Sunday, September 24, 2023

ግብፅና ሱዳን የህዳሴ ግድብን አጀንዳ ከአፍሪካ ኅብረት ለማላቀቅ የፈጠሩት ጥምረት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ በግብፅናሱዳን መንግሥታት መካከል ያለውን ልዩነት ለመፍታት ሲካሄድ የከረመው ድርድር የተለያዩ አደራዳሪዎችንና ታዛቢዎችን እየቀያየረ ዓመታትን ቢዘልቅም፣ መሠረታዊ የልዩነት ነጥቦቹ ግን ዛሬም እንዳሉ ናቸው። 

ሳይንስን መሠረት ባደረገ ውይይት ኢትዮጵያ የያዘችውን ምክንያታዊ አቋም ማስቀየር ያልቻሉት ሁለቱ የታችኛው ዓባይ ተፋሰስ አገሮች፣ በዋናነትም ግብፅ ጥቅሟን ለማስከበር ያላትን ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉልበት ተጠቅማ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታ ምክር ቤት ብትወስደውም፣ ኢትዮጵያ ብስለት በተሞላበት ሥልት የህዳሴ ግድቡን አጀንዳ ከተመድ እጅ ውስጥማውጣት በአኅጉራዊው የአፍሪካ ኅብረት ሥር እንዲታይ ማድረግ መቻሏ ይታወሳል። 

የህዳሴ ግድቡ አጀንዳ ወደ አፍሪካ ኅብረት መተላለፉን የግብፅ መንግሥት ባይቀበለውም፣ ይህንን በይፋ መናገር ለኅብረቱም ሆነ ለአፍሪካ አኅጉር አገሮች የሚያስተላልፈው መልዕክትና ይዞ የሚመጣውን ጣጣ በመመዘን ሳይወድ በግዷ የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነትን ተቀብሏል፡፡  

የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ የግል ጥረት የህዳሴ ግድቡ አጀንዳ በኅብረቱ ጠረጴዛ ላይ ለውይይትና ድርድር ቢቀመጥም፣ አጀንዳውን ደጋግሞ ከመግለጽና ይህንኑ ተግባር ዳግም ለመተግበር ቀጠሮ ከመያዝ ውጪ ሦስቱ አገሮችን ይህ ነው የሚባል ስምምነት ላይ ለማድረስ አልተቻለም። 

ላለፋት ዘጠኝ ዓመታት ሲካሄድ በቆየው በዚህ ድርድር የሦስቱ አገሮች የልዩነት ነጥቦች ሳይንስን መሠረት ባደረገ ድርድር መቋጫ እንዳያገኝ፣ የተለያዩ ሰበቦችንና ምክንያቶችን በመጠቀም ያጓተተችው ግብፅ እንደሆነች በኢትዮጵያ በኩል ወቀሳ ሲነሳ ቆይቷል። 

ይህ አጀንዳ በአፍሪካ ኅብረት የአደራዳሪነት ሚና ሥር ከገባበት ጊዜ አንስቶ በተካሄዱት ድርድሮች ግን፣ የሱዳን መንግሥት የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ የተጀመረው ድርድሮች እንዲቋረጡና እንዲራዘሙ በተደጋጋሚ ጊዜ ምክንያት ሆኗል።

በሱዳን ተደራዳሪዎች በኩል ሲቀርቡ ከነበሩት ምክንያቶች መካከልም ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር መወያየት እንደሚፈልጉና ከሱዳን ብሔራዊ ካውንስል ጋር ለመወያየት ጊዜ እንዲሰጣቸው የሚጠይቁ ነበሩ። በዚህም ጥረት በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት የተጀመረው ድርድር በሱዳን ወገን ተደራዳሪዎች ጥያቄ፣ ድርድሩ ቢያንስ ለሦስት ጊዜ ያህል ተቋርጧል ወይም በወቅቱ ሳይካሄድ ተራዝሟል። 

ድርድሩ ዳግም እሑድ ታኅሳስ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. የጀመረ ሲሆን፣ በዚህም ወቅት አደራዳሪው የአፍሪካ ኅብረት የወከላቸው ባለሙያዎች በሦስቱ አገሮች ልዩነቶች ዙሪያ ያቀረቡት ሰነድ ለውይይት ቀርቦ ነበር። 

በደቡብ አፍሪካ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትርና የአፍሪካ ኅብረት አስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሰብሳቢነት በተካሄደው በዚህ የሰሞኑ ድርድር፣ የሦስቱ አገሮች ስድስት ሚniስትሮች ተገኝተው በቀረበው ሰነድ ላይ የየአገሮቻቸውን አቋም በማንፀባረቅ ድርድሩ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን የኢትዮጵያ የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። 

ይህንኑ የሰሞኑ ድርድር አስመልክቶ በሱዳን መንግሥት የተሰጠው መግለጫም ተመሳሳይ ነበር።

በአፍሪካ ኅብረት የተወከሉት ባለሙያዎች ያቀረቡትን ሰነድ ኢትዮጵያ በበጎ እንደምትመለከተው፣ በቀጣይ በሚካሄደው ድርድር ሰነዱን እንደ ግብዓት ለመጠቀም ፈቃደኛ መሆኗን እንዳሳወቀች በመንግሥት በኩል ይፋ የተደረገው መግለጫ ያስገነዝባል። 

የግብፅ ወገን ሰነዱን ጨርሶ እንደማይቀበለው የሚገልጸው የኢትዮጵያ መግለጫ፣  በሱዳን በኩል ደግሞ ሰነዱ ለሒደቱ ጠቃሚ እንደሆነና በቀጣይ የአፍሪካ ኅብረት ባለሙያዎች ተጨማሪ ሚና ላይ በጋራ በማፅደቅ ድርድሩን መቀጠል ፍላጎት እንዳለው በወቅቱ ማስታወቁን፣ ይኸው የኢትዮጵያ መግለጫ ያስገነዝባል። 

በሱዳን መንግሥት በኩል ይፋ የተደረገው መግለጫ በበኩሉ፣ ‹‹የቀረበው ሰነድ የአፍሪካ ኅብረት ባለሙያዎች ድርድሩን በማመቻቸት ረገድ የሚኖራቸውን ሚና በግልጽ የማያስቀምጥና የመፍትሔ አቅጣጫዎችንም የማያመላክት ስለሆን የተሟላ አይደለም። ቢሆንም የቀረበው ሰነድ ድርድሩን ለማስቀጠል ጠቃሚነት አለው፤›› በማለት የሱዳንን አቋም ይፋ አድርጓል።

በሱዳን መንግሥት የወጣው መግለጫ አክሎ እንዳስታወቀው ታኅሳስ 25 ቀን የተካሄደው ውይይት መደምደሚያ ሦስቱ አገሮች በጋራ ተገናኝተው የልዩነትና የስምምነት ነጥቦቻቸውን ለይተው፣ ጥር 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ለሚካሄደው ድርድር የተጠናቀረ ሪፖርት እንዲያቀርቡ በደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቅጣጫ የተሰጠበት ነበር።

በመሆኑም በኢትዮጵያ በኩል በዕለቱ የተካሄደውን ስብስባ አስመልክቶ ከተሰጠው መግለጫ ጋር ስምምነት እንዳለው መገንዘብ ይቻላል። 

ታኅሳስ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. የተካሄደው ውይይት በተገለጸው መንገድ ከተጠናቀቀ በኋላ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት፣ ሦስቱ አገሮች የልዩነትና የስምምነት ነጥቦቻቸውን ለመለየት የሚያስችላቸውን ውይይት ለመጀመር በቀጣዩ ቀን ቀጠሮ ይዘው የነበረ ቢሆንም፣ በቀጠሮው ቀን የሱዳን ወገን ባለመገኘቱ ምክንያት ሳይካሄድ ቀርቷል። 

ጉዳዩን አስመልክቶም የውኃመስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ሰኞ ታኅሳስ 26 ቀን 2013 ዓ.ም. መግለጫ አውጥቷል።

‹‹የዕለቱ ሰብሳቢ የሆነችው ኢትዮጵያ ባስተላለፈችው ጥሪ መሠረት የግብፅ ልዑክ፣ እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት ባለሙያዎችና ታዛቢዎች ተገኝተዋል፡፡ ሆኖም የልዩነትናአንድነት ሐሳቦችን ለማጠናቀር የታሰበው የዛሬው ስብሰባ በሱዳን አለመገኘት ምክንያት ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ ይኸውም ለአፍሪካ ኅብረት አስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር በኢትዮጵያ በኩል ተገልጿል፤›› ሲል መግለጫው ያስረዳል፡፡

የሱዳን ወገን በውይይቱ ያልተገኘበትን ምክንያት የተመለከተ መግለጫ ሰኞ ታኅሳስ 26 ቀን በሱዳን የመስኖና የውኃ ሀብት ጉዳዮች ሚኒስቴር አማካይነት ተሰጥቷል።

‹‹ሱዳን እሑድ ዕለት የተካሄደው የሚኒስትሮች ውይይት መጠናቀቁን ተከትሎ በአፍሪካ ኅብረት ከተወከሉት ባለሙያዎችና ከታዛቢዎች ጋር የተናጠል ውይይት በዚያው ዕለት ለማካሄድ ጥያቄ አቅርባ መልስ እየጠበቀች የነበረ ቢሆንም፣ ለጥያቄው መልስ ሳይሰጣት የቀጣዩ ውይይት ጥሪ የደረሳት በመሆኑ በውይይቱ ከመሳተፍ ታቅባለች፤›› ሲል መግለጫው የሱዳንን ምክንያት ይጠቅሳል። 

በማከልም የሱዳን መንግሥት በአፍሪካ ኅብረት ለተወከሉ ባለሙያዎች ግልጽ የሆነ የአደራዳሪነት ሚና እንዲሰጥና ድርድሩ እንዲካሄድ በፅኑ እንደምትሻ፣ እንዲሁም በዚህ ሁኔታ የሚደረግ ድርድር በሦስቱ አገሮች መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ ያስችላል የሚል እምነት እንዳላት ያመለክታል።

ይሁን እንጂ ሱዳን ታኅሳስ 25 ቀን ባወጣችው መግለጫ በቀጣዩ ቀን በተጠራው ወይይት ላይ ላለመሳተፍ ምክንያት የሆናትን አመክንዮ፣ ወይም የተናጠል ውይይት ጥያቄ ማቅረቧንም ሆነ መልስ አለማግኘቷን በተመለከተ የሚለው የለም፡፡

የሦስቱ አገሮች መሠረታዊ የልዩነት ነጥብ ምንድነው? 

በህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልና አለቃቅን በተመለከተ በሦስቱ አገሮች መካከል ለዘጠኝ ዓመታት ሲካሄድ በከረመው ድርድር በርካታ የቴክኒክ ጉዳዮች መፍትሔ ቢያገኙም፣ ሁለት አንድነት ያላቸው ነጥቦች የአገሮቹ መሠረታዊ ልዩነቶች ሆነው ይጠቀሳሉ። 

ከእነዚህ ሁለት የልዩነት ነጥቦች መካከል መሠረታዊው የልዩነት ምንጭ ኢትዮጵያ ከህዳሴ ግድቡ በላይ በሚገኘው በዓባይ ተፋሰስ ላይ ወደፊት የምታካሂደው ልማት፣ የህዳሴ ግድቡን የውኃ ሙሌት ቀመር ለማውጣት ጥቅም ላይ መዋል አለበት የሚል ነው። 

ይህም ማለት ወደ ህዳሴ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን ኢትዮጵያ ከህዳሴ ግድቡ በላይ በየትኛውም የዓባይ ውኃ ተፋሰስ ላይ በምታካሂደው ልማት ምክንያት የተፈጠረ እንደሆነ፣ እንደ ድርቅ ሁኔታ መከሰት ተቆጥሮ ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ ከያዘችው ውኃ ላይ እንድትለቅ የሚያስገድድ መሆኑን አንድ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባል ይገልጻሉ። 

ይህ ሙግት በዋነኝነት የሚነሳው በግብፅ በኩል ቢሆንም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሱዳን መንግሥትም እየተነሳ ነው። 

‹‹ኢትዮጵያ በዚህ ወጥመድ ውስጥ ወደቀች ማለት ያላት አማራጭ አንድም ከግድቡ በላይ ባለው የዓባይ ተፈሳስ ምንም ዓይነት ልማት አለማካሄድና ህዳሴ ግድቡን ብቻ መሙላት ይሆናል። ለማካሄድ ከወሰነች ደግሞ በቅድሚያ ለግብፅና ሱዳን የማሳወቅ ግዴታ እንደሚኖርባትና ባካሄደችው ልማት የተፈጠረ የውኃ መቀነስን ለማካካስ በህዳሴ ግድቡ ከያዘችው ውኃ ለግብፅና ሱዳን የመልቀቅ ግዴታ ይወድቅባታል፤›› ሲሉ አጣብቂኙን ያስረዳሉ። 

ይህም ማለት ከግድቡ በላይ ባለው የዓባይ ተፋሰስ ላይ ልማት አካሂዳለሁ የሚል አቋም በኢትዮጵያ በኩል ከተያዘ፣ የህዳሴ ግድቡን ሙሉ በሙሉ በውኃ መሙላት እንደማይቻል፣ ይህም ከግድቡ የሚፈለገውን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት አያስችልም ብለዋል።

ከህዳሴ ግድቡ በላይ የዓባይን ውኃ ላለማልማት ኢትዮጵያ ተስማማች ማለት ደግሞ በዓባይ ላይ የሚኖራት የመጠቀም መብት ህዳሴ ግድቡ ብቻ እንደሚሆን፣ ይህም የዓባይ ውኃን ክፍፍል እንዳደረገች የሚቆጠርና በወደፊት ትውልድ ፍላጎት ላይ ዛሬ እንደወሰነች ይቆጠራል ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ሌላኛው የልዩነት ነጥብ የድርድሩ ውጤት በአገሮቹ ላይ አስገዳጅ መሆን አለበት የሚል ሲሆን፣ የልዩነት ነጥቦቹ ሳይፈቱና መፃኢ የተፈጥሮ ሁኔታዎችን ማወቅ በማይቻልበት ዓውድ ውስጥ ኢትዮጵያን ለማሰር በሁለቱ የታችኞቹ አገሮች የተሸረበ ሸፍጥ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ታኅሳስ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የህዳሴው ግድብ ሙሌትና ዓመታዊ አስተዳደርን የሚመለከተው ሰነድ ላይ የሚደረገው ድርድር በአመዛኙ መግባባት የተደረሰበት ቢሆንም፣ ወደፊት በዓባይ ተፋሰስ ላይ ከሚገነቡ የውኃ ልማት ሥራዎች ጋር የሚኖረው ቁርኝት ዋነኛ የልዩነት ሐሳብ መሆኑን ይገልጻል።

መግለጫው በማከልም፣ ‹‹የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ ፍጆታ የሌለው የኃይል ማመንጫ ግድብ እንደ መሆኑ፣ በግድቡ ላይ የሚደረሰው ስምምነት ይህንኑ ከግምት ያስገባና የተሟላ የውኃ ስምምነት በሌለበትና ኢፍትሐዊ አጠቃቀም በሰፈነበት ተፋሰስ፣ የኢትዮጵያን የመጠቀም መብት የሚያቅብ እንዲሆን ኢትዮጵያ አትፈቅድም፤››  ሲል የኢትዮጵያን ፅኑ አቋም አስታውቋል፡፡

ይህን መሠረት በማድረግ ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ አሞላልና ዓመታዊ አስተደዳር የሚመለከተውን ደንብ በጋራ ስምምነት ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ እንደሆነች፣ በዚህም መሠረት የስምምነት አማራጮችን ለግብፅናሱዳን እንዳቀረበች፣ ላቀረበቻቸው አማራጮችም የሁለቱ አገሮች ምላሽ ቀና እንደሚሆን ተስፋ እንደምታደርግ አስታውቃለች። 

የታኅሳስ 25 ቀን ስብሰባ መጠናቀቅን ተከትሎ የሱዳን የሸግግር መንግሥት ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌተና ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልልሲሲ ጋር በስልክ መወያየታቸውን የሱዳን መንግሥት የዜና ምንጭ የሆነው ሱና አስታውቋል። 

በውይይታቸውም በሁለቱ አገሮች መካከል ትብብርን ለማጠናከርና በቀጣናዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን እንዲሁ የዜና ምንጩ አክሏል፡፡

የሦስቱ አገሮች ቀጣይ ውይይት በሚጀመርበት ታኅሳስ 26 ቀን የሱዳን ተደራዳሪዎች ምከንያታቸውን ሳያሳውቁ የቀሩ ሲሆንበዚህ ዕለት ግን የህዳሴ ግድቡን አጀንዳ ከሚመሩት የግብፅ ባለሥልጣናት መካከል ቁልፍ ናቸው የሚባሉትን የግብፅ የደኅንነት ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል አባስ ካመልን ሱዳን በካርቱም ተቀብላለች። 

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባል የግብፅና የሱዳን ወቅታዊ ጥምረት፣ በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታና አለመረጋጋት ላይ የተመሠረተና ጉልበት ለማግኘት የሚተጋ እንደሆነ ገልጸዋል። 

በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ትኩረት ከህዳሴ ግድቡ ውጪ ሆኖ በበርካታ የውስጥ ጉዳዮች ላይ እንዲበተን ማድረግ ነው ብለዋል። 

ይህ የሁለቱ አገሮች ወቅታዊ ጥምረት መሠረታዊ ፍላጎት ሲሆን የአጭር ጊዜ ግብ አድርገው ያስቀመጡት ደግሞ፣ የህዳሴ ግድቡን አጀንዳ ከአፍሪካ ኅብረት እጅ እንዲወጣ ለማድረግ ጊዜመግደል መሆኑን ባለሙያው ይገልጻሉ።

የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሲሪል ራማፎዛ የሥልጣን ዘመን በዚህ ወር መጨረሻ ላይ የሚያበቃ በመሆኑ ድርድሩ እንዲጓተትወሩም ያለ ውጤት ተጠናቆ፣ የህዳሴ ግድቡ አጀንዳ ወደ ተመድ የፀጥታ ምክር ቤት እንዲመለስ የተሸረበ የሁለትዮሽ ሴራ መሆኑን ገልጸዋል። 

በአሜሪካ መንግሥት በኩል የህዳሴ ግድቡን አጀንዳ ይዘው የነበሩት የአሜሪካ ትሬዠሪ ዲፓርትመንት ኃላፊ ስቴቨን ሙንሺን፣ በዚህ ሳምንት ለይፋ የሥራ ጉብኝት ሱዳን እንደሚገቡ ተሰምቷል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -