Wednesday, December 6, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ተወዳዳሪ ለመሆን አስቻይ የንግድ ሥርዓት የሚጠይቀው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ተግባራዊ መደረጉ ይፋ ከሆነ አንደኛ ሳምንቱን ይዟል፡፡ ኢትዮጵያም ለአፍሪካ ገበያ በሯን ከፍታለች፡፡ የአፍሪካ አገሮችም ለኢትዮጵያ በራቸውን ከፍተው ያለ ታሪፍ መገበያየት የሚያስችለውን ዕድል መፍጠር ችለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን ነፃ የንግድ ገበያ መቀላቀሏን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማስወሰን የገባችበት ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት አንድ ተብሎ በተጀመረበት ዕለት፣ በይፋ የተጀመረውን አፍሪካ ነፃ የንግድ ገበያ አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ንግድ መጀመሩ ለአኅጉራችን ትልቅ ደስታ ነው፤›› በማለት፣ ‹‹እንኳን ደስ አለን፤›› ብለዋል፡፡

አያይዘውም፣ ‹‹የአዲሱ የአፍሪካ የንግድ ቀጣና ስምምነት ውስን አዕምሮዎቻችን ለሐሳብ፣ ገበያችንን ደግሞ ለንግዱ ክፍት የሚሆንበት ቀጣናዊ ውህደት ነው፡፡ ንግድ በእጅጉ አሳሳቢ የሆኑ ግንኙነቶችን ቀላል የማድረግ ባህሪ አለው፡፡ የተቀናጁ ገበያዎች ደግሞ ብልፅግናን ያስገኛሉ፤›› በማለት ጅማሬውን አወድሰዋል፡፡ ይህ መልዕክት ኢትዮጵያ ከዚህ ገበያ ተጠቃሚ ትሆናለች የሚለውን እሳቤ የያዘ ነው፡፡

በዚህ ገበያ መፈጠርና ኢትዮጵያም አንዷ አገር መሆኗ ዕድሉን ከተጠቀመችበት እንደሚያዋጣ ብዙዎች የሚስማሙበት ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የንግዱ ኅብረተሰብ አባላት፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችና ነገሩን ጉዳዬ ብለው እየተከታተሉ ያሉ ወገኖች ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አካል መሆኗ ላይ ያላቸው ምልከታ አዎንታዊ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ገበያ ውስጥ መግባት አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፉ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) አንዱ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ስምምነቱ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ያደርጋታል ብለው ያምናሉ፡፡

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናን አጀማመር በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡን የኢኮኖሚ ባለሙያ ደግሞ፣ ‹‹አፍሪካውያን ገበያችንን ለምን አናቀላቅልም›› በሚል ተነስቶ የተጀመረና ግቡን የመታ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ አፍሪካውያን አንድ ነፃ የንግድ ቀጣና እንፍጠር በሚል ከተስማሙ በኋላ ፕሮቶኮል አበጅተውና ተስማምተው ወደ ተግባር የገቡበት ትልቅ ዕርምጃ ነው ይላሉ፡፡

የዚህ ቀጣና መፈጠር የአፍሪካን 1.2 ቢሊዮን ሕዝብ ገበያ በአንድ ላይ ለማምጣት የሚያስችልና ለአፍሪካ የዕድገት መልካም ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ አፍሪካ የሌሎች ሸቀጣ ሸቀጥ ማራገፊያ ከምትሆን የራሷን የሥራ ዕድልና ገበያ ፈጥራ መጠቀም እንደምትችል ታምኖበት የተገባበትም ነው፡፡

ይህንንም በምሳሌ ሲያስረዱ በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የፋብሪካ ምርት የ110 ሚሊዮን ሕዝብ ገበያ ታሳቢ ተደርጎ የሚሠላ ሲሆን፣ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና መተግበር ደግሞ የገበያ ዕድሉን ወደ 1.2 ቢሊዮን ከፍ ያደርገዋል፡፡

እንደ ንግድ ይህ ትልቅ ዕድል ነው የሚሉት ባለሙያው፣ አፍሪካውያን በመካከላቸው ያሉትን የገበያ መሰናክሎች በማስወገድ ለንግድ ምቹ ሁኔታ መፍጠር የቻሉበት በመሆኑ በመልካም የሚታይ ጅማሬ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡  

ኢትዮጵያ ይህንን ገበያ መቀላቀሏ ደግሞ ይጠቅማታል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ይህንን ትልቅ የገበያ ዕድል እንዴት መጠቀም እንችላለን የሚለው ጉዳይ ግን ቁልፍ ነገር ስለመሆኑ ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

ኢትዮጵያ የዚህ ቀጣና አባል መሆኗ ተጠቃሚ የሚያደርጋትና ገበያውን የሚያሰፋላት ነው፡፡ ከአፍሪካ የሚገባው ምርት አሁን ላይ ብዙ ስላልሆነ ተጠቃሚ የሚኮንበት ዕድል የሰፋ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች በአንፃራዊነት ሲታዩ በዚህ ቀጣና አባልነቷ ጥሩ ተወዳዳሪ ያደርጋታል፡፡

ሆኖም ይህ ተወዳዳሪነት ዛሬ በአንድ ጀምበር የሚመጣ ሳይሆን፣ የወደፊት ተጠቃሚነቷን የሚያሳይ ነው፡፡ ውድድሩ ከጎረቤት አገሮች ጋር ስለሆነ እንጂ በማኑፋክቸሪንግ ጡንቻቸው ከፈረጠሙ የእስያ አገሮች ጋር ቢሆን ብዙ ትርጉም ላይኖረው ይችላል፡፡ ሆኖም ከአፍሪካ ገበያ በማኑፋክቸሪንግ ጥሩ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚቻልበት ዕድል አለ ብለዋል፡፡

 አጠቃላይ ምልከታው አፍሪካውያን ትልቅ የገበያ ዕድል ስለመፍጠራቸው ያመለክታል ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ተነፃፃሪ ጥቅሟ የተፈጥሮ ሀብቶቿ ናቸው የሚሉት ኢንጂነር መላኩ ደግሞ የግብርና፣ የቁም ከብት፣ የማዕድን፣ የደንና የመሳሰሉትን  የተፈጥሮ ሀብቶች በጥሬው እየተላኩ የምንወዳደር ከሆነ ትርጉም የለውም ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው መጀመርያ ምርት እነሱ ከሚፈልጉት እኛ ምን ያህል እናመርታለንና ከዓለም አቀፍ አንፃር ምን ያህል ተወዳዳሪ ያደርገናል የሚለው መታየት እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡

ከአፍሪካ አገሮች የሚመጣው ገቢ ምርት ምን ያህል ነው? መሠረታዊ ናቸው ወይስ የቅንጦት? ወደሚለው ትንተና መሄድም ያስፈልጋል፡፡

ከአፍሪካ አገሮች ጋር የሚደረገው የንግድ ክፍፍል ትንሽ ነው፡፡ የዚህ ገበያ መጀመር ግን ከዚህ በኋላ ገበያውን ሊጨምር ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ግን የተመረተውን ለአፍሪካ ገበያ ማቅረብ ካልተቻለ፣ ይህ የተመቻቸ ገበያ ለትልቅ የውጭ አምራቾች ማራገፊያ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓመት እስከ 18 ቢሊዮን ዶላር ከውጭ የምታስገባ መሆኑንም በማስታወስ፣ ከዚህ ውስጥ ከአፍሪካ አገሮች የምታስገባው 4.1 በመቶ አካባቢ ብቻ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ኢትዮጵያ ዓመታዊ አጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ ወደ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 20 በመቶ አካባቢ የሚሆነው ወደ አፍሪካ አገሮች ከምትልከው የምታገኘው ነው፡፡ በመሆኑም እንዲህ ያሉት የገቢና የወጪ ምርቶች ተሠልተው ከቀጣናዊ ገበያው እንዴት አትራፊ እንሆናለን? የትኛው ምርት ላይ እናተኩር? ማለት ይፈልጋልም ብለዋል፡፡

ከአፍሪካ ያለው የወጪ ንግድ ከፍተኛ ገቢ ንግድ ደግሞ ዝቅተኛ በመሆኑ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አባል በመሆኗ ተጠቃሚ ስለሚያደርጋት ከዚሁ አንፃር መዘጋጀት ተገቢ ነው ብለውም ያምናሉ፡፡

ይህ ሆኖ ግን ኢንዱስትሪው በአጠቃላይ የተወሳሰበ ችግር አለበት፡፡ ችግሩ ባልፈታበት መንገድ ደግሞ ውድድሩ በጣም ከባድ መሆኑን መዘንጋት እንደማያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡

ኢንጂነር መላኩም፣ ውድድሩ ቀላል የሚባል ባለመሆኑ አሁንም ብዙ ሥራ ይጠበቃል ብለው ያምናሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያን የንግድ ኅብረተሰብ ማብቃት ነው፡፡ የንግዱን ኅብረተሰብ ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ለማድረስ ደግሞ ደረጃውን ከፍ የማድረግ ሥራ በብርቱ ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡

እሳቸው የሚመሩት ንግድ ምክር ቤትም ኃላፊነት ይኖርበታል ያሉት ኢንጂነር መላኩ፣ መንግሥትም የራሱን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባው ያምናሉ፡፡ ‹‹ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ነጋዴ እየፈጠርን ካልሄድን ውስጥ ለውስጥ እጥረት እየፈጠረ የሚነግድ ነጋዴ ይዞ መቀጠልና ውድድሩን መጋፈጥ አይችልም ይላሉ፡፡

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ገበያ መፈጠሩ የንግድ ዕድልን ማስፋቱ የሚታመንበት ቢሆንም፣ ይህንን ዕድል እንዴት እንጠቀምበት የሚለው ጥያቄ መልስ የሚሻ መሆኑን የሚያመለክቱት ኢንጂነር መላኩ፣ በጥራት፣ በዋጋ፣ በብዛትና በመሳሰሉት አቅም መፍጠር ላይ ሊሰመርበት እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡ ገዥው በሚፈልገው ብዛት ልክ ማቅረብ መቻል ግድ ስለሚልም በዚህ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ኢንዱስትሪ አለን ወይ? የሚለው ጥያቄ መልስ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡  

ስለዚህ ዕድሉ መኖሩ ብቻ ሳይሆን ዕድሉን ለመጠቀም ማሥላት ያስፈልጋል፡፡ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር አብዛኛዎቹ ፋብሪካዎች ለጥሬ ዕቃ ግዥ የሚሆናቸው የውጭ ምንዛሪ ስለማያገኙ ሲቸገሩ ይታያል፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የጥቁር ገበያን ሳይነካ የሚገባ ጥሬ ዕቃ የሌለ በመሆኑ፣ እንዲህ ያለውን ችግር ለመፍታት ካልተሠራ ተወዳዳሪነት ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡

‹‹ኡጋንዳ ያለ አንድ ፋብሪካና እዚህ ያለ አንድ ፋብሪካ ጥሬ ዕቃውን በተመሳሳይ ዋጋ ይገዙታል ወይ የሚለውም መመለስ ይኖርበታል፤›› ያሉት ኢንጂነር መላኩ፣ የኡጋንዳው ፋብሪካ በፈለገው መንገድ ዶላር እያገኘ ጥሬ ዕቃ እየገዛ ሲያመርት፣ የኢትዮጵያው ፋብሪካ በስድስት ወራት የውጭ ምንዛሪ ካገኘ እንዴት አድርጎ ሊወዳደር ይችላል? የሚልም ጥያቄ በማንሳት ጥሩ ተጠቃሚ ለመሆን የውጭ ምንዛሪ ግኝቱም ወሳኝ መሆኑን ሳያመላክቱ አላለፉም፡፡

ሌላው መታየት ያለበት ብለው የጠቆሙት ለአምራቾች የሚሰጠው ማበረታቻ ነው፡፡ የኬንያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አንድ ምርት ለማምረት የሰጠው ማበረታቻና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ማበረታቻ ታይቶ መስተካከል ይኖርበታል፡፡

ስለዚህ መፈተሽ ያለባቸው በርካታ ነገሮች አሉ የሚሉት ኢንጂነር መላኩ፣ መንግሥትና የንግዱ ኅብረተሰብ በአንድ ላይ ሆኖ ዕድሉን መጠቀም የሚያስችል ስትራቴጂ በአንድ ላይ ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል የሚል እምነት አላቸው፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ደግሞ፣ የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ከ15 በመቶ ላይ 20 በመቶ አካባቢ ስለሆነ ወደ ውጭ ከመላክ እዚህ አገር መሸጥ ያዋጣዋል፡፡ ነገር ግን ትልቁን ገበያ መቀላቀል ግድ ስለሆነ ለዚህ የሚሆን ምርት የግድ ይለናል ይላሉ፡፡

እንዴት አድርገን ነው? ከዚህ ልንጠቀም የምንችለው የሚለው ላይ አሁንም ብዙ መሠራት እንዳለበት እሳቸውም ይስማሙበታል፡፡ በእሳቸው ምልከታ ወደ አፍሪካ አገሮች የምንልካቸው ምርቶች የትኞቹ ናቸው? ብሎ መሠራት አለበት፡፡ ኢንጂነር መላኩ ደግሞ፣ በዚህ ዕድል የንግዱ ኅብረተሰብ ተወዳድሮ ማሸነፍ የሚችለው መንግሥት አስቻይና አመቻች የሆኑ አሠራሮች ሲያዘጋጅ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ አሁን ላይ ተወዳዳሪ የሚያደርጉ የተለያዩ ምርቶች አሉ፡፡ ጨርቃጨርቅ፣ የቆዳ ምርቶችና የመሳሰሉት ተወዳዳሪ የሚያደርጉ ምርቶች በመሆናቸው በእነዚህ ቶሎ ገበያ ውስጥ መግባት ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ በኋላ ደግሞ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ዕቅድ መታሰብ ያለበት 54ቱ የአፍሪካ አገሮች ከሌላው አገር ለምሳሌ ከህንድ፣ ከቻይና፣ ከቱርክ ከእስራኤልና ከመሳሰሉ የሚያመጧቸው ግን እኛ ልናቀርብላቸው የሚችሉ ምርቶች ምንድናቸው ተብሎ መጠናት አለበት፡፡

ኢትዮጵያ ከእስያና ከሌሎች አገሮች የምታስገባቸው፣ ግን ከአፍሪካ አገሮች ልታመጣ የምትችላቸው ምርቶች ምንድናቸው ብሎ ማሰብም ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም ንግዱ በመቅረቡ ከትራንስፖርት ዋጋ መቀነስ ይቻላል በኮሚሽን የሚገኙ ዕድሎችም አሉ፡፡ ስለዚህ የአፍሪካ ንግድ ቀጣና አባልነት ንግዱን የበለጠ ያሳልጣል ማለት ነው፡፡

በዚህ የገበያ ዕድል ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ልትሆን የምትችለው በተግባር በሚሠሩ ሥራዎች ነው፡፡ ይህንን ሥራ ደግሞ መንግሥት ወይም ነጋዴ በመሥራት የሚያመጡት አይደለም፡፡ መንግሥት ተወዳዳሪ ነጋዴዎች እንዲወጡ አስቻይ የሆኑ ነገሮችን አመቻችቷል ወይ? የሚለውን መመለስ አለበት፡፡

የንግድ ኅብረተሰቡም በተፈጠረለት መስክ ለውድድር ራሱን ብቁ አድርጎ እንዲዘጋጅ ማድረግንም የሚጠይቅ ነው፡፡ የንግድ ኅብረተሰቡን ጉድለት መንግሥት እየሞላለት፣ የኢትዮጵያ አምራቾች ተወዳዳሪነትን እያረጋጠ፣ እያረመና እያበቃ መሄድ ይጠበቅበታል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች