ለአሠልጣኞች የአንደኛ ደረጃ ሥልጠና መሰጠት ተጀመረ
ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ቅድመ ዝግጅት የተመረጡ ብሔራዊ አትሌቶች በመጪው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ ስታዲየም የመጀመርያ ዙር ቅድመ ማጣሪያ እንደሚያደርጉ የኢትዮጵያ አትሌቲከክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡ ማጣሪያው ከ800 እስከ 10 ሺሕ ሜትር በሁለቱም ጾታ የተመረጡ አትሌቶችን ይመለከታል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ባለፈው ታኅሣሥ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በሐዋሳ ባካሄደው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ፣ በቶኪዮ አስተናጋጅነት ከስድስት ወር በኋላ ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው 32ኛ ኦሊምፒያድ በሦስት የስፖርት ዓይነቶች በአትሌቲክስ፣ ወርልድ ቴኳንዶና በሴቶች ብስክሌት ቅድመ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ መግለጹ ይታወሳል፡፡
ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በተለይ በአትሌቲክስ ከ120 በላይ አትሌቶች ለቅድመ ዝግጅት ተመርጠው በሆቴል እንደሚገኙ ገልጾ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በራሱ መንገድ ማጣሪያ በማድረግ መያዝ የሚገባቸው አትሌቶች ተይዘው ዋናው ዝግጅት እንደሚጀመር ለጉባዔው ማስረዳቱ አይዘነጋም፡፡
በዚህ መነሻነት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአምስት የውድድር ዓይነቶች ማለትም በ800 ሜትር፣ 1,500 ሜትር፣ በ3,000 ሜትር መሰናክል፣ በ5,000 እና 10,000 ሜትር በሁለቱም ጾታ ለቅድመ ዝግጅት መርጦ፣ በመጪው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ ስታዲየም የመጀመርያ ዙር ማጣሪያ እንደሚያደርግ ይፋ አድርጓል፡፡
በሌላ በኩል ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ቀደም ሲል በአገር ውስጥ የሁለተኛ ደረጃ የአትሌቲክስ ሥልጠናን ወስደው ላጠናቀቁና በሙያው ሥልጠና እየሰጡ ለሚገኙ አሠልጣኞች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሊያደርጋቸው የሚችል የአንደኛ ደረጃ ሥልጠና እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ሥልጠናው ከጥር 2 እስከ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ የሚቆይ ነው፡፡
በብሔራዊ ወጣቶች ስፖርት አካዴሚ በሚሰጠው በዚሁ የአንደኛ ደረጃ የአሠልጣኞች ሥልጠና ላይ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ 24 ሠልጣኞች ይሳተፋሉ፡፡ በሁለት ዙር የሚሰጠውን ሥልጠናው የሚሰጡት ደግሞ የቀድሞ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህርና አሠልጣኝ አቶ አድማሱ ሳጅና በፌዴሬሽኑ የጥናትና ምርምር ባለሙያ አቶ ሳሙኤል ብርሃኑ መሆናቸው ታውቋል፡፡