አንበሳ ኢንሹራንስ ኩባንያ የሕይወት መድን ሽፋን አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችለውን የ20 ሚሊዮን ብር ካፒታል መመደቡንና በ2012 የሒሳብ ዓመት ከ53.3 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉን ገለጸ፡፡
ኩባንያው የ2012 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው መረጃ የሕይወት የመድን ሽፋን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ካፒታል በመመደብ ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑና በዚህም የሚሰጠውን የመድን አገልግሎት በማስፋት በኢንዱስትሪው የተሻለ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቀጠል መሰናዳቱን አስታውቋል፡፡
በኢንዱስትሪው ከሚስተዋለው ዋጋን መሠረት ያደረገ የከረረ ውድድር አገሪቱ ካስተናገደቻቸው አስከፊ የማኅበረሰብ ቀውሶች እንዲሁም ባልታሰበ መልኩ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ጋር ተያይዞ በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ላይ የተፈጠሩትን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ በ2012 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ከ53.3 ሚሊዮን ብር በላይ ማተረፉንም ገልጿል፡፡ ይህ የትርፍ ምጣኔ ከ2011 የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር አራት ሚሊዮን ብር ወይም 8.1 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡
አንበሳ ኢንሹራንስ ዓመታዊ ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው በ2012 የሒሳብ ዓመት ከተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ያገኘው ገቢ በ34 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህም ለኩባንያው ዓመታዊ የትርፍ ዕድገት አስተዋጽኦ እንደነበረውና በጥቅሉ በ2012 የሒሳብ ዓመት ከተለያዩ ኢንቨስትመንቶች 51 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገልጿል፡፡ እነዚህ ገቢዎች የተገኙት ኩባንያው በባንኮች ካለው የቁጠባና የጊዜ ገደብ ተቀማጮች የወለድ ገቢ፣ ከአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ከእናት ባንክ፣ ከኢትዮ ሬኔስንስ (ህዳሴ) አክሲዮን ማኅበር እንዲሁም ከሰላም ባስ አክሲዮን ማኅበር የትርፍ ክፍፍልና የኪራይ ገቢዎች የተገኘ መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
እንደ ኩባንያው መረጃ በሒሳብ ዓመቱ ከወለድ ያገኘው ገቢ 31.1 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም የወለድ ገቢ በ2011 አግኝቶት ከነበረው በ27.5 በመቶ ዕድገት ያሳየ ነው፡፡ ከተለያዩ ኢንቨስትመንቶቹ ያገኘው የትርፍ ክፍፍል ድርሻ ያገኘው ገቢው ደግሞ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረበት 7.5 ሚሊዮን ብር ወደ 10.4 ሚሊዮን ብር ገከፍ ብሏል፡፡ ከሌሎች ገቢዎች ደግሞ 2.9 ሚሊዮን ብር ማግኘት መቻሉንም ኩባንያው አስታውቋል፡፡
ኢንሹራንስ ኩባንያው በ2012 የሒሳብ ዓመት በአጠቃላይ 386 ሚሊዮን ብር ዓረቦን የሰበሰበ ሲሆን ይህም 2.9 ሚሊዮን ብር ወይም የ1.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የተከፈለው የተጣራ ካሳ ክፍያው 184.5 ሚሊዮን ብር እንደነበርም አመልክቷል፡፡
የአክሲዮን ማኅበሩ የተከፈለ የካፒታል መጠን ካለፉት ዓመት በተለየ የ25.7 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 148.5 ሚሊዮን እንዲሁም አጠቃላይ ካፒታሉና የተቀማጭ መጠኑ ብር 243.1 ሚሊዮን መድረሱን አመልክቷል፡፡
በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የኩባንያው አጠቃላይ የሀብት መጠን በ2011 የሒሳብ ዓመት ከነበረው 722.6 ሚሊዮን ብር ወደ 842 ሚሊዮን ብር ማደጉንም ገልጿል፡፡ ይህ የሀብት መጠን የ16.5 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡
አንበሳ ኢንሹራንስ ኩባንያ ከአሥር ዓመታት በፊት በ16 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል እንዲሁም በ66.4 ሚሊዮን የተመዘገበ ካፒታል የተመሠረተ ሲሆን፣ በ2012 መጨረሻ ላይ የተከፈለ ካፒታሉ 148.5 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡
ኩባንያው በ2012 መጨረሻ ላይ የቅርንጫፎቹንና የአገናኝ ቢሮዎቹን ቁጥር 42 ያደረሰ ሲሆን፣ የአጠቃላይ ሠራተኞቹም ቁጥር 338 ነው፡፡