Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢትዮጵያና በኢንዶኔዥያ 346 ሰዎች ያለቁበት የማክስ አውሮፕላን አምራች ቦይንግ ኩባንያ ቅጣት ተጣለበት

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከአሜሪካ ደኅንነትና የጥንቃቄ ባለሙያዎች መረጃዎችን መደበቁ የተደረሰበትና ክስ ተመሥርቶበት የነበረው የቦይንግ 937 ማክስ8- አውሮፕላን አምራች ኩባንያ፣ ጥፋቱን ማመኑንና የተመሠረተበትን 2.5 ቢሊዮን ዶላር ቅጣት ለመክፈል መስማማቱ ታወቀ፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ፣ ለስድስት ደቂቃ ብቻ እንደነበረረ በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ ኤጀሬ ወረዳ ቱሉ ፈራ ቀበሌ በመውደቁ፣ በውስጡ የነበሩ 17 ኢትዮጵያውያንና 32 ኬንያውያንን ጨምሮ የቻይና፣ የጣሊያን፣ የካናዳ፣ የአሜሪካ፣ የፈረንሣይና የሌሎች አገሮች ዜጎች በአጠቃላይ 157 ሰዎች በሙሉ ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፡፡

በቦይንግ ኩባንያ የተሠራው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን በኢንዶኔዥያ በተመሳሳይ ዓመት ጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ኤጃሻ በሚባል ባህር ውስጥ ገብቶ 189 ሰዎች ማለቃቸውም አይዘነጋም፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ አውሮፕላኑን የገዙ በመላው ዓለም ያሉ አገሮች አውሮፕላኑ እንዳይበር ማገዳቸውም ይታወሳል፡፡

ኩባንያው ማሳወቅ የነበረበትን መረጃ ለአሜሪካ የደኅንነት ተቋም፣ ለአብራሪዎችና ለቴክኒሻኖች ግልጽ ማድረግ ሲገባው አለማድረጉን፣ የአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ በማረጋገጡ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ቅጣት እንደተጣለበትና ኩባንያውም ለመክፈል መስማማቱን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ባለፈው ሳምንት ውስጥ ዘግበዋል፡፡

ቦይንግ ኩባንያ ከተጣለበት የቅጣት ገንዘብ ውስጥ 500 ሚሊዮን ዶላር በተከሰከሱ አውሮፕላኖች ሕይወታቸውን ላጡት ቤተሰቦች የሚከፈል ሲሆን፣ ከአውሮፕላኖች የደኅንነት መጓደል ጋር በተያያዘ ለፈጸማቸው ጥፋቶች ደግሞ 243.6 ሚሊዮን ዶላር እንደሚከፍልም ተጠቁሟል፡፡

የቦይንግ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ሚስተር ዴቪድ ካልሁን ቅጣቱን አስመልክተው፣ ‹‹ወደ ስምምነት መግባታችን ትክክለኛው ነገር እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ይህም ከእሴቶቻችንና ከሚጠበቅብን ምን ያህል ወደኋላ መቅረታችንን ያሳያል፤›› ሲሉ፣ የአሜሪካው ፍትሕ ቢሮ ደግሞ፣ ‹‹ይህ ስምምነት ኩባንያው ምን ያህል ጉድለት እንዳለበት የሚያሳይ ነው፡፡ ለማንኛውም ኩባንያው ከግልጽነት ልቅ ትርፉን አስቀድሟል፤›› ማለቱን ዘገባዎቹ ያሳያሉ፡፡ የቦይንግ ክፍተኛ የሥራ ኃላፊ አክለውም ስምምነቱ ሁሉንም የሚያስታውሰው ለግልጽነት የተገባው ግዴታ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡

ቢሮው በበኩሉ እንደገለጸው፣ የቦይንግ ባለሥልጣናት በኢንዶኔዥያና በኢትዮጵያ ለአውሮፕላኑ መከስከስ ምክንያት ስለሆነው ‹‹ኤምካስ›› ስለተባለው አውቶማቲክ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት ላይ ስለተደረገው ለውጥ መረጃ ደብቀዋል፡፡

የአውሮፕላን አብራሪ ሥልጠና መመርያ ስለ ሥርዓቱ በቂ መረጃ ባለመያዙ፣ በተሳሳተ መረጃ የአውቶማቲክ ሥርዓቱ የአብራሪውን ውሳኔ እንደሚሽረው፣ አውሮፕላኑ ከማኮብኮቢያው በተነሳ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ አፍንጫውን ዘቅዝቆ ቁልቁል እንዲምዘገዘግ እንደሚያደርገው የቢሮው ውሳኔ እንደሚያሳይ ተገልጿል፡፡ ቦይንግ ጉዳት ካደረሰ በኋላም ለስድስት ወራት ያህል ለምርመራ ባለሙያዎች ትብብር አለማድረጉንም ቢሮ አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች ጥብቅና የቆሙ የሕግ ባለሙያዎች ቦይንግ ኩባንያ ክሱን አምኖ ለመክፈል ስምምነት ቢያደርግም፣ የመሠረቱትን ክስ እንዲያቋርጡ እንደማያደርጋቸው እየገለጹ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ ሁሉም የኩባንያው 737 ማክስ አውሮፕላኖች ደኅንነት በገለልተኛ ወገን ተፈትሸው መስተካከላቸው እስከሚረጋገጥ ድረስ፣ ወደ በረራ እንዲገቡ መፈቀድ እንደሌለበት ባለሙያዎቹ እየገለጹ ቢሆንም የአሜሪካ ደኅንነት ተቆጣጣሪዎች፣ ‹‹አውሮፕላኖቹ ለበረራ ዝግጁ ናቸው፤›› በማለታቸው፣ ካለፈው ታኅሳስ ወር ጀምሮ ወደ ሥራ መመለሳቸው ታውቋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች