የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ በአዲሱ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነት ‹‹ትክክለኛ ዕድሜ ለኢትዮጵያ ስፖርት›› በሚል መሪ ቃል የሚያካሂደው የአንደኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ የውድድር ደንብ ላይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ምክክር በማድረግ የተለያዩ ውሳኔ አሳለፈ፣ የውድድር አውራ ደንብም አፀድቋል፡፡
ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ከትግራይ በስተቀር ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የስፖርት ኮሚሽነሮች፣ የብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ማክሰኞ ጥር 4 ቀን 2013 ዓ.ም. በጁፒተር ሆቴል በወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ በቅድሚያ መደረግ ስለሚገባቸው ተግባራት ተወያይቷል፡፡
በመድረኩ ውድድሩ በሚደረግበት ወቅት የትምህርትና መሰል አገራዊ ጉዳዮች ጋር መጣረስ እንዳይኖር ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ፣ በዋናነት ከኦሊምፒክ ውጪ የሆኑ ስፖርቶች የሚሳተፉበት መንገድ፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በትክክለኛ ዕድሜ ለመቅረብ ማድረግ በሚገባቸው ቅድመ ሁኔታ ላይ እንዲሁም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በተመለከተ ጠንካራ የጤና ኮሚቴ ሊኖር እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
ሌላው ከፀረ አበረታች ቅመሞች ጋር በተገናኘ ጠንካራ የግንዛቤ ሥራ መሠራት እንደሚገባ በመድረኩ ተነስቶ ምክክር የተደረገ ሲሆን፣ በመጨረሻም የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ አውራ ደንብ በሙሉ ድምፅ መፅደቁ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በመረጃ ትስስር ገጹ አሳውቋል፡፡