግድ ምክር ቤቶች ተሳትፏቸውን በተገቢውና በሚጠበቀው ልክ እንዳያሳድጉ፣ መተማመን እንዳይፈጥሩ፣ የጭቅጭቅና ንትርክ ምርጥ ምሳሌ እንዲሆኑ ያደረገ መሆኑን ጭምር ገልጸዋል፡፡

ከ18 ዓመታት በላይ በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 341/95 ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት ለውጥ ብሎም የንግድ እንቅስቃሴና ዘርፉ ከሚፈልገው አሠራር ደረጃ አንፃር ብዙ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑን በማመን፣ በተለይም አዋጁ ለትርጉም የተጋለጡ፣ ለትግበራ የማይመቹና ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይሄዱ ድንጋጌዎችን የያዘ ብቻ ሳይሆን የንግድ ምክር ቤቶችን በእጅጉ ያዳከመ እንደሆነ በተደጋጋሚ መገለጹን አስታውሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እምነት አሁን ያለው የግሉ ዘርፍ አባልነት አሻሚ፣ አደረጃጀቱ የተበታተነ፣ ያልተቀናጀና የታለመለትን ዓላማ ለማሳካት ያላስቻለ ደካማ መሆኑን ከተግባር ተሞክሮ ለመረዳት ይችላልም ብለዋል፡፡  

በዚህ ረገድ ተደራራቢና የተከፋፈለ ድርጅታዊ መዋቅር መኖር፣ በአዋጁ ሳይሆን በሌሎች ሕግች ተደግፈው በመደራጀት የሚንቀሳቀሱ የንግድና አምራች ማኅበራት እንዳሉ፣ በጥቅሉ ሲታይ በአዋጅ ቁጥር 341/1995 የተደራጁት የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ጠንካራ ሆነው አጥጋቢ እንቅስቃሴ አድርገዋል ለማለት እንደማያስደፍር አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡ ይልቁንም በተበታተነ መንገድ የተደራጁት የኢትዮጵያ የንግድና አምራች ኅብረተሰብ አካላት ለተመሳሳይ ዓላማ ጊዜና ሀብት ሲያባክኑ ይታያሉ፡፡ በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ውስጥ በንግድ፣ በአገልግሎትና በምርት ተግባር የተሰማሩ የግሉ ዘርፍ አደረጃጀቶችን በሚመለከት የተደረጉ በርካታ ጥናቶች ይህንኑ ድክመት ያመላክታሉ ብለዋል፡፡ ኢንጂነር የመላኩን ሐሳብ ከዕለቱ ተሳታፊዎች በርካቶች የሚጋሩት ስለመሆኑ ከሰጡት አስተያየት ለመረዳት ተችሏል፡፡

ተቃውሞ ያስነሳው አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ስያሜና አደረጃጀት

በመድረኩ በቀድሞና በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተሰጡ አስተያቶች ከአዋጁ ስያሜና መግቢያ የሚጀምር ነው፡፡ በተለይ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ የኢትዮጵያ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የሚለው ስያሜ ተገቢ ያለመሆኑን የሚጠቁሙ በርካታ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል፡፡ አራቱ የቀድሞ ንግድ ምክር ቤቶች ፕሬዚዳንቶችም በዚህ ሐሳብ የማይስማሙ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በማስታወስ የንግድ ምክር ቤቱ አደረጃጀት ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ከሚል ንግድ ምክር ቤት መባል ይኖርበታል ብለዋል፡፡

በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ‹‹የንግድ ኢንዱስትሪ ንግድ ምክር ቤት›› መባሉ ችግር የሚፈጥር መሆኑን ለማመላከት ከተሰጡ ማብራሪያዎች ውስጥ ስያሜው የንግድ ኅብረተሰቡን በመከፋፈል ውዝግብ ይፈጥራል የሚለው አንዱ ነው፡፡ የንግድ ኅብረተሰቡን እንዲህ ሊከፋፍል በሚችል መልኩ አደረጃጀቱን ማስቀመጡ አደጋ አለውም ብለዋል፡፡ እንዲህ ያለው ችግር ደግሞ በቀድሞው አዋጅ የታየ ነው፡፡ በሁሉም ዘርፍ ያሉ የንግድ ድርጅቶች በጥቅል ነጋዴ በሚል ተይዘው ንግድ ምክር ቤት በሚል ሥር መተካት ይኖርባቸዋል የሚለው ሐሳብ የብዙዎቹ ነበር፡፡ አሁን እንደሚታየው ንግድ ለብቻ ኢንዱስትሪ ለብቻ ተደርጎ የሚዋቀር ነው፣ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ በየዘርፉ ከፋፍሎ ከማየት በአንድ ንግድ ምክር ቤት ሥር መጠቅለል ይኖርባቸዋል የሚል አስተያየት ተሰጥቷል፡፡

ይህንን ሐሳብ በእጅጉ ከሚደግፉት የሲዳማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ አንዱ ናቸው፡፡ እስካሁን በነበረው አደረጃጀት ነጋዴው ተበድሮ ሲተራመስ ሌሎች ተጠቃሚዎች ሆነውበታል፡፡ ስለዚህ ረቂቅ አዋጁም እንዲህ ያለውን የተከፋፈለ አደረጃጀት ትቶ ‹‹ንግድ ምክር ቤት›› በሚል መሰየም ይኖበታል ብለዋል፡፡

ስያሜው ንግድና ኢንዱስትሪ ማለቱ በራሱ ሌሎች የንግድ ዘርፎች ምን ሊሆኑ ነው የሚለውን ጥያቄ ያስነሳ ሲሆን፣ እንደ ቱሪዝም፣ እርሻ፣ ትራንስፖርትና ሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች ሳይታሰቡ ነው ወይ? ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የሚባለው መከራከሪያ ቀርቧል፡፡ እንዲህ ያሉ ብዥታዎችን ሁሉ ለማስቀረት ሁሉንም የቢዝነስ ዘርፍ በማጠቃለል የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ተብሎ መሰየም ይኖርበታል ተብሏል፡፡ ይህ ማለት ግን ሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች በየራሳቸው መቋቋም አይችሉም ማለት እንዳልሆነም ተገልጿል፡፡

የቦርድ ምርጫና የፕሬዚዳንቶች አሰያየም

አዲሱ ረቂቅ አዋጅ በብርቱ ትችት ከቀረበበት ነጥብ ሌላኛው የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ምክትል ፕሬዚዳንትና የቦርድ አባላትን አሰያየም የሚመለከት ነው፡፡ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ በጠቅላላ ጉባዔ የተመረጡት የቦርድ አባላት ከመካከላቸው ፕሬዚዳንቱንና ምክትል ፕሬዚዳንቱን ይመርጣሉ፡፡ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት የጉባዔውንና የቦርዱን ስብሰባዎች ጥሪ ያስተላልፋል፣ ይመራል፡፡ የቦርድ አባላት ፕሬዚዳንቱንና ምክትል ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ከ11 መብለጥ የለባቸውም፡፡ በምክር ቤቱ የቦርድ አባላት መሆን የሚችለው ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ብቻ መሆኑን ያመለክታል፡፡

የቦርድ አባላት ስብጥር

ረቂቁ የቦርድ አባላት ሲመረጡ ስብጥራቸው ምን መምሰል እንዳለበትም ያስቀምጣል፡፡ በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የቦርድ አባላት ስብጥር፣ ከክልል የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች 50 በመቶ፣ ለአገር አቀፍ ደረጃ ከሚቋቋሙ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማኅበራት 40 በመቶ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚቋቋሙ የንግድ ሥራ ዘርፍ ማኅበራት 10 በመቶ፣ ያካተተ መሆን አለበት ይላል፡፡ የክልል የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች የቦርድ አባላት ስብጥር፣ ከግለሰብ ነጋዴዎች 10 በመቶ፣ ከሽርክና ማኅበራት 20 በመቶ፣ ኃላፊነታቸው ከተወሰነ የንግድ ማኅበራት 20 በመቶ፣ ከንግድ ሥራ ዘርፍ ማኅበራት 10 በመቶ ያካተተ መሆን እንዳለበትም ይገልጻል፡፡ ይህ ክፍፍል በቀድሞው አዋጅ የሌለ ሲሆን፣ በአዲሱ ረቂቅ ላይ ግን የቦርድ አመራር እንዲህ ባለው መንገድ መዋቀር ይኖርበታል ብሎ ደንግጓል፡፡

የቦርድ አባላት አወቃቀር ተሰባጥሮ ከየዘርፉ ከሚወከሉ ይሁን መባሉ ትክክል ሊሆን የማይችልባቸው የተለያዩ ምክንያቶች ከእነዚህም ስብጥር ለማሟላት ሊኖር የሚችለው ፍለጋና ኮታ ለማሟላት ተብሎ ጠንካራ አመራር ማግኘት አለመቻል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም የፕሬዚዳንትና የምክትል ፕሬዚዳንት ምርጫ በቀጥታ በጠቅላላ ጉባዔ የሚመራ ሲሆን፣ በአዲሱ ረቂቅ ግን በጠቅላላ ጉባዔ የሚመረጡት አሥራ አንዱ የቦርድ አባላት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ይመርጣሉ የሚል መሆኑ፣ ፈፅሞ ለአሠራር የሚመች አለመሆኑም ተገልጿል፡፡  በረቂቅ አዋጁ የፕሬዚዳንትና የምክትል ፕሬዚዳንት አሰያየም ላይ በጠቅላላው ጉባዔ የተመረጡ የቦርድ አባላት ፍላጎት የተለያየ መሆኑና ሁሉም ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት መሆን ቢፈልግ እንዴት ሊመረጥ ይችላል? የሚል ጥያቄም ተነስቷል፡፡

በዚህ አካሄድ ከቦርድ አባላቱ ጠንካራ የሚባል መሪ ተገቢውን ቦታ ላያገኝ የሚችል በመሆኑ እንዲህ ባለው የፕሬዚዳንቶችና የምክትል ፕሬዚዳንቶች ምርጫ ለንግድ ኅብረተሰቡ ሊያገለግሉ የሚችሉ መሪዎችን ማግኘት ያስቸግራል የሚል ሥጋትም አስከትሏል፡፡  የፕሬዚዳንትና የምክትል ፕሬዚዳንት ምርጫው በጠቅላላ ጉባዔ ቢሆን ይመረጣል የሚል ሐሳብም ቀርቧል፡፡  

ከዚህ ጋር ተያይዞ የተነሳው የንግድ ምክር ቤቶች አባላት ስብጥርን በተመለከተ ከግለሰብ፣ ከሸርክና ማኅበራት፣ ኃላፊነቱ ከተወሰነ ማኅበራት፣ ከአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማኅበራትና ከንግድ ዘርፍ ማኅበራት የተውጣጡ መሆን አለባቸው መባሉ ነው፡፡ ቦርዱ ከአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ 40 በመቶ መያዝ አለበት የማለቱ ነገርም ረቂቅ አዋጁ ከፋፋይ ነው አስብሏል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ባለው ሁኔታ ስብጥር መቀመጥ የሌለበት በመሆኑ ከረቂቅ አዋጁ መውጣት አለበት፡፡  

የንግድ ምክር ቤት ፖለተካዊ አንድምታ

በምክክር መድረኩ ላይ የቀድሞው ፕሬዚዳንቶች ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች አንዱ፣ የንግድ ምክር ቤቱ መሪዎች የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ ንግድ ምክር ቤቱን ለሚፈልጉት ፖለቲካ ማራመጃ አድርገውታል የሚለው ነው፡፡ እንዲህ ባለው አስተያየት ላይ አራቱም ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ አንዳቸውም የእኔ የሚሉት የፖለቲካ አመለካከት ያልነበራቸውና የአንድም የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዳልነበሩ ገልጸዋል፡፡ እንዲያውም በተቃራኒ መንግሥት ምክር ቤቱን የፖለቲካ ፓርቲ መጠቀሚያ በማድረግ ሲጥር እንደነበር አመልክተዋል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ የፖለቲካ አመለካከት አለው ያስባለው የንግድ ኅብረተሰቡን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ይዞት የሚቀርበው ሐሳብ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡ እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችለው ረቂቅ የሊዝ አዋጁ ላይ ንግድ ምክር ቤቱ በጥናት ላይ ተመሥርቶ አስተያየቱን ባቀረበበት ወቅት የገጠመው ችግር መሆኑን አቶ ብርሃነ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ምረጥ አዲስ›› በሚል ዜጎች የመምረጥ መብታቸውን እንዲጠቀሙ የሚያስቸል ፕሮግራም በአቶ ክቡር ገና፣ መንግሥት በአቶ ክቡር ገና ላይ ጥርስ እንዲነክስ ያደረገ እንደነበር አቶ ብርሃነ አብራርተዋል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱን በሚመሩበት ሰዓት ገጥሟቸው የነበሩ ችግሮችን በተለያየ መልክ የገለጹት የቀድሞዎቹ ፕሬዚዳቶች፣ መንግሥት በምክር ቤቱ ውስጥ ጣልቃ ለመግባትና የራሱን ፍላጎት ለማራመድ ሲጠቀም እንደነበርም አመላክተዋል፡፡ ያለውን ጫና ተቋቁሞ ጠንካራ የንግድ ምክር ቤት እንዲኖር ስለመጣራቸው አብራርተዋል፡፡

ይሁንና ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ በኋላ መቆጣጠር ያልቻለው ንግድ ምክር ቤቱን ነበር ያሉት አቶ ብርሃነ መዋ፣ በጊዜ ሒደት ግን ንግድ ምክር ቤቱን ለማስተንፈስና ለመጣል ያግዛል የተባለ ሕግ ተቀርፆ ተግባራዊ ሆኗል ብለዋል፡፡

ይህ የሆነው የንግዱን ኅብረተሰብ የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ በጥናት ጭምር በማቅረብ የሚደረገው ሙግት ‹ንግድ ምክር ቤቱን የፖለቲካ ማራመጃ አደረጉት› ከሚል የመነጨ ሲሆን፣ ይህም የንግድ ምክር ቤቱን መሪዎች መስዋዕትነት አስከፍሏል ብለዋል፡፡ አሁንም የተዘጋጀው ረቂቅ የመንግሥን ፍላጎት ለመሙላት ተብሎ የሚወጣ መሆን እንደሌለበት በመግለጽ፣ ጠንካራ ንግድ ምክር ቤት እንዲኖር በተለይ ከመንግሥት ፍላጎት ውጪ የንግድ ኅብረተሰቡን ሊጠቅም በሚችል መልኩ መቀረፅ እንዳለበት መክረዋል፡፡

‹‹የንግድ ኅበረተሰቡ በነፃነት የመከረበት ሕግ ነው የሚያስፈልገን፤›› ያሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ ‹‹እየተጻፈ የሚቀርብልንን ሕግ መቀበል የለብንም፣ የሚያስፈልገንን መክረንና ተወያይተንበት ማቅረብ ይኖርበታል፤›› በማለት ከመንግሥት ተፅዕኖ ውጪ የሆነ አዋጅ እንዲኖር አመልክተዋል፡፡

‹‹የ21ኛውን ክፍለ ዘመን የሚመጥን ሕግ ነው የሚፈለገው፤›› ያሉት አቶ ክቡር ገናም፣ የንግድ ምክር ቤቶች አደረጃጀት የንግድ ኅብረተሰቡን በሚጠቅም መልኩ መሆን እንዳለበት፣ ጠንካራ መሆን ካስፈለገ የሌሎች አገሮችን ልምድ ማየትና የተሻለ የሚሆነውን በመምረጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡   

አባላት በፈቃደኝነት ወይስ በግዳጅ

በዕለቱ አንዱ አነጋጋሪ ጉዳይ የነበረው የንግድ ምክር ቤቶች አባላነት ጉዳይ ነው፡፡ ድርጅቶችና ግለሰብ ነጋዴዎች የንግድ ምክር ቤቱ አባል መሆን ያለባቸው በፈቃደኝት ነው? ወይስ በአስገዳጅ? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ በመድረኩ ላይ ተነስቷል፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሕግ ባለሙያዎች በቅርቡ እንዳብራሩት፣ የአባልነት ጉዳይ ብዙ ሲባልበት የቆየ ሲሆን፣ ይህንን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ የእንዲቻል የተለያዩ አማራጮች ስለመታየታቸው ገልጸው ነበር፡፡ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ መንግሥት ተደራጁ ብሎ አዋጅ ካወጣ አባልነት ግዳጅ ሊሆን ይችላል፣ ካልሆነ ግን በፈቃደኝት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት ብለዋል፡፡ አቶ ሰለሞን ደግሞ አባልነት በግድ መሆን አለበት ብለው በብርቱ ሞግተዋል፡፡ እንደ እኛ ላለ አገር አባልነት ግዴታ መሆን እንደሚኖርበትም የተለያዩ ምሳሌዎችን ጠቅሰው ተናግረዋል፡፡

አቶ ክቡር አባልነት በግዳጅ ይሁን ወደሚለው ያደላ ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡ ግዴታ የሚለው ጉዳይ ተስማሚ ባይሆን የውዴታ ግዴታ በሚል ሊተካ እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡ አቶ ብርሃነ ደግሞ፣ ‹‹አባልነት በግዴታ መሆን የለበትም፤›› የሚል አመለካከታቸውን ሰንዝረዋል፡፡    

የውይይት መድረኩም ረቂቅ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ በጥልቀት በመወያየት፣ የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ የሚጠበቅበትን ሚና በተገቢው መወጣት የሚያስችለውን፣ ከአቻ አካላት ጋር ተወዳዳሪነቱን የሚያጎለብተውን ተደማጭ፣ እንዲሁም በአደረጃጀቱና አሠራሩ ጠንካራ የሆነ ምክር ቤትን ለማቋቋም የሚያስችለውን ግብዓት ለማሳሰብ ያለመ ነበር፡፡ ከመድረክ መታዘብ የተቻለው፣ አዲሱ ረቂቅ አዋጅም ብዙ ክፍተት ያለበት መሆኑን ነው፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ በዕለቱ ያሰባሰበውን ግብዓት አደራጅቶ ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን ይህ ረቂቅ አሁን እየቀረበበት ካለው አስተያየት አንፃር ድጋሚ መታየት ይኖርበታል የሚለው አመለካከት ብልጫ ይዟል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች