የልደት በዓል አዲስ አበባ ውስጥ ሰላማዊና በተረጋጋ መንፈስ ቢያልፍም በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በደረሰው የእሳት ቃጠሎ ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ንብረት ወድሟል፡፡ በተሽከርካሪ አደጋም በአምስት ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ እንዳሉት፣ በዓሉ በሰላም ያለፈው በየወረዳው ያሉት የፖሊስ አባላት ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረጋቸውና በዚህም እንቅስቃሴ ላይ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ በመታከሉ ነው፡፡
አዲስ አበባ 833 ቀጣናዎች እንዳሉት፣ በእያንዳንዱም ቀጣና 70 ወጣቶች ፀጥታን በማስፈን ሥራ ላይ እንደተመደቡ፣ የተመደቡት ወጣቶች አብረዋቸው ከተሰለፉት ፖሊሶች ጋር በቁጥጥሩ ሥራ ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡
በበዓሉ ዋዜማ የተከናወነው የቅስቀሳና የጉትጎታ ሥራ እንዲሁም ለወጣቶቹና ለፖሊሶቹ ሰላምና ፀጥታን በተመከተለ ማብራሪያ መሰጠቱ ለተገኘው ውጤት ተጨማሪ ዕገዛ ማድረጉን አክለዋል፡፡
በበዓሉ ዋዜማ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በደረሱት የተሽከርካሪ አደጋዎች ሳቢያ አራት ሰዎች ቀላል አንድ ሰው ደግሞ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ከኮማንደር ፋሲካ ጠቁመዋል፡፡
በቦሌ፣ በቂርቆስና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ በመኖርያና የንግድ ቤቶች ላይ በተከሰተው የእሳት አደጋ ከሦስት ሚሊዮን 500 ሺሕ ብር በላይ የሚያወጣ ንብረት መውደሙን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ ገልጸዋል፡፡
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 መሿለኪያ ወይም ቄስ ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በመኖሪያና በንግድ ቤቶች ላይ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ 3,500,000 ብር የሚያወጣ ንብረት መውደሙን አመልክተዋል፡፡
በቦሌ ክፍል ከተማ ወረዳ 12 ውስጥ 93 ቁጥር ማዞሪያ አካባቢ በአንድ መኖሪያ ቤት በተለኮሰ ሻማ ሳቢያ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ 50,000 ብር፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍል ከተማ ወረዳ 3 አጀባ ኮንዶሚኒየም በሚገኝ አንድ ቤት ላይ መንስዔው ባልታወቀ ምክንያት በተከሰተው የእሳት ቃጠሎ 40,000 ብር የሚያወጣ ንብረት ከጥቅም ውጪ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አመስት ሦስት ቁጥር ማዞሪያ እንዲሁም በዚሁ ወረዳ በሌላ ቦታ በሚገኙ የደረቅ ቆሻሻ ክምሮች ላይ የእሳት ቃጠሎ ተከስቶ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳያደርስ ወዲያውኑ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ አቶ ጉልላት ገልጸዋል፡፡
የእሳት አደጋዎቹን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ከ200 ሺሕ ሊትር በላይ ውኃ የተረጨ ሲሆን፣ 150 የሚጠጉ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችና 30 ከባድና ቀላል ተሽከርካሪዎች ተሰማርተዋል፡፡
ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ ፖሊሶች ጋር ተቀናጅተው ባካሄዱት እንቅስቃሴ መሆኑን የቡድን መሪው አመልከተው፣ በዚህ ዓይነቱም እንቅስቃሴ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ከውድመት ማትረፋቸውን በሰውና በእንስሳት ሕይወት ላይ ጉዳት አለመድረሱን አስረድተዋል፡፡