Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊገደብ ያጡ አጭር የጽሑፍ መልዕክቶች

ገደብ ያጡ አጭር የጽሑፍ መልዕክቶች

ቀን:

ለብዙዎች የሁልጊዜ ምሬት ከሆነ ሰንብቷል፡፡ አንዳንዴም ግለሰቦች በማያገባቸው ጉዳይ ላይ መልዕክት ሲላክላቸው በንዴት ሲናገሩ ይሰማል፡፡

አገልግሎቱን ለመጠቀም ሲፈልጉ እንኳን ከስልካቸው ምን ያህል ገንዘብ እንደሚቆረጥና አገልግሎቱን በምን መልኩ ማቋረጥ እንዳለባቸው በወቅቱ የሚያሳውቅ ባለመኖሩ ግራ የሚያጋቡ በርካቶች ናቸው፡፡ ጉዳዩ በደንብ ሳይገባቸው ኦኬ (Ok) ብለው የላኩ ደግሞ የሞባይል ስልክ ካርድ ሳይሞሉ ቆይተው አንድ ቀን ሲሞሉ ገንዘባቸው በተላከው የመልዕክት ብዛት ተቆርጦባቸው ምክንያቱን ባለማወቅ ‹‹ቴሌ በላኝ›› የሚሉም በርካታ ናቸው፡፡

‹‹ኦኬ›› ብለው ልከው እንዴት ማቋረጥ እንዳለባቸው መረጃው የሌላቸው፣ ከሞባይል ስልካቸው ገንዘብ እየተቆረጠ መሆኑን የሚያውቁት ካርድ ሲሞሉ እንደሆነና የተሞላው ካርድ በሙሉ ተቆርጦባቸው የሚያውቁም አሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ያለ ፈቃድ የሚገቡ አጭር የጽሑፍ መልዕክቶች በኢትዮጵያ ብቻ ባይሆንም፣ እ.ኤ.አ. በ2019 ‹‹ትሩኮለር›› የተባለው የጥሪና የአጭር መልዕክት አጣሪ ድርጅት የተሠራው ጥናት፣ ያለፍላጎት የሚገቡ የስልክ መልዕክቶች ከሚፈነጩባቸው አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ የመጀመርያዋ ናት ብሏል፡፡ በዚህም በወር በአማካይ 119 ያልተፈለጉ መልዕክቶች በአንድ ሰው ሞባይል ስልክ ሊላክ እንደሚችል ያስቀምጣል፡፡ ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ደቡብ አፍሪካን በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ኬንያን አስቀምጧል፡፡፡

የአጭር ጽሑፍ መልዕክት (Hot Line) አገልግሎት ኢትዮ ቴሌኮም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ከሚሠራቸው ሥራዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡

አጋር ድርጅቶቹ ለሚልኩት የመልዕክቶች ይዘት ኃላፊነት ሲወስዱ፣ መልዕክቶቹን በመፈተሽም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የሚሠሩ ከ500 በላይ ተቋማት አሉ፡፡ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ደግሞ ፈቃድ የመስጠቱን ኃላፊነት ተረክቦ እየሠራ ይገኛል፡፡ ግንዛቤው አናሳ በሆነበት፣ የተለያዩ መልዕክቶች በተለያዩ ቋንቋዎች በሚላኩበትና ሕገወጥነት በሚታይበት የጽሑፍ መልዕክት አገልግሎት ላይ የኢትዮ ቴሌኮም የሽያጭ ክፍል ዋና ኃላፊ ለሪፖርተር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡   

በአጭር የጽሑፍ መልዕክት አገልግሎት መስጠት የሚፈልግ ድርጅት በመጀመርያ ከቴሌኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ፈቃድ ማምጣት እንዳለበት ዋና ኃላፊው አቶ መሐመድ ሐጂ ተናግረዋል፡፡

ፈቃድ ይዘው ስለመጡ ብቻ ሳይሆን በዚህ አገልግሎት መሥራት የሚፈልጉ ድርጀቶች ደግሞ ማሟላት ያለባቸው መሥፈርቶች አሉ፡፡ ኃላፊው በምሳሌነትም ያነሱት ንግድ ፈቃድና የምዝገባ ወረቀት፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) ክፍያ ከፋይ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ሰነዶች ማሟላት ሲችሉ ነው፡፡ ለ30 ቀናት ሊሰጡ የሚችሉትን አጭር የጽሑፍ መልዕክቶች መገምገምና ማሻሻልም ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የነበረው የምዝገባ አካሄድ በአጋር ድርጅቶች በኩል ሲሠራ እንደነበር፣ በዚህም ብዙ ድርጅቶች ከደንበኞች ላይ ያልተገባ ጥቅም ሲያገኙ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዓመት በፊት የነበረው አሠራር ምዝገባውን የሚያከናውት ድርጅቶቹ በራሳቸው ሲስተም መሠረት በመሆኑ፣ አንድ ደንበኛ ያለ ግለሰቡ ፈቃድ ምዝገባውን አከናውኖ ገንዘብ መቁረጥ ይችል እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

ከዚያ በኋላ ግን የኢትዮ ቴሌኮም ሰርቪስ ዴቨሎፕመንት ፕላት ፎርም ዘርግቶ ደንበኞች በፍላጎት ኦኬ ብለው ካልላኩ በስተቀር አገልግሎቱን መስጠትም ሆነ ገንዘብ መቁረጥ እንዳይቻል የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን አሁን ላይ ገንዘብ ተቆርጦብናል ብለው የሚመጡ ደንበኛ ቁጥር የለም ማለት እንዳልሆነና ብዛት ያላቸው ደንበኞች ቅሬታቸውን እንደሚያሰሙ ገልጸዋል፡፡ አቶ መሐመድ እንዳስረዱት፣ ቀደም ብለው ተመዝግበው ሲሠሩ የነበሩ ድርጅቶች እስካልወጡ ድረስ፣ ግለሰቡ ኦኬ (Ok) ብለው ከላኩት ገንዘብ ይቆርጥባቸዋል፡፡

ለደንበኞች የሚደርሱት አጭር የጽሑፍ መልዕክት ይዘቶች ማስታወቂያ መሆናቸውን የማያስረዱት ኃላፊው፣ ብር የሚቆርጡ እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡ ብር ሊቆርጡ የሚችሉት ደንበኛው ተስማምቶ ኦኬ ብሎ ከላከ ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮ ቴሌኮም ሕግ መሠረት የአጭር ጽሑፍ መልዕክት አገልግሎት ማስተዋወቂያው ጭምር ያለ ደንበኛው ፍላጎት መላክ የለበትም፡፡  

አገልግሎቱን የሚሰጡ 671 ድርጅቶች ሲኖሩ፣ ከሕግ አግባብ ውጪ መልዕክት የሚልኩ ሆኖም ማንኛውም ደንበኛ ያለ ፍላጎቱ መልዕክት ያለመቀበል መብት አለው፡፡

ይህን ተላልፈው የተገኙ ድርጅቶች የሚወሰዱባቸው ዕርምጃዎች መኖሩንና ያለ ደንበኛ ፍላጎት የሚልኩ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ሕጋዊ ያለመሆን ችግር ሳይሆን ሕግ ተላልፈው የሚሠሩ ድርጅቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ብዙ ድርጅቶች ላይ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያም ተሰጥቷል፡፡ ለአሥራ አምስት ቀናት አገልግሎት እንዲቋረጥባቸው የተደረጉም፣ ለሁለተኛ ጊዜ ሕጉን በጣሱ ላይ ደግሞ 75 ሺሕ ብር ቅጣትና ለ30 ቀናት አገልግሎቱ እንዲቋረጥ የሚደረግ ሲሆን፣ ለሦስተኛ ጊዜ ሕግ የሚጥስ ድርጅት ካለ 50 ሺሕ ብርና እስከ መጨረሻው ከአገልግሎቱ እንዲታገድ እንደሚደረግ አቶ መሐመድ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ 

 ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በተወሰዱ ዕርምጃዎች 141 ድርጅቶች የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 54 ድርጅቶች የብር ቅጣትና 49 የሚሆኑት ደግሞ ሙሉ በሙሉ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ያላቸውን ውል እንደተቋረጠ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

አጭር የፅሑፍ መልዕክቶች አገልግሎት ለመስጠት አገልግሎት ሰጪዎች ኃላፊነት እንዲወስዱ የሚደረግ ሲሆን፣ አገልግሎቱ የተሰጠው በግለሰቡ ፍላጎት መሆኑንና አለመሆኑን ማወቅ የሚቻለው ደግሞ በኅብረተሰቡ ጥቆማ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአቶ መሐመድ ገለጻ፣ ዕርምጃ አወሳሰዱ ከደንበኞችና ከኅብረተሰቡ ከሚሰጠው ጥቆማ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በሌላ በኩል ድርጅቶች የተለያዩ ማስታወቂያዎች ሲያስነግሩ ለደንበኞች ሙሉ መረጃ እንዲያቀብሉ ቢታመንም፣ በአመዛኙ ስለሚሰጡት መረጃ እንጂ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚቆርጥና ኅብረተሰቡ አገልግሎቱን እንዴት ማቋረጥ እንዳለበት አይገልጹም፡፡  

በመሆኑም ኢትዮ ቴሌኮም ግምገማ አከናውኖ ለድርጅቶቹ ማሳወቁን ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

ብሮድካስትና ሌሎች ሚዲያዎችን በመጠቀም የተሳሳቱና ከፕሮፖዛላቸውና ከተፈቀደላቸው አገልግሎት ውጪ ይዘት ያላቸው ማስታወቂያዎች በመሥራት ደንበኞችን በተሳሳተ መረጃና መንገድ እንዲመዘገቡ ማድረግ እንደሚከለክል ተገልጿል፡፡

በየትኛውም የማስታወቂያ መንገዶች እየተሰጡ ያሉ አገልግሎቶች ክፍያ ያላቸው መሆኑን ከመግለጽና ከማሳወቅ አኳያ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች መኖራቸውን አቶ መሐመድ ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ መልዕክቶች በነፃ ይመዝገቡ የሚል እንጂ ፣እንዴት አገልግሎት ማቋረጥ እንዳለባቸው የማይገልጹ መሆኑን የጠቆሙት አቶ መሐመድ፣ በምሳሌነትም በአንድ ብሮድካስት ሚዲያ የሚያስተዋወቅ አንድ አጋር ድርጅት ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ እንቅስቃሴ መጀመሩን ያክላሉ፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ከሚያገኘው ገቢ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝንም ይገልጻሉ፡፡ በ994 ላይ ከሚመጡ ጥሪዎች መካከል ሁለተኛ ደረጃ የሚይዘው የአጭር የጽሑፍ የመልዕክት ቅሬታዎች ናቸው፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ጥሪዎች የሚመጡ ሲሆን፣ ኢትዮ ቴሌኮም እነኚህን ጥሪዎች ለማስተዳደር የሰው ኃይል፣ የሲስተምና የጊዜ ኢንቨስትመንት በመኖሩ ከሚያገኘው ገቢ ይልቅ የሚያወጣው ወጪ ከፍ እንደሚል ይናገራሉ፡፡

ነገር ግን ይህንን አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ መዝጋት አይቻልም፡፡ እንደ ብቸኛ ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ሰጪነት ሲታይም የህዳሴ ግድብ፣ መቄዶንያ፣ የኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥንና መሰል ለአገር የሚጠቅሙ ድርጅቶች ስላሉ ጥቅሙን ሳይሆን አገልግሎቱን ማየት ይገባል ብለዋል፡፡

ዘርፉ ብዙ የቴሌኮም አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ በሚያደረገው ኢትዮ ቴሌኮም ውስጥ ብዙ ቅሬታ ይዞ የሚመጣው አጭር የጽሑፍ መልዕክት አገልግሎት ነው፡፡ ነገር ግን የአጭር የጽሑፍ መልዕክት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ከአንድ ሚሊዮን በታች ሲሆን፣ ከሌሎች አገልግሎቶች አኳያ ትንሽ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ከዚህ በፊት ሙሉ በሙሉ ሲስተሙ አጋር ድርጅቶች ዘንድ መሆኑን ያስታወሱት አቶ መሐመድ፣ አሁን ያለው የመቆጣጠሪያ ሥርዓት ያለው አቅም ካሉት ደንበኞች ብዛት አንፃር ዝቅ ያለ መሆኑንና ምንም እንኳን የመቆጣጠሪያ ሥርዓት መጥበብ ቢኖርም እየተቆጣጠረ ኅብረተሰቡን ካላስፈላጊ ወጪ ለመታደግ እየጣረ ይገኛል ብለዋል፡፡

የገቢ ተፅዕኖና ደንበኞች ጋር የመድረስ ውስንነት ቢኖረውም፣ ኢትዮ ቴሌኮም እየተቆጣጠረ ደንበኞች ያላግባብ ገንዘባቸው ሳይወሰድባቸው መረጃ ማግኘት እንዲችሉ መምረጡን አቶ መሐመድ አስረድተዋል፡፡

ከ500 ሺሕ እስከ 600 ሺሕ የአጭር የጽሑፍ መልዕክት ተገልጋዮች ሲኖሩ በይበልጥ የሚጎዱት አገልግሎት ሰጪዎች ናቸው የሚሉት አቶ መሐመድ፣ አንዴ ለብዙ ቡድኖች መልዕክት ሲልኩ ገንዘብ ይቆርጥባቸዋል፡፡ ከዚያም መልዕክቱን ተቀብሎ ኦኬ ብሎ የሚልከው የሰው ቁጥር አነስተኛ ስለሚሆን ኪሳራው ለድርጅቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም የመክፈል አቅማቸው እየተዳከመ የመጡ ድርጅቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በማጭበርበር ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች በራሳቸው ጊዜ ራሳቸውን ከቢዝነስ ውስጥ እያወጡ ይሄዳሉ የሚሉት አቶ መሐመድ፣ አንድ ደንበኛ ገንዘብ ሊቆረጥበት የሚችለው በተላኩ የአጭር ጽሑፍ መልዕክት ልክ ብዛት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥን በቅርቡ እንዳሳወቀው አንድ ሰው በአጭር የጽሑፍ መልዕክት አንዴ ሲልክ በቀን አንድ ብር ይቆረጥበታል፡፡ ነገር ግን ማቋረጥ ከፈለገ ደግሞ በቀላሉ ቁጥሩን በመጻፍ ስቶፕ (Stop) ብሎ በመላክ አገልግሎቱን ማቋረጥ እንዲችሉ ያደርጋል፡፡ ሌሎች የአጭር የጽሑፍ መልዕክት አገልግሎቶች ያለ ግለሰብ ፈቃድ በስልክ ከተላከለት ሕገወጥ አሠራር በመሆኑ ደንበኛው በ994 በመደወል ቅሬታ ማቅረብ እንደሚችሉ ይገልጻሉ፡፡

በኢትዮ ቴሌኮም ሲስተም መዘግየትና መጨናነቅ ምክንያት ተገልጋዮች እንዴት ማቋረጥ እንዳለባቸው የማቋረጫ መልዕክት የማይደርስ ሲሆን፣ በጊዜ ሒደት ሲስተሙን ለማዘመን እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የነበረው አጭር የጽሑፍ መልዕክት ብቻ እንደነበር የገለጹት ኃላፊው፣ አሁን ላይ ደግሞ ዲጂታላይዝድ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ጌም መግዛትና መጫወት እንዲሁም በቅርቡ ይፋ የተደረገው የአውታር መተግበሪያ ተካቷል ብለዋል፡፡

በሌሎች አገሮች እጅግ የተለመደው የዲጂታል መልዕክት አገልግሎት በኢትዮጵያ የተጀመረ ቢሆንም፣ ካለው የሕዝብ ንቃተ ህሊና አንፃር ከአውታር የሙዚቃ መተግበሪያ መልዕክት ውጪ አገልግሎት የሚሰጥ የለም፡፡

ከዚህ በፊት የሰብስክሪብሽን ሊንክ በፌስቡክና በዩቲዩብ ይቀመጥ ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን ሰዎች ወደውና ፈቅደው ሲሆን ብቻ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...