Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ውዥንብር ያስነሳው የተጻፈበት የብር ኖት

‹‹የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ከፍተኛ ወጪ የሚያስከትል ቢሆንም፣ በአጠቃቀም ችግሮች ምክንያት ከአገልግሎት ጊዜው ቀድሞ የሚበላሸውን በርካታ ገንዘብ የሚመለከት መመርያም ተዘጋጅቷል፡፡ የብር ኖቶችና ሳንቲሞ ከፍተኛ ገንዘብ ወጥቶባቸው በውጭ ምንዛሪ ቢታተሙም፣ በአጠቃቀምና አያያዝ ጉድለት ሳቢያ እየተበላሹ ነው፡፡ ሆን ብለው የብር ኖቶችንና ሳንቲሞችን የሚያበላሹትን የሚቆጣጠር መመርያ መጥቷል፡፡ በብር ኖቶች ላይ ጽሑፍ ይጻፋል፡፡ ይቀደዳል፡፡ በተለይ በገጠር አካባቢ ከፍተኛ የአያያዝ ችግር አለ፡፡ ይህ በመሆኑ ብር ቶሎ ቶሎ እየተበላሸ  ነው፤›› ይህንን ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ሲሆኑ፣ ይኼ ንግግራቸው መንፈቅ ያልሞላው ነው፡፡

ከዚህ ጋር አያይዘውም፣ ‹‹በዚህም ምክንያት የቆይታ ዕድሜው እያጠረ ከኢኮኖሚ ውጪ የሚደረግበት አጋጣሚ እየበዛ በመምጣቱና መልሶ ለመተካት ከፍተኛ ወጪ እየጠየቀ በመሆኑ፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ውሳኔዎች ተላልፈዋል፡፡ ከአሁን በኋላ በብር ኖቶች ላይ መጻፍና ሌሎች ጉዳቶችን ማድረስ በሕግ ያስጠይቃል፤›› ብለዋል፡፡ በእርግጥም እንዲህ ያለው ማሳሰቢያ መሬት ጠብ የሚል አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ መገበያያ ገንዘብ የሆነው የብር ኖት አያያዝ ጉድለት፣ በግልጽ የሚታይ ነውና ዜጎች የብር ኖት አያያዛቸውን በወጉ እንዲያደርጉና በጥንቃቄ እንዲጠቀሙ መምከርም ሆነ ማስጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ የብር ኖት አያያዝ ራሱን የቻለ ሕግ ቢኖረውም ክፋት የለውም፡፡ ምክንያቱም በአያያዝ ጉድለት አንድ የብር ኖት ማገልገል የሚገባውን ያህል ጊዜ ሳያገለግል መቅረቱ እንደ አገር ዋጋ ያስከፍላልና፡፡

በአያያዝ ጉድለት ከግልጋሎት ውጪ የሚሆኑ የብር ኖቶቻችንን መልሶ አሳትሞ ለመተካት ወጪ አለው፡፡ ወጪው ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ይጠይቃል፡፡ እያንዳንዱ የብር ኖት ዶላር ተከፍሎበት ማሳተም ግድ ይላል፡፡ ይህም የውጭ ምንዛሪ ችጋር በሆነበት አገር የምንጠቀምበትን የብር ኖት የመገልገያ ጊዜ እያሳጠርን አገርን ላላስፈላጊ የውጭ ምንዛሪ ወጪ መዳረግ በምንም መለኪያ ተቀባይነት የለውም፡፡ ስለዚህ እንደ አንድ ኃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ የብር ኖቶቹን በጥንቃቄ መያዝና መገልገል አገርን እንደ መርዳት የሚቆጠር የዜግነት ኃላፊነት ነው፡፡

ለትልቅ ለትንሹም አገርን የውጭ ምንዛሪ ማስወጣት ተገቢ ባለመሆኑ የብር ኖት አያያዛችንን በወጉ ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡ ይህም በቀላሉ የምናደርገው እንጂ የሚከብድ አይሆንም፡፡ በአጭሩ የብር ኖር አያያዣችን ኃላፊነት የተሞላበት አለመሆን በአገር ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ጉዳት አውቆ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡

አሁን ላይ ደግሞ አገልግሎት ላይ መዋል ከጀመረ መንፈቅ ያልሞላው አዲሱ የብር ኖት በወራት ልዩነት ተቀዶና ተጎሳቁሎ ስንመለከት ሁኔታው ቢያሳስበን አይገርምም፡፡ የተለያዩ ጽሑፎች በተለይ ቁጥሮች ሠፍረውበት፣ በአያያዝ ችግር ገና በጠዋቱ የተጎሳቆሉ የብር ኖቶች ገበያ ውስጥ መታየቱም የብር ኖት አያያዛችን ምን ያህል ደካማ መሆኑንና አሁንም አገርን ላላስፈላጊ ወጪ እየዳረግን ስለመሆኑ ያመለክታል፡፡

እንዲህ ያለውን እውነት በግልጽ እየተመለከትን ባለንበት ሰዓት፣ ከሰሞኑ ባንኮችና ሱፐር ማርኬቶች የተጻፈበትንና የተጎሳቆሉ የብር ኖቶችን አንቀበልም አሉ በሚል የተፈጠረው ውዥንብር አነጋጋሪ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የተጎሳቆለ፣ የተጻፈበትና የተቀደደ ብር አንቀበልም ያሉ ባንኮች እነዚህኑ የብር ኖቶች በኤቲኤም ማሽኖቻቸው በመክተት እንዲሁም ከባንክ ዴስክ ለተገኙትም በመክፈል  ብዥታ መፍጠራቸው አስገራሚ የሚባል ተግባር ነው፡፡ 

እዚህ ላይ ምናልባት ከብዙዎች የተለየ ምልከታዬ የተጻፈበትና የተቀደደ ገንዘብ ማንቀሳቀስ እንደማይቻልና እንዲህ ማድረግ ሕገወጥ መሆኑን የሚያስገነዝበው መመርያ ተግባራዊ ባልሆነበት ባንኮች የተጻፈበትን የብር ኖት አንቀበልም ማለታቸው ላይ ደግሞ አንዳንዴ እነዚያ ተጻፈባቸው የተባሉ የብር ኖቶች በባንኮቹ ሠራተኞች ጭምር የተጻፈባቸው ላለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡ ኅብረተሰቡም በገንዘብ አያያዝ ላይ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ ነው መረጃ አለው ብሎ ለመናገርም አያስደፍርም፡፡

በሌላ አነጋገር ግን ብሔራዊ ባንክ እተገብረዋለሁ ብሎ የተሰናዳበትን መመርያ ካለመተግበሩ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ክፍተት አለ ሊባል ይችላል፡፡ ከሰሞኑ የተፈጠረውን ውዥንብር ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ደግሞ የተጻፈበትን የብር ኖት አትቀበሉ እየተባለ የሚናፈሰው ወሬ መሠረተ ቢስ መሆኑን ገልጾ፣ ነገር ግን በጣም የተጎዱ የብር ኖቶች ሲያጋጥሙ ከዝውውር ስለሚወጡበት ሁኔታ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በእኔ ግምት በዚህ ጉዳይ ላይ አሁንም ብዥታ ተፈጥሯል፡፡  

እንዲህ ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መግለጫ ብዙም ምቾት አይሰጥም፡፡ ምክንያቱም የብር ኖቱን በአግባቡ መያዝ እንደሚገባና በአግባቡ አለመያዝ የሚያስከትለውን ጉዳት በማመን፣ ተግራዊ መሆን የነበረበት የመቆጣጠሪያ ዝርዝር መመርያ ቢተገበር ምን ሊኮን ነው የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል፡፡  

ስለዚህ ከሰሞኑ በተፈጠረው መወነባበድ አንዱ ተጠያቂ ራሱ ብሔራዊ ባንክ ይሆናል፡፡ ባንኮች በሌለ መመርያ ጽሑፍ የተጻፈበት ወይም የተቀደደ ገንዘብ አንቀበልም በማለት ኅብረተሰቡን ብዥታ ውስጥ ከተዋል ማለት አይቻልም፡፡ ሳይታዘዙ ይህን አላደረጉምና፡፡ ይህ ሳያንስ አንቀበልም ያሉትን ኖት መልሰው በኢቲኤም ማሽናቸው ከተው ተጠቃሚ እጅ እንዲገባ ካደረጉ በኋላ ተመልሶ እነርሱ ጋር ሲቀርብ አንቀበልም ማለታቸውም ሌላ ችግር ነበር፡፡፡

ለዚህ የተወነባበደ ተግባር ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መግለጫ ደግሞ የእሳት ማጥፋት ዓይነት ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የተጻፈበትና የተቀደደ ብር መያዝ ያስጠይቃል የሚለው መመርያ ሲወጣ እንዴት ሊተገበር ይችላል የሚለው ነገር አሳሳቢ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

ስለዚህ ዜጎች የብር ኖቶቹን በአግባቡ መያዝ እንዳለባቸው ማስገንዘብና ማስተማር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የብር ኖት ላይ ጉዳት የሚያደርግ አካል ተጠያቂ መሆን አለበት የሚለውን እምነት እንዳያደበዝዘው ያሠጋል፡፡ ለማንኛውም ከብር ኖት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት ዘላቂ መፍትሔው ከጥሬ ገንዘብ ግብይት መውጣት ነው፡፡ ይህ ግን በአንድ ጀምበር የሚፈጠር ባለመሆኑ፣ የብር ኖቶቹ እንዳይበላሹ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት፡፡ ብሔራዊ ባንክም ግልጽ መመርያ ይኑረው፡፡

ከጥሬ ገንዘብ ግብይት ቀስ በቀስ መውጣትና ዜጎችን የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ውስጥ በማስገባት አሁን የሚታየውን የብር ኖት አያያዝ ችግር ለመቅረፍ ይቻላል፡፡ ከጥሬ ገንዘብ ግብይት እስክንላቀቅ ግን የብር ኖቶች አጠቃቀምን በግልጽ ማሳየት፣ ዝርዝር መመሪያውን ማውጣት አሠራሩን መስመር ማስያዝ ተገቢ ይሆናል፡፡ አብዛኛው ማኅበረሰብ ገንዘቡን በብብቱና በደረቱ በሚሸጉጥበት፣ በቦርሳ ከቶ አጥፎ በሚያስቀምጥበት፣ ለመደበቅ ብሎ በየቦታው በሚከትበት ሁኔታ ኅብረተሰቡን ቀድሞ ማስተማር ተገቢ ነው፡፡   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት