አዲሱ የንግድ ምክር ቤቶች መቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በደንብ መፈተሽ ያለበትና ነጋዴው የሚፈልገው አዋጅ ሆኖ እንዲወጣ የንግድ ምክር ቤቶች አመራሮች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው የቀድሞ የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤቶች ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ብርሃነ መዋ ገለጹ፡፡
አቶ ብርሃነ ተሻሻሉ የቀረበውን የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅን በተመለከተ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባሰናዳው መድረክ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት የነጋዴውን ፍላጎት የሚያንፀባርቅ አዋጅ እንዲሆን አመራሩ ከፍተኛ ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡ ከነጋዴው ፍላጎት ውጭ መንግሥት አዋጅ ካወጣም በተቃውሞ መቆም እንዳለባቸውም አሳስብዋል፡፡
አዋጁ መውጣት ያለበት ነጋዴው በሚፈልገውና የሚያሠራ መሆን አለበት፡፡ ይህንን መፈልፈል ያለበት ደግሞ አመራሩ መሆኑን የገለጹት አቶ ብርሃነ ከነጋዴው ፍላጎት ውጭ መንግሥት አዋጅ ቢያወጣ በተቃውሞ መቆም እንደሚገባቸውም ገልጸዋል፡፡
‹‹አሁን በሚታየው አካሄድ የግል ዘርፍ የሚባለው ነገር ትርጉሙ በጣም እየጠፋ ነው፤›› ያሉት አቶ ብርሃነ የግል ዘርፉ በኢሕአዴግ ጠፍቶ የግል ዘርፍ የሚባሉት የፓርቲ ድርጅቶች መሆናቸውን በማመልከት ‹‹አሁን ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ባላውቅም የግል ዘርፉ ማድረግ ያለበትን እነሱ እያደረጉት ከመንግሥት ጋር የተለጠፉ ነጋዴዎች ፍላጎት ያላቸው ስላሉ የኢትዮጵያ ነጋዴ ሊጠበቅ የሚችለው ይህንን ግልጽ አድርጎ ማየት ሲቻል ብቻ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በተለይ የንግድ ማኅበረሰቡ የሚያስማማው ነገር ስለመኖሩ በማመልከትም ይህንን የጋራ ፍላጎቱን ሊያሟላለት የሚችል አመራር እንደሚያስፈልግም አክለዋል፡፡ ይህንንም አባባላቸውን ‹‹የሸቀጥ ዋጋ ሲጨምር የተጨመረበት ምክንያት የፖሊሲ ድክመት ሊሆን ይችላል፡፡ የአፈጻጸም ድክመት ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ከተራ ኃላፊ ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ ይህንን ያደረገው ስግብግብ ነጋዴው ነው ይባላል፡፡ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ በተፈጠረ ቁጥር የመጀመርያ ተጠያቂ የሚሆነው የንግድ ኅብረተሰብ ነው፤›› በማለት የገለጹት አቶ ብርሃነ እንዲህ ባሉ ምክንያቶች የንግድ ኅብረተሰቡ የጋራ ፍላጎት ስላለው ይህንን የጋራ ፍላጎት የሚጠብቅለት ድርጅት እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል፡፡ ለአጠቃላይ የንግዱ ኅብረተሰብ የሚጠቅም ነገር ለማድረግ የሚችል ድርጅት አስፈላጊ መሆኑንም በመግለጽ የንግድ ምክር ቤቶች አደረጃጀት ጠንካራ መሆን እንደሚገባው አመልክዋል፡፡
አዲሱን ረቂቅ አዋጅ ሲመለከቱት ገና ከመጀመርያው የሚያስደነግጥ ነገር ማየታቸውን የገለጹት አቶ ብርሃነ ‹‹ተዓማኒነት ያለው የንግድ ምክር ቤት›› በሚል በአዋጁ የተቀመጠው መንግሥት የሚፈልገው ተዓማኒነት ያለው የንግድ ምክር ቤት ነው የሚፈልገው የሚለውን ያመለክታል፡፡ ስለዚህ እኛ የምንፈልገው ይህንን ነው ብለን ያቀረብነውን ወደ ጎን አድርጎ እኛ እንዲሆኑ የምንፈልገው እንደዚህ ነው ካለ ችግር ሊኖረው ስለሚችል የንግድ ኅብረተሰቡ የሚስማማበት አዋጅ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
ከ18 ዓመታት በፊት የንግድ ምክር ቤቶች አዋጅ ቁጥር 341/95 ሲወጣ በወቅቱ የነበረው የንግድ ምክር ቤቱ ተሳትፎ ምን ይመስል ነበር የሚል ጥያቄ ላይ አቶ ብርሃነ ወደ ኋላ መለስ ብለው የሚያስታውሱትን አካፍለዋል፡፡
የንግድ ምክር ቤቶች አዋጅ በ1995 ዓ.ም. በዚያ መልኩ እንዲቀየር የተፈለገው ሁለት የራሱ ምክንያቶች ነበሩት ያሉት አቶ ብርሃነ ይህም አዋጁ የመንግሥትን ፍላጎት የሚጠብቅ ሆኖ እንዲወጣ በመፈለጉ ነው፡፡ ‹‹ከአነሳሱ ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን በተቆጣጠረበት ጊዜ አንድ ሊቆጣጠረው ያልቻለ ቦታ ቢኖር የንግድ ምክር ቤት ነበር፡፡ ከፍተኛ መካረር የተደረገበት ነበር፤›› ያሉት አቶ ብርሃነ ጠንካራ የነበረው የንግድ ምክር ቤት እንዲፈርስ መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡
ኢሕአዴግ ከመምጣቱ በፊት የነበረው አደረጃጀት ከዘጠኙ የቦርድ አባላት ውስጥ አሥሩ የመንግሥት ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች ናቸው፡፡ የግል ዘርፉን የሚወክል አንድ ሰው ብቻ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ የኮርፖሬሽን ኃላፊዎችን ማባረር ሲጀምር እነሱ ሲደናገጡ ንግድ ምክር ቤቱ ባዶ ሊቀር መቻሉን ጠቁመው በወቅቱ በምክር ቤቱ የቀሩት ነፍስ ኄር አቶ ውብሸት ወርቃለማው ብቻ ነበሩ፡፡ እሳቸውን ማገዝ ያስፈልጋል ተብሎ ስለታሰበ በወቅቱ ጠንካራ የነበረው የኢትዮጵያ የግል ኢንዱስትሪዎች ማኅበር የሌሎች ማኅበራት ማጠናከሪያ እንቅስቃሴ ተደርጎ ንግድ ምክር ቤቱ ጠንካራ እንዲሆን መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡ ይህም መንግሥት ሳይወድ በግዱ በቦርዱ ውስጥ የግል ዘርፉ ብቻ ያደረገ ያደረገው መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ከዚያም በኋላ የንግድ ኅብረተሰቡንና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመጠበቅ ምክር ቤቱ ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ ሁልጊዜ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ከፖለቲካ ጋር መያያዛቸው ስለማይቀር ይኼ በከፍተኛ ደረጃ መንግሥት የሚያሳስበው በመሆኑ መንግሥት ንግድ ምክር ቤቶች ራሳቸውን እንዲያከስሙ ማድረግ ያስፈልጋል ወደሚለው ውሳኔ ገባ፡፡ ይህንንም ለማድረግ የተወሰደው የመጀመርያ ውሳኔ አንድ ነጋዴ ፈቃድ ለማውጣት ሲሄድ የምክር ቤት አባልነት ክፍያ እንዲፈጽም ይጠየቅ የነበረውን ክፍያ አስቀረ፡፡ በዚያን ወቅት ነጋዴው ሁሉንም ክፍያ ስለሚከፍል የንግድ ምክር ቤቶች አቅም እንደሚሰጣቸው ስለታወቀ ይህ ክፍያ ሲቀር ይህ ገቢ ያጥራቸዋል በማለት የተወሰነ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡ ስለዚህ ራሳቸውን ወደሚያፈርሱበት ደረጃ ይሄዳሉ በሚል የተተገበረ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ንግድ ምክር ቤቶች ስትራቴጂያቸውን ቀይረው ለንግድ ማኅበረሰቡ አገልግሎት በመስጠት አባልነት በፈቃደኝነት ሊሆን ይገባል በማለት ስትራቴጂክ በመያዙ በዚህም በርካታ አባላትን ለማቆየት ተቻለ፡፡ በርካታ አባላቱን ለማቆየት የንግድ ምክር ቤቶች አደጀረጃጀት በተለይ በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት አደረጃጀት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች መንግሥት የሚፈልጋቸው ብቻ እንዲሆኑ ስለተፈለገ አወቃቀሩ ላይ የመንግሥት እጅ እንዲገባበት ተደረገ፡፡
ይኽ በመሆኑም ክልል አካባቢ የነበሩ የንግድ ምክር ቤቶች ከፍተኛ የሆነ የክልል ባለሥልጣናት ተፅዕኖ ይደርሳበቸው ነበር፡፡ ያንን ተፅዕኗቸውን ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት እንዳመጡትም አክለዋል፡፡
በወቅቱ የመንግሥት ተፅዕኖ ከባድ ቢሆንም ያን ሁሉ ተቋቁሞ ምክር ቤቱ የንግድ ኅብረተሰቡን ድምፅ ለማሰማት የሄደው፡፡ ፍላጎቱ በንግድ ኅብረተሰቡ ላይ የመንግሥት ተፅዕኖ ለማሳደር ስለነበር አሁን ሥራ ላይ ያለው አዋጅ ሊወጣ የቻለው የሚለውን አመለካከታቸውን ተናግረዋል፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ ሊደርስ የሚገባው ደረጃ ላይ ላለመድረሱ ምክንያቱ ይህ ነው፡፡ በመሆኑም አሁንም አዲሱ ረቂቅ አዋጅ በትክክል የንግድ ማኅበረሰቡን ፍላጎት የሚያሟላ መሆኑን በደንብ መፈተሽ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡