የህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌትና ዓመታዊ አስተዳደርን በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ሲደረግ የቆየው ሰባት ወራትን የፈጀ የመፍትሔ ፍለጋ ውይይት ሰሞኑን ያለ ውጤት ተጠናቋል።
የድርድሩ ቀጣይ ዕጣ ፈንታን ለመወሰንም ጉዳዩ ለወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ እንደተመራ ተደራዳሪ አገሮቹ በይፋ አስታውቀዋል።
የሦስቱ አገሮች ድርድር እሑድ ጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ቢካሄድም፣ በሱዳን መንግሥት በቀረበው ተቃውሞ ምክንያት ወደ ቀጣይ የድርድር ምዕራፍ መሻገር አልቻለም።
ለድርድሩ መቋረጥ ምክንያቱንና በመጨረሻው ድርድር ወቅት የተነሱ ነጥቦችን አስመልክቶ፣ የኢትዮጵያ የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም ከሳምንት በፊት እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ድርድር ሱዳን ባለመገኘቷ ምክንያት ሳይካሄድ የቀረ በመሆኑ፣ የአፍሪካ ኅብረት አስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር ድርድሩን ለማስቀጠል ይረዳል በሚል አገሮቹ ለሦስት ቀናት ከአፍሪካ ኅብረት ባለሙያዎች ጋር የሁለትዮሽ ስብሰባ እንዲያካሂዱ፣ በማስከተል የሦስትዮሽ ስብሰባ እንዲካሄድና ውጤቱ ለሊቀመንበሯ የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲገለጥ ሐሳብ እንደቀረበ ተመላክቷል።
በዚሁ መሠረት ኢትዮጵያና ግብፅ የተቀመጠውን የድርድር አማራጭ ተቀብለው ለመቀጠል ተስማምተው የነበረ ቢሆንም፣ ሱዳን ሐሳቡን ባለመቀበሏ ስብሰባው በዚህ ሁኔታ ያለ ውጤት መጠናቀቁን ያስረዳል።
ከሳምንት በፊት እንዲካሄድ ተወስኖ በነበረው ድርድር የሱዳን መንግሥት ባለመገኘቱ መተላለፉን የሚገልጸው ይኸው በኢትዮጵያ በኩል የወጣ መግለጫ፣ ሱዳን በዚያ ሳምንት ሊካሄድ ከነበረው ድርድር ራሷን ያገለለችበት ምክንያት ቀጣይ ድርድር ከመካሄዱ በፊት ከአፍሪካ ኅብረት ባለሙያዎች ጋር ሦስቱም አገሮች የተናጠል ስብሰባ እንዲያደርጉ ያቀረበችው ጥያቄ መልስ ባለማግኘቱ መሆኑን ይጠቁማል።
ነገር ግን ጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም. በተጀመረው የሦስቱ አገሮች ድርድር፣ የሱዳንን ጥያቄ ሊመልስ በሚችል ደረጃ ሦስቱ አገሮች ወደ ቀጣይ ድርድር ከመግባታቸው አስቀድሞ ለሦስት ቀናት ከአፍሪካ ኅብረት ባለሙያዎች ጋር የሁለትዮሽ ስብሰባ እንዲያደርጉ ሐሳብ መቅረቡን ያስታውሳል። ቢሆንም ይህንን ጥያቄ ከሳምንት በፊት ያነሳችው ሱዳን፣ የቀረበውን ሐሳብ ባለመቀበል ለአፍሪካ ባለሙያዎች የተጨማሪ ኃላፊነት ቢጋር ካልተዘጋጀ በቀር ድርድር ለማካሄድ እንደማትችል የሚገልጽ አቋም መያዟን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ የሱዳንን ጥያቄዎች ለመመለስ እንዲቻል በግድቡ ደኅንነት፣ በመረጃ ልውውጥ፣ እንዲሁም በሌሎች ቴከኒካዊ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ለመስጠት ዝግጁነቷን በወቅቱ እንዳስታወሰችም መግለጫው ጠቁሟል።
ይህንንም ድርድሩ በሚካሄድበት በአሁኑ ወቅት ውጤታማና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ በመመሥረት የመረጃ ልውውጡን ለመጀመር፣ ኢትዮጵያ ፈቃደኛ መሆኗን እንዳስታወቀች ይገልጻል።
ነገር ግን ሱዳን በያዘችው አቋም በመፅናቷ ድርድሩ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ መሸጋገር አልቻለም።
በመሆኑም በቀጣይነት የአፍሪካ ኅብረት የአስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር ለወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የስብሰባውን ውጤት እንዲያቀርቡ መወሰኑን፣ ሦስቱ አገሮችም የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ምከር ቤት የሚሰጠውን ቀጣይ አቅጣጫ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን አመልክቷል።
ያልተጨበጠው የሱዳን ፍላጎትና ተቃርኖዎች
የሱዳን መንግሥት ተደራዳሪ ቡድንን የሚመሩት የአገሪቱ የመስኖና የውኃ ሀብት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ያሲር አባስ ባለፈው ዓመት በሰጡት መግለጫ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ጥራትና በሱዳን ላይ ሊያደርስ በሚችለው ውስን አሉታዊ ተፅዕኖ ላይ የሱዳን መንግሥት ሥጋት የነበረው ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ የሱዳን መንግሥት ሥጋቶችን ለመቅረፍ በወሰደችው ቁርጠኛ አቋም የሥጋት ምንጭ የነበሩት ጉዳዮች እንደተቀረፉ ተናግረው ነበር።
የህዳሴ ግድቡ ግንባታ፣ የግድብ ግንባታ ልምድ ባለው ኩባንያ የሚከናወንና የግንባታ ጥራቱም ከግብፅ ግድቦች በተሻለ ደረጃ የሚከናወን በመሆኑ፣ የሱዳን ሥጋት መቀረፉን፣ የቀሩ ጉዳዮችንም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በየጊዜው በመመካከር የሚፈቱ እንደሚሆን እምነታቸውን ሱና ለተባለው ሱዳን መንግሥት የዜና ወኪል ገልጸው ነበር።
አሁን ግን ፕሮፌሰር ያሲር አባስ እያንፀባረቁ ያለው ሐሳብ ከቀደመው አቋማቸው ጋር የሚጋጭ ከመሆኑ ባሻገር፣ በህዳሴ ግድቡ ላይ እየተካሄደ ያለው ድርድር ወደ ውጤት እንዳይሸጋገር ምክንያት ሆኗል።
ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በነበረው የህዳሴ ግድብ ድርድር በሱዳን መንግሥትና በኢትዮጵያ መካከል ተመሳሳይ አቋም የማንፀባረቅ ልማድ፣ ዛሬ ወደ ትዝታነት እየተቀየረ ይመስላል።
ከህዳሴ ግድቡ ባሻገርም የድንበር ውዝግብ በሁለቱ አገሮች መካከል የተከሰተ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም እየተባባሰና ወደ ድንበር ጦርነት የመሸጋገር ጥላ አጥልቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በህዳሴ ግድቡ ላይ በአሁኑ ወቅት እየተስተዋለ ያለውን ልዩነትም ሆነ፣ ሱዳን ከኢትዮጵያ በምትዋሰንበት ድንበር ላይ የጀመረችውን ወታደራዊ እንቅስቃሴና ጥቃት በእርጋታ ለማሳለፍ ጊዜያዊ አማራጭ ይዟል።
ለዚህም የሚሰጠው ምክንያት ጉዳዩ የሱዳን ሳይሆን፣ ከጀርባ ያሉ አካላት ሱዳንን በመጎትጎት ለኢትዮጵያ ያዘጋጁት ወጥመድ ነው የሚል ነው።
ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ በሱዳን በኩል ያለውን የልዩነት ነጥብና ምክንያታዊነት የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባላት እንዲያስረዱ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ መልሳቸው፣ ‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዳንሰጥ ታግደናል›› የሚል ሆኗል።
ከተደራዳሪዎቹ መካከል ሁለት ከፍተኛ ባለሙያዎችን በስልክ ለማነጋገር ቢሞከርም፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት እንዳትሰጡ የሚል መመርያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንደተላለፈላቸው ገልጸዋል።
‹‹እስከ ዛሬ በነበረው ሒደት እንዲህ ዓይነት አቋም ተይዞ አያውቅም፤›› ያሉት አንድ የኢትዮጵያ ወገን ተደራዳሪ፣ ‹‹ሕዝብ የማወቅ መብት አለው፣ ነገር ግን ፖለቲከኞቹ ይህንን የወሰኑበት ምክንያት ለእኛ ግልጽ ያልሆነ ፖለቲካዊ ፋይዳ ሊኖረው ስለሚችል ለጊዜው መመርያውን ተቀብለን ዝምታውን መርጠናል፤›› ብለዋል።
የሱዳኑ ተደራዳሪ ፕሮፌሰር ያሲር አባስ የህዳሴ ግድቡ ድርድር ውጤታማ እንዲሆን በአፍሪካ ኅብረት ለተወከሉ ባለሙያዎች ሰፊ ሚና ሊሰጥ እንደሚገባ፣ ይህንንም ዕውን ለማድረግ በግልጽ የተዘረዘረ ቢጋር ሊዘጋጅ እንደሚገባ ሱዳን አቋም መያዟን ሰሞኑን ገልጸዋል።
‹‹ይህ ካልሆነ ግን ሱዳን በዚህ ውጤት አልባ ድርድር ውስጥ መሽከርከር አትፈልግም፤›› ሲሉ የመንግሥታቸውን አቋም ያስታወቁት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ድርድሩንም በሁለት ምዕራፎች ማለትም በመጀመርያ የውኃ ሙሌትና ዓመታዊ የግድብ አስተዳደር ከፍሎ ለመወያየት ሱዳን አትሻም፤›› ብለዋል።
መፍትሔው ወጥ እና ሁሉን አቀፍ ስምምነት በህዳሴ ግድቡ ላይ ማድረግ እንደሆነ፣ በዚህ ሁኔታ የሚደረሰው ስምምነትም አስገዳጅ ሊሆን ይገባል ሲሉ የሱዳንን አቋም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ሱዳንና ግብፅ የሚያንፀባርቁት አቋም ኢምክንያታዊ እንደሆነ፣ ዋና ግቡም ለዘመናት የዘለቀ የዓባይን ውኃ ሁለቱ አገሮች ብቻ በብቸኝነት የመጠቀም ኢፍትሐዊነትን ማስቀጠል እንደሆነ በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች፡፡
ይህንን ኢፍትሐዊነት እንደማትቀበል በማሳወቅም በህዳሴ ግድቡ የመጀመርያ ምዕራፍ የውኃ ሙሌት የመጀመርያ ዓመት ሙሌትን በ2012 ዓ.ም. የክረምት ወቅት ያጠናቀቀች ሲሆን፣ የመጀመርያው ምዕራፍ የመጨረሻ የውኃ ሙሌትን በ2013 ዓ.ም. በሐምሌ ወር እንደምታከናውን ለአደራዳሪው የአፍሪካ ኅብረትና ለሚመለከታቸው ሁለቱ አገሮች ዓርብ ታኅሳስ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በይፋ አስታውቃለች፡፡
ሱዳን ለዚህ ደብዳቤ የተቃውሞ ምላሽ የሰጠች ሲሆን፣ ስምምነት ሳይደረስ የሚደረግ የውኃ ሙሌትን አጥብቃ እንደምትቃወም ፕሮፌሰር ያሲር አባስ ተናግረዋል፡፡
የህዳሴ ግድቡን ድርድርና የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ፣ ሱዳን ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ስታንፀባርቅ የነበረውን አቋም በተቃራኒው በማጠፍ የህዳሴ ግድቡን አጀንዳ ከሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር ለማስተሳሰር እንደጣረች ይገልጻሉ፡፡
የህዳሴ ግድቡ ድርድር በአፍሪካ ኅብረት የአደራዳሪነት ሚና ሥር ከገባ ሰባት ወራት እንደቆጠሩ የገለጹት ባለሙያው፣ በተጠቀሱት ወራት ውስጥም የሱዳን መንግሥት የተለያዩ ተለዋዋጭ ምክንያቶችን በመደርደር ለሰባት ጊዜ ድርድሩ እንዲቋረጥ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
የሱዳን መንግሥት የህዳሴ ግድቡን አጀንዳ ከሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር በማቆራኘት፣ የአጭር ጊዜ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት እየሞከረ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ይህ አዲስ የፖለቲካ መንገድ የህዳሴ ግድቡን አጀንዳ ከኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ማካለል ጋር ለማገኘት ከፍተኛ ሩጫ ውስጥ እንደገባ፣ እ.ኤ.አ. በ1972 በሁለቱ አገሮች መካከል የተደረሰውን ስምምነት እስከ መጣስ እንደ ደረሰ ይገልጻሉ፡፡
በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የድንበር ወሰን ጥያቄ ሁለቱ አገሮች በውይይትና በጋራ የድንበር ኮሚሽናቸው አማካኝነት እስኪፈታ ድረስ፣ ነባራዊ ሁኔታው ባለበት እንዲቆይ የደረሱትን የ1972 ስምምነት በመጣስ ሱዳን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ማድረጓን ጠቅሰዋል፡፡
የዚህ ጉዞ ዓላማ ሁለት ሊሆን እንደሚችል የገለጹት ባለሙያው አንደኛው አጋጣሚውን በመጠቀም ስትራቴጂያዊ የድንበር አካባቢዎችን መቆጣጠር ሲሆን፣ ሌላኛው ስምምነቱን በመጣስ የተናጠል መንገድ ለመከተል ምክንያት የሆናት ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ሙሌት በተናጠል ውሳኔ በማካሄዷ ነው በሚል ጎል ለማስቆጠር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡