Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትከኦሊምፒክ ተሳትፎ የራቀው የኢትዮጵያ ቦክስ

ከኦሊምፒክ ተሳትፎ የራቀው የኢትዮጵያ ቦክስ

ቀን:

በኢትዮጵያ የቀደመ ታሪክ ካላቸው ስፖርቶች ቦክስ አንዱ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ውጤት ከራቃቸው ተርታ ከሆነ ዘመን አስቆጥሯል፡፡ ቦክስ ከአትሌቲክስ ቀጥሎ እስከ ለንደን በተለያዩ ኦሊምፒኮች ላይ አልፎ አልፎ ኢትዮጵያ ስትወከልበት የቆየ ስፖርት መሆኑ ይወሳል፡፡ ይሁንና ስፖርቱን ከሚመራው ብሔራዊ ተቋሙ እስከ ታች ክለቦች ድረስ ከጊዜውና ከወቅቱ ጋር ተጣጥሞ መራመድ የሚችል መዋቅር ብቻ ሳይሆን ለስፖርቱ ውጤታማነት ትልቅ ድርሻ የነበራቸው በሠራዊቱ ይደገፉ የነበሩ ክለቦች እየተዳከሙ መምጣታቸው ለውድቀቱ ምክንያት መሆናቸው የሚናገሩ አሉ፡፡

ስፖርቱ በተለይም ከለንደን ኦሊምፒክ በኋላ በአፍሪካ ደረጃ የሚደረጉ ማጣሪያዎች ለኦሊምፒክ ተሳትፎው መገደብ ዓይነተኛ ምክንያት ተደርጎ የሚቀርብበት አጋጣሚ እንዳለ የሚናገሩ በአንድ በኩል፣ በሌላ ገጽ ደግሞ በዚህ ጉዳይ የማይስማሙ የዘርፉ ሙያተኞችም አልጠፉም፡፡

ብዙዎቹ ለስፖርቱ መዳከም አንዱና መሠረታዊ ተብሎ ሊወሰድ የሚገባው ቀደም ባሉት ዓመታት በሠራዊቱ መካከል ይደረጉ የነበሩ የውስጥ ውድድሮች እየተዳከሙ መምጣታቸው፣ ሌላው ደግሞ ቀድሞ ክለብ የነበራቸው እንደ ኢትዮጵያ ቡና፣ ሕዝብ ማመላለሻ፣ ሕንፃ ኮንስትራክሽንና የመሳሰሉት ተቋማት ክለቦቻቸው እንዲፈርሱ መደረጉ፣ ከዚሁ ጎን ለጎን የፋይናንስ አቅም ውስንነት ተፎካካሪነቱ እንዲዳከም ምክንያት እየሆነ መምጣቱን በመከራከሪያት ያቀርባሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ከተሟሉ በኢትዮጵያ ቀድሞ  የነበረውን ቦክስ ለመመለስ ብዙም ችግር እንደማይሆን ጭምር ያምናሉ፡፡  

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ስፖርቱን ወደ ቀድሞ ስምና ዝናው ለመመለስ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ የተለያዩ ዕቅዶችን በማውጣት እንቅስቃሴ መጀመሩን ይናገራል፡፡ ከዕቅዶቹ መካከል በክልል ደረጃ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ በአማራ ክልል በጎንደርና ደሴ ከተሞች፣ ከደቡብ ክልል በሆሳዕና፣ በአላባ፣ በአርባ ምንጭና በወላይታ ከተሞች ወጣቶችን መነሻ ያደረጉ ክለቦች እንዲቋቋሙ በማድረግ በአኅጉር ደረጃ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ወጣቶች አካዴሚ ያፈራቸው ወጣት ቦክሰኞች በሞሮኮ አስተናጋጅነት በ2011 ዓ.ም. በተካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮና ላይ ከወርቅ እስከ ነሐስ፣ እንዲሁም በዚያው ዓመት በናይጀሪያ በተካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሊምፒክ ላይ በተመሳሳይ ከወርቅ እስከ ነሐስ ሜዳሊያ መመዝገቡ የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ያደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና ስፖርት ኮሚሽን ከፍተኛ የፋይናንስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጭምር ፌዴሬሽኑ አልሸሸገም፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ቀደም ሲል ስፖርቱን ተጫውተው ያሳለፉ፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በተለያየ የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሀብቶችን በአመራር ሰጪነት ጭምር እንዲያገለግሉ እያደረገ ስለመሆኑ ጭምር ያስረዳል፡፡ ከእነዚህ አመራሮች የቀድሞ ቦክሰኛ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በሆቴልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙት አቶ ኢያሱ ወሰን አንዱ ናቸው፡፡ ባለሀብቱ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን በቅርቡ ባደረገው ፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል፡፡

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ይህን ትልቅ ኃላፊነት ከመረከባቸው በፊት ስፖርቱን አቅማቸው በፈቀደ መጠን በዕውቀትም ሆነ በገንዘባቸው ዕገዛ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡ በዋናነት ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ቦክሱን ወደ ቀድሞ ስምና ዝናው ለመመለስ በአሁኑ ወቅት በተለየየ የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሀብቶችን በማሰባሰብ ስፖርቱን እንዲያግዙ ጥረት በማድረግ ላይ ሲሆኑ፣ ቀደም ሲል በተለያዩ የክልልና የከተማ አስተዳደር ከተሞች እንዲመሠረቱ የተደረጉ ክለቦች የዚህ እንቅስቃሴ ውጤቶች መሆናቸውን ጭምር ባለሀብቱ ያስረዳሉ፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቱ ከሆነ በእሳቸውና በፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች አማካይነት ከሦስት ዓመት በፊት በተጀመረው እንቅስቃሴ ቦክሱን ወደ ነበረበት ለመመለስ በተደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ውጤት መታየት ጀምሯል፡፡ በ2011 የውድድር ዓመት በአኅጉር ደረጃ በተደረጉ ሻምፒዮናዎች ከወርቅ እስከ ነሐስ የተመዘገቡት ሜዳሊያዎች የዚህ ማሳያ መሆናቸው እርግጥ ቢሆንም የነበረውን ማስቀጠል አልተቻለም፡፡ እንደ ኃላፊው፣ ‹‹የኮቪድ 19 ወረርሽኝ›› ተጀምሮ የነበረውን እንቅስቃሴ በታቀደው ልክ እንዳይጓዝና የተሻለ ሥራ እንዳይሠራ የአጋጣሚውን መጥፎነት ያስረዳሉ፡፡

በሌላ በኩል ለቦክስ ውድቀት የፋይናንስ ውስንነት እንደ ተጠበቀ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እንደ ተቋም ወቅቱን የሚመጥን አደረጃጀት አለመላበሱ ተጨማሪ ተግዳሮት እንደሆነ የሚያምኑ አሉ፡፡ ይህን የሚጋሩት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት፣ ‹‹እንደ አለመታደል ሆኖ የአገራችን አትሌቶች ባይታደሉም፣ ቦክስ በዓለም ላይ ትልቅ ገንዘብ ከሚያስገኙ ዘርፎች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ብዙዎች ቢሊየነር ሆነውበታል፡፡ የሚገርመው ስፖርቱ በእኛ ጊዜ ከትምህርት ቤት ጀምሮ ወረዳና አውራጃ እያለ በየደረጃው ከፍተኛ ፉክክር ይደረግበት የነበረ ስፖርት ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ያ ነገር ፈጽሞ እየተቀዛቀዘ መምጣቱ ችግሩ እንዲባባስ አድርጎታል፡፡ ችግሩ በቀላሉ ይፈታል የሚል እምነት ባይኖረኝም በተወሰነ መልኩም ቢሆን በዋናነት ጎልቶ የወጣውን የፋይናንስ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ጀምረናል፡፡ በተለይ ቀደም ሲል በቦክስ ስፖርት ተሳታፊ የነበሩ እንደ መከላከያ የመሳሰሉ ተቋማት ቡድን እንዲያቋቁሙ የማግባባት ሥራ እየሠራን ነው፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

ብሔራዊ የቦክስ ፌዴሬሽን በቅርቡ ባከናወነው ምርጫ ፕሬዚዳንት መሆናቸውን የሰሙት በሚዲያ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ወሰን፣ ‹‹እኔ ብመረጥም ባልመረጥም ቦክስ እንዲቀጥል እፈልጋለሁ፡፡ አጋጣሚው ፈቅዶ መመረጤ በተሻለ ኃላፊነት እንድንቀሳቀስ የሚያግዘኝ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ቦክስ ትልቅ ስፖርት ነው፣ መንግሥትም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ስፖርቱ መቀጠል እንዳለበት ያምናል፣ የአስር ዓመት መሪ ዕቅድ ወጥቷል፣ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ይህ የሚያሳየው ስፖርት እንደ ቀድሞ የመንግሥትን በጀት ሳይጠብቅ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በተለይ የአመራሮቹ ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ እኛም እንደ ቦክስ ዕቅዶቻችን እንዲሳኩ ለውጪ ሙያተኞች ሰጥተን እንዲጠኑና ወደ መሬት እንዲወርዱ የማድረግ ሥራዎችን ጀምረናል፤›› በማለት የተቀበሉት ኃላፊነት በቀላሉ የሚታለፍ አለመሆኑን ጭምር ያሰረዳሉ፡፡

‹‹ስፖርት በብዙዎቹ አገሮች ትልቅ ቦታ ተሰጥቶት በጦርነት የሚፈላለጉ አገሮች የሚቀራረቡበት ብቻ ሳይሆን፣ ማኅበራዊ ግንኙነታቸው የሚጠናከርበት ትልቅ መድረክ እየሆነ ነው›› የሚሉት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት፣ ‹‹ይህንኑ በአገራችን ማስረጽ ይኖርብናል፤›› በማለት በኢትዮጵያ ለስፖርት የሚሰጠውን የተዛባ ትርጉምና ግንዛቤ ይተቻሉ፡፡

እየፈረሱ የነበሩ ክለቦች እንደገና እንዲቋቋሙ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሚናገሩት ኃላፊው፣ ፌዴሬሽኑ ስፖርቱን ወደ ቀደመ ስሙ ለመመለስ ክለቦችን በሁሉም ክልልና የከተማ አስተዳደር እንዲቋቋሙ ያቀረበው ጥያቄ አሁን ባለው ሁኔታ ፍሬ እያፈራ እንደሆነና የሚቀረው ይህንን ሊመልስ የሚችል የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ብቻ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

በመጨረሻም ከሩሲያዊው የዓለም አቀፉ ተቋም ፕሬዚዳንት ጋር ጠንካራ ግንኙት መፍጠራቸውን ያከሉት አቶ ኢያሱ፣ ለቦክስ ባለሙያዎች የሙያ ማሻሻያ ሥልጠናን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርጉላቸው ቃል የገቡላቸው ስለመሆኑ ጭምር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...